“ልጅ ለመውለድ መጥቼ ነው፤ የነዋሪነት ደብዳቤ ጻፉልኝ፣ ማረፊያ ፈልጉልኝ፣ በሚሉ እንግዶች መማረራቸውን የዋሽንግተን ዲሲ አካባቢ ነዋሪዎች ይናገራሉ። “አሜሪካ ሄጄ ልወልድ ነው”፤ ወይም “እሱ እኮ፣ እሷ እኮ አሜሪካ ነው የተወለደው/የተወለደችው” የሚል ጠንከር ያለ አቅምን የሚጠይቅ የማንነት መገለጫ ንግግሮችም እንደቀልድ ከሰዎች አንደበት ጣል ሲደረጉ ይሰማሉ።
አንዲት እናት ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በሚገኙ ሆስፒታሎች ውስጥ በመደበኛ የወሊድ መንገድ ልጅ ለመውለድ ብትፈልግ 10 ሺህ ዶላር 225 ሺሕ የኢትዮጵያ ብር ማለት ነው መክፈል አሊያም የክፍያውን ተመጣጣኝ የሕክምና ኢንሹራንስ በግዢ ማቅረብ ይጠበቅባታል።
ይህን ክፍያ የማይፈጽሙ አሊያም በዲሲ ከተማ በሚገኝ መኖሪያ ቤት ውስጥ በዝቅተኛ ደረጃ መኖሯን ማረጋገጫ አቅርባ የነፃ ኢንሹራንስ አገልግሎት ማግኘት ይጠበቅባታል። ከመደበኛው ውጭ በሆነ በቀዶ ጥገና ከወለደች ደግሞ ክፍያው እስከ 17 ሺሕ ማለትም ከ382 ሺህ በላይ የኢትዮጵያ ብር ይፈጃል።
ኢትዮጵያ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ እንዲህ ያሉ የሕክምና ክፍያዎች አለመፈፀማቸው ያሳሰበው ይመስላል በቅርቡ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ የማኔጅመንት አባላት በዚህ ጉዳይ ላይ መልዕክት ልኳል። በኢትዮጵያ የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ የመረጃ መኮነን እና ቃል አቀባይ ኒኮላስ ባርኔትን ስለጉዳዩ ጠይቄያቸው ነበር።
ደንበኞቻቸው ከቪዛ ሰጪው አካል ቪዛ ስለሚያገኙበት መንገድ መከተል ያለባቸውን መስፈርት ሳይከተሉ ሲቀሩ ለማስተማር ብዙ ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሠራተኞችና ቤተሰቦቻቸው ጉዳይ የዚህ አንዱ አካል እንደሆነ ተናግረዋል።
“ከኤምባሲው የተላከውን መልዕክት ስትመለከችው በዋናነት የሚያስረዳው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሠራተኞችም ሆኑ ሌሎች ቪዛ ጠያቂዎች ወደ አሜሪካ ለምን እንደሚሄዱና ምን ማድረግ እንደሚፈልጉ እውነቱን ሊነግሩን ያስፈልጋል የሚል ነው።”
ለምሳሌ ይላሉ ኒኮላስ ይህንን ሐሳባቸውን በምሳሌ ሲያስቀምጡ “አንድ ሴት የአንድ ዓመት ቪዛ አላት እንበል። ቪዛው በተሰጣት ወቅት እርጉዝ አልነበረችም። እርግዝናው የመጣው ከዛ በኋላ ቢሆንና ቪዛውን ለዛ ተጠቅመውበት ከሆነ ግለሰቧ ምንም ሕገ ወጥ ተግባር አልሠሩም ማለት ነው። ይህም ሆኖ ግን በሆስፒታል ውስጥ የተሰጣቸውን የወሊድ የሕክምና አገልግሎት ወጪ ሙሉ ለሙሉ መክፈል ግዴታ አለባቸው። ለሁለተኛ ጊዜ በሚያመለከቱበት ጊዜም ቪዛውን ለተጠቀሙበት ትክክለኛ ተግባርና እውነቱን መናገር ይጠበቅባቸዋል” ብለዋል።
አያይዘውም “ብዙ ሰዎች ቪዛ ለማግኘት በሚያመለክቱበት ጊዜ የሚያቀርቡት በጣም አስፈላጊ ብለው የሚያስቧቸውን ሰነዶች ፣ የድጋፍ ደብዳቤዎችንና የመሳሰሉትን ነው። ይህ ስህተት ነው። እኛ ምን ዓይነት ሰነድ መሟላት እንደሚያስፈልግ በጣም ግልፅ የሆነ አሰራር አለን። በዋናነት ትኩረት የምንሰጠው ግን የሚሞሉትን ማመልከቻ ነው። ማመልከቻው በሀቅ ላይ ተመስርቶ መሞላት አለበት። አመልካቾች አጭበርብረው ቪዛ ለማግኘት ከሞከሩ ለአንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ለሁል ጊዜውም ሊከለከሉ ይችላሉ። ይህ አክብደን የምናየው ጉዳይ ነው።”
ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር የሚያደርጉት ውይይት ከተለያዩ ቡድኖችና የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመገናኘት ለሚያደርጉት ጥረት አንዱ ማሳያ መሆኑን ገልፀው ሰዎች ሕጎቹን ባለማገናዘብና ባለመረዳት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንዳይወድቁ ይረዳቸዋል ይላሉ ቃል አቀባይ ኒኮላስ።
“ይህ ሕግ ለሁሉም ይሠራል። አሜሪካ ውስጥ ልጅ መውለድም ሆነ በአሜሪካ ውስጥ በሚገኙ የሕክምና ተቋማት ውስጥ ሕጋዊ ሰነድ ይዞ አገልግሎት ማግኘትም ሕጋዊ ነው። ለአገልግሎቱ ክፍያ መፈፀም ግን ግዴታ ነው። በተጨማሪም ለሁለተኛ ዙር ቪዛ ማመልከቻ በሚቀርብበት ጊዜ እውነቱን መናገር አለባቸው። የጉዞው ምክኒያት ለወሊድ ወይም ለሕክምና መሆኑን። ያንን በግልጽ መናገር ያስፈልጋል። መረጃውን ከደበቁና ዋሽተው ካገኘናቸው ያ ትልቅ ማጭበርበር ነው።”
በዋሽንግተን ዲሲ ነዋሪ የሆነውና የኔትዎርክ ኦፍ ፋሚሊ ሰርቪስ ፕሮፌሽናልስ መስራች አቶ ተፈራ ሃይሉ በጉብኝት እና በንግድ ቪዛ ወደ ዩናይትድ ስቴይትስ በመጓዝ ልጅ የሚወልዱ ሰዎችን ማንነት “ባለሃብቶች ፣ የአየር መንገድ ሠራተኞችና የባለሥልጣን ቤተሰቦች” ሲል በሦስት ይከፍላቸዋል።
እነዚህ ሰዎች በተለይ ዲኤምቪ በሚባለውና ዋሽንግትን ዲሲ፣ቨርጅኒያ እና ሜሪላንድ በሚያካትተው አካባቢ ለመውለድ ከመጡ አሊያም እዚህ ከመጡ በተለየ ምክኒያት አገልግሎቱን ማግኘት ከፈለጉ አገልግሎቱን የሚያገኙት በተለያየ መንገድ እንደሆነ አቶ ተፈራ ይናገራል።
አንደኛ ክፍያውን ሙሉ ለሙሉ ይፈጽማሉ ወይም ኢንሹራንስ ይገዛሉ ይህንን የሚያደርጉትም በጣም ጥቂቶች እንደሆኑ ይነገራል። ሁለተኛው መንገድ በተለይ በዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ የሚኖርና ዝቅተኛ ገቢ ማግኘቱን በተጨማሪም እንደ ውሃና መብራት የመሳሰሉ ወርሃዊ ክፍያዎቹ ዝቅተኛ መሆኑን የሚያሳይ መረጃ በማቅረብ የነፃ ሕክምና ያወጣሉ።
ሦስተኛ የተቸገሩ ሰዎችን የሚረዱ ድርጅቶች እና ሆስፒታሎች ጋር በመሄድ ምንም ገቢ እና ሰው የሌላቸው መሆኑን አስረድተው አገልግሎቱን ያገኛሉ። አራተኛው መንገድ በድንገተኛ ወደ ሆስፒታሎቹ መግባትና አገልግሎቱን ማግኘት ነው።
በዋሽንግተን ዲሲ ኢትዮጵያ የኅብረተሰብ አገልግሎት የልማት ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ከአቶ ዳዊት ግዛው ጋር ሰፋ ያለ ውይይት አድርገን ነበር። በዚህ ጉዳይ ስማቸው ከተነሳው መካከል የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሠራተኞች ጭምር በመሆናቸው ከአየር መንገዱ ምላሽ ጥያቄ አቅርበን ነበር።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ