በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአሜሪካው የመከላከያ ሚኒስትር በአፍሪካ ጉብኝት ላይ ናቸው


የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስቲን፣ ከሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሐሳን ሼክ ሞሐሙድ ጋራ ጅቡቲ እአአ መስከረም 9/25/2023
የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስቲን፣ ከሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሐሳን ሼክ ሞሐሙድ ጋራ ጅቡቲ እአአ መስከረም 9/25/2023

ጅቡቲን፣ ትላንት እሑድ የጎበኙት የአሜሪካው የመከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስቲን፣ ዛሬ ሰኞ ኬንያ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ኦስቲን፣ በኬንያ ካሉ የመከላከያ ባለሥልጣናት ጋራ በጸጥታ እና በፀረ ሽብር ጉዳዮች ላይ ይነጋገራሉ፤ ተብሏል።

ለሞኒዬ ተብሎ በሚጠራው በጅቡቲ የአሜሪካ ወታደራዊ ሰፈር፣ በትላንትናው ዕለት የተገኙት ሎይድ ኦስትን፣ ባለፈው ሚያዝያ የዲፕሎማቶችን ደኅንነት ጠብቆ ከሱዳን በማስወጣት ረገድ፣ የአሜሪካ ወታደሮች የተጫወቱትን ሚና አድንቀዋል።

ከጂቡቲ ፕሬዚዳንት እና ከሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር ጋራ የተነጋገሩት ኦስትን፣ አገሪቱ፣ በአፍሪካ የአሜሪካ ዋና ወታደራዊ ጣቢያን በማስተናገድ እና ሶማሊያ ከሽብርተኞች ጋራ የምታደርገውን ፍልሚያ በመደገፍ ያላትን አጋርነት ጠቅሰው አመስግነዋል።

ከሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሐሳን ሼክ ሞሐሙድ ጋራ ጅቡቲ ውስጥ የተገናኙት ሎይድ፣ የሶማሊያ ወታደሮች ከአል-ሻባብ ጋራ በሚደረገው ፍልሚያ እያሳዩ የሚገኙትን መሻሻል አድንቀዋል፤ ከአስተዳደራዊ ቁጥጥር ውጪ ያሉ አካባቢዎች፣ አሁንም የሽብርተኞች ምንጭ ሊኾኑ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ባለፈው ቅዳሜ በማዕከላዊ ሶማሊያ፣ በለደወይን፣ በተሽከርካሪ ላይ በተጠመደ ቦምብ በደረሰ ጥቃት፣ 21 ሰዎች ሲሞቱ፣ 52 ተጎድተዋል። መኪናውን አስመልክቶ መረጃ የደረሳቸው የጸጥታ አባላት፣ በፍተሻ ላይ እንዳሉ ፍንዳታው እንደተከሠተ ታውቋል።

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በደረሰ ጥቃት ደግሞ፣ አንድ የአሜሪካ ተቋራጭ እና አንድ አጋር ወታደራዊ አባል እንደተጎዱ፣ የአሜሪካ መከላከያ ባለሥልጣናት ለቪኦኤ ተናግረዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG