በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የባይደን እጩ ተሿሚዋ ሊንዳ ቶመስ ስለ አፍሪካ ምርጫ ተናገሩ


ፎቶ ፋይል፦ ሊንዳ ቶመስ ግሪንፊልድን
ፎቶ ፋይል፦ ሊንዳ ቶመስ ግሪንፊልድን

ተመራጩ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ጥቁር አሜሪካዊቷን ሊንዳ ቶመስ ግሪንፊልድን በተባበሩት መንግሥታት የዩናይትድ ስቴትስ አምባሰደር አድርገው ማጨታቸውን አስታውቀዋል፡፡ ከኖቬምበር 3ቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በፊት፣ የቪኦኤ ዘጋቢ ሻካ ስሳሊ ዩናይትድ ስቴትስ በአፍሪካ ስለምትከለው ፖሊሲ አነጋግራቸው ዘገባ አጠናቅራለች፡፡

ሊንዳ ቶመስ ግሪን ፊልድ፣ በዲፕሎማሲው፣ የ35 ዓመታት ልምድ አላቸው፡፡ በሲዊዘርላንድ፣ ፓኪስታን፣ ኬንያ፣ ጋምብያ፣ በናይጄሪያና ጃማያካ ተዘዋውረው ሰርተዋል፡፡ በላይቤሪያ፣ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሰደር የነበሩ ሲሆን፣ በዩናይትድ ስቴት ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደግሞ፣ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ጸሀፊ ሆነው አገልግለዋል፡፡ በአፍሪካ ጉዳይ ከሚያስደንቃቸው መካከል፣ የአፍሪካው መሪዎች፣ ሥልጣን ላይ መቆየት የሚፈልጉበት የጊዜ ገደብ መሆኑን፣ እንዲህ በማለት አበክረው ይናገራሉ፡፡

“በአንዳንድ አገሮች በህገመንግስታቸው የሥልጣን ጊዜ ገደብ አልተቀመጠም፡፡ ስለዚህ ዝምብሎ ከዓመት ወደ ዓመት፣ ለዓመታት ሥልጣን ላይ የሚቆይ ፕሬዚዳንት ይኖርሃል፡፡ እኔ ግን የምለው፣ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በተለይም በአፍሪካ፣ ስኬታማ ሆነናል የምለው፣ የሚካሄዱ ምርጫዎች በሙሉ፣ የጊዜ ገደብን እንደ አንድ መስፈርት አድርገው ሲያስቀምጡ ነው፡፡ ከዚያ ቀጥሎ ሊመጣ የሚገባው ነገር፣ ምርጫዎቹ ፍትሃዊና ግልጽ መሆናቸውን ማረጋገጥና በስልጣን ላይ ያሉት፣ ምርጫውን ላልተወሰነ ጊዜ ሥልጣን ለመቆየት የሚጠቀሙበት መሳሪያ እንዳይሆን ማድረጉ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ነገር በተለይ የሥልጣን ጊዜ ገደብ በሌላቸው አገራት የሚታይ ይመስለኛል፡፡”

ሊንዳ ቶመስ ፣ አፍሪካ ወደ ዘላቂ ልማት እየተሸጋገረች በመምጣቷ፣ በርካታ የዓለም ኃያላን አገራት፣ በአፍሪካ ያላቸው ተሳትፎ እየጨመረ መምጣቱን ሲያስረዱ የሚከተለውን ብለዋል

“ሁላችንም ያ ለውጥ ቀስ በቀስ እየተከስተ መሆኑን እያየን ነው፡፡ እኔ እንደሚመስለኝ በአህጉሪቱ እንዳለ በግልጽ ከሚታየው ሀብት ጋር የሰው ኃይልም ሀብት ያለ ይመስለኛል፡፡ አፍሪካ ባላት የህዝብ ብዛትም ሆነ ወጣት ታዳጊ አህጉር ናት፡፡ እነዚያ ወጣቶች በአህጉሪቱ ምን መካሄድና አፍሪካ ምን መሆን እንዳለባት ትርክቱን ሲቆጣጠሩትና ሲመሩት እያየን ነው፡፡ በርግጥ የዚያን የለውጥ ፍሬዎች ውጤት ገና አላየንም፡፡ ያን ለውጥ ማየት በምንጀምርበት ወቅት ግን አስደናቂ ነገር የምናይ ይመስለኛል፡፡ በአፍሪካ ትልቅ ተጽእኖ ይኖረዋል ብዬ አስባለሁ፡፡ አፍሪካ የመጨረሻው መዳረሻ ምዕራፍ ናት፡፡ ይህን ሁል ጊዜ ነው የምናገረው፡፡ በአፍሪካ አህጉር ያለው እድል በየትኛም የዓለም ክፍል የለም፡፡ ያንን በዓለም ዙሪያ እያየነው ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ አፍሪካውያንም ራሳቸው ከዚያ የመጨረሻው ምዕራፍ ተጠቃሚ የሚሆኑ ይመለኛል፡፡”

ቶመስ ግሪን ፊልድ፣ ለሪፐብሊካን እና ለዴሞክራት ፕሬዚዳንቶች የሠሩ ሲሆን፣ ሁለቱም አስተዳደሮች ለአፍሪካ በሚያደርጉት ትኩረት፣ የጋራ አድናቆት እንዳላቸው ይገልጻሉ፡፡

“እኔ ባለሙያ አገልጋይ ነኝ፡፡ በሁሉም የአስተዳደር ዓይነት ሠርቻለሁ፡፡ በሁለቱም አስተዳደሮች ፖሊሲዎች በሚወጡበት ጊዜ ሁለቱም ፖሊሲዎች ተፈጻሚ እንዲሆኑ በታማኝ የቢሮክራሲው ሙያተኝነቴ አከናውኛቸዋለሁ፡፡ እኔ እንደማስበው እያንዳንዱ አስተዳደር ስትራቴጂያዊ ይሁን ወይም የሞግዚትነት፣ አፍሪካን በሚመለከት ሁለቱም አስተዳደሮች አፍሪካን እንደ አጋርነት የተመለከቱ ሲሆን አፍሪካ ውስጥ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት የሞከሩትም በዚያው መንገድ ይመስለኛል፡፡”

ለ35 ዓመታት ያገለገሉት ነበሯ ዲፕሎማት፣ ሊንዳ ቶማስ ግሪን ፊልድ፣ በተባበሩት መንግሥታት፣ የዩናይትድ ስቴትት አምባሳደር ሆነው እንዲሰሩ፣ በባይደን እንደ ተመረጡ፣ በቲውተር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ፣ “እናቴ ዓለምን የተሻለች ለማድረግ፣ በደግነት እና በርህራሄ መምራት እንደሚገባ አስተምራኛለች፡፡ በውጭ አገር የአገልግሎት ዘመኔም ያንን ትምርህት ተግባራዊ ሳደርግ ኖሪያለሁ፡፡ አሁንም ሹመቴ ከጸደቀልኝ፣ በተባበሩት መንግሥታት አምባሰደርነቴ፣ ተመሳሳዩን አደጋለሁ” ብለዋል፡፡

ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምጽ ፋይል ያድምጡ፡፡

የባይደን እጩ ተሿሚዋ ሊንዳ ቶመስ ስለ አፍሪካ ምርጫ ተናገሩ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:18 0:00



XS
SM
MD
LG