በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በርሃሌ መጠለያ ውስጥ አምስት ስደተኞች መገደላቸውን ተመድ አስታወቀ


ፋይል - በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ በሚገኝ አግዳ በተሰኘ ሆቴል ቅጥር ግቢ ውስጥ የዩ.ኤን ኤች. ሲ. አር ምልክት ያለበት ካርቶን ውስጥ ባለስሥልጣናት እስከሚመዘግቧቸው በመጠባበቅ ላይ ያሉ ሴቶች/ እንደ አውሮፓውያን የቀን አቆጣጠር የካቲት 14/2022. በሰመራ የሚገኘው የአግዳ ሆቴል በመቶዎች የሚቆጠሩ ሲቪሊያንን አስጠልሏል።
ፋይል - በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ በሚገኝ አግዳ በተሰኘ ሆቴል ቅጥር ግቢ ውስጥ የዩ.ኤን ኤች. ሲ. አር ምልክት ያለበት ካርቶን ውስጥ ባለስሥልጣናት እስከሚመዘግቧቸው በመጠባበቅ ላይ ያሉ ሴቶች/ እንደ አውሮፓውያን የቀን አቆጣጠር የካቲት 14/2022. በሰመራ የሚገኘው የአግዳ ሆቴል በመቶዎች የሚቆጠሩ ሲቪሊያንን አስጠልሏል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኛ ጉዳዮች ከፍተኛ ኮሚሽነር /ዩ.ኤን.ኤች.ሲ.አር/ አርብ የካቲት 11/2014 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አፋር ክልል በርሃሌ ውስጥ በሚገኘው የስደተኞች መጠለያ ካምፕ ውስጥ በደረሰ ጥቃት አምስት ሰዎች መገደላቸውና በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ደግሞ አካባቢውን ጥለው መሰደዳቸው ሪፖርት እንደደረሰው አስታውቋል።

የመንግሥታቱን ድርጅት የምስራቅና የአፍሪካ ቀንድ ቢሮ ቃል አቀባይ ፌዝ ካሲናን አፋር ክልል ከታኅሣር ወር ጀምሮ ጦርነት ውስጥ መቆየቱን ገልፀው በየካቲት ወር መጀመሪያ ላይ ደግሞ በርሃሌ ውስጥ በሚገኘው የኤርትራ ስደተኞች መጠለያ ካምፕ ውስጥ ጥቃት መድረሱን ተናግረዋል።

ፌዝ ሁኔታውን ሲያስረዱ፤ “እንደ አውሮፓውያን የቀን አቆጣጠር በየካቲት ወር መጀመሪያ የታጠቁ ሰዎች በርሃሌ ካምፕ ውስጥ በመግባት ጥቃት ማድረሳቸውንና በአካባቢው ያሉ ሰዎችም መጎዳታቸውን በተመለከተ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርት ደርሶታል። በወቅቱ ሰዎች ለነፍሳቸው ሲሉ መሸሽ ነበረባቸው። ስለዚህ እንደ አካባቢው ባለሥልጣን ከሆነ 34 ሺሕ ኤርትራዊያን ስደተኞች ለመሸሽ ተገደዋል። እነዚህ 34 ሺሕ የሚሆኑ ሰዎች በካምፑ ውስጥና በአካባቢው ባለው መጠለያ ውስጥ የሚኖሩ ናቸው።” ብለዋል ።

በርሃሌ በሚገኘው የስደተኞች መጠለያ ከደረሰ ጥቃት የተረፉ ሰዎችን ቃል ጠቅሶ መግለጫ ያወጣው የመንግሥታቱ ድርጅት፤ ጥር 26/2014 ዓም የታጠቁ ሰዎች ወደ ካምፑ ከገቡ በኋላ ቢያንስ አምስት ስደተኞች ሲገደሉ፣ በርካታ ሴቶችን ማገታቸውን አስታውቋል።

ካምፑን ጥለው በመሸሽ ላይ በነበሩበት ወቅት በተፈጠረ ትርምስ የቤተሰባቸው አባላት የጠፉባቸው መሆኑን ተፈናቃይ ስደተኞቹን ዋቢ ያደረገው መግለጫ ይዘረዝራል። ድርጀቱ ጥቃቱን ያደረሰቱን ታጣቂዎች ማንነት ይፋ ያላደረገ ሲሆን ቃል አቀባዩዋ ፌስ ካሲናን የታጣቂዎቹ ማንነት እንዳልታወቀ ተናግረዋል።

“በግጭቱ ምክኒያት የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ከፍተኛ ኮሚሽን ሠራተኞችና ሌሎች የሰብዓዊ ጉዳይ አጋሮቻችን አካባቢውን ለቀው ለመውጣት ተገደው ነበር።” ያሉት ፌዝ ካሲናን “ስለዚህ ለየት ያለ ጥቃት ፈፃሚዎች ማን እንደሆኑ ማረጋገጥ አልቻልንም። አሁን ኮሚሽኑ ቅድሚያ የሚሰጠው የስደተኞችና ማኅበረሰቦቻቸው ደህንነት እና በድጋሚ ለመፈናቀል መዳረጋቸው ነው። ደህንነታቸውን ማረጋገጥ እንሻለን። ስለዚህ ለስደተኞችና ለተመላሾች አገልግሎት ከሚሰጡና ሌሎች የጋራ አጋሮች ጋር በመሆን የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ ለሚሹ ሁሉ ተደራሽ ድጋፍ ለማድረግ እየሠራን ነው።” ብለዋል።

የበርሃሌ የስደተኞች መጠለያ አፋርን እና ትግራይን ከሚያዋስን ሥፍራ ይገኛል።

ህወሃት አብዛኛውን ትግራይን ቢቆጣጠርም “የመንግሥት ደጋፊ በሆኑ ኃይሎች ጥቃት ደርሶብኛል” ሲል እንደ አውሮፓውያን የቅን አቆጣጠር ካለፈው የጥር ወር አንስቶ በአፋር ወታደራዊ ዘመቻ መክፈቱን ተናግሯል።

ኤ.ኤፍ.ፒ በዚህ ሳምንት አፋር ዋና ከተማ ሰመራ ውስጥ ራሳቸውን አትርፈው ከዚያ የደረሱ ሰዎችን አግኝቶ ባደረገው ቃለ ምልልስ ጥቃቶቹን ያደረሰው ህወሃት መሆኑን መናገራቸውን ዘግቧል።

"እንዲህ ዓይነት ነገር አይቼ አላውቅም" ሲሉ የሁኔታውን አስከፊነት የገለጹት መሃሙዳ አህመድ የተባሉ ኤ.ኤፍ.ፒ ካነጋገራቸው ስደተኞች አንዱ ናቸው። “አንድም የመንግሥት ደጋፊ ታጣቂ በአካባቢው በሌለበት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈፀመ ጥቃት ነው” ሲሉ ስለነበረው ሁኔታ በማስታወስ አስረድተዋል።

"ወታደሮች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ተኩስ ሲከፍቱ አይቼ አላውቅም። የሚዋጋቸው ወታደርም አልነበረም። የነበሩት ሴቶች እና ህጻናትን ጨምሮ ሲቪሎች ብቻ ነበሩ። እናም ከባድ መሳሪያዎችን ይተኩሱ ነበር" ብለዋል።

ከሰባቱ ልጆቻቸው ሁለቱ የስድስት ዓመት ወንድ ልጃቸው እና የአራት ዓመቷ ሴት ልጃቸው፣ እንዲሁም ከሁለቱ ሚስቶቻቸው አንደኛቸው አሁንም ድረስ የገቡበት አልታወቀም።

በስደተኛ ካምፑ ውስጥ ከነበሩት የተመዘገቡ 34 ሺሕ ስደተኞች ውስጥ አራት ሺሕ የሚሆኑት ሰመራ የሚገኘው ዩ.ኤን. ኤች ሲ አርና የኢትዮጵያ መንግስት ስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ኤጀንሲ በጋራ በሚያስተዳድሩት ካምፕ ውስጥ እንደሚገኙ ኮሚሽነሩ ገልጿል። ቀሪዎች 10 ሺሕ ደግሞ ከሰመራ 225 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው አፍዴራ ከተማ ውስጥ እንደሚገኙ ማረጋገጡን አስፍሯል።

ቀሪዎቹ የት እንደሆኑ የተጠየቁት ፌዝ፤ “ባለሥልጣናቱ ስደተኞቹ ያሉበትን ቦታ ሊያረጋግጡ አልቻሉም። የምናውቀው ነገር ቢኖር 14 ሺሕ የሚሆኑ ስደተኞች በአካባቢው መኖራቸውን ነው። እነዚህ ናቸው አፋር ክልል ዋና ከተማ ሰመራ ድረስ ተጉዘው መድረስ የቻሉት። ሌሎቹ ደግሞ በቀሪ የክልሉ ከተሞች ውስጥ ናቸው ያሉት። ስለዚህ ላልተቆጠሩት ስደተኞች የረድኤት ተቋማት ድጋፍ ለማድረግና አስቸኳይ እርዳታ ለመለገስ ይፈልጓቸዋል” ብለዋል።

ቀደም ሲል በካምፑ ውስጥ የነበሩና አሁን ከጥቃቱ በኋላ የት እንዳሉ የማይታወቁ ያልተቆጠሩት ስደተኞች ወደ 20 ሺሕ እንደሚጠጉ ቃል አቀባዩዋ ጨምረው ተናግረዋል።

የአፋር ክልል መንግሥት ባለስልጣናት እና እንዲሁም የብሄራዊ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት ድርጅት በተመሳሳይ ለዚህ ሁሉ ተጠያቂው ህወህት ነው ብለዋል።

ካምፑ የሚደረስበት ባመሆኑ የተባለውን ማረጋገጥ ያለመቻሉን ጠቅሶ ኤ.ኤፍ.ፒ ዘግቧል። የህወሃት መሪዎችንም ለጊዜው ያለማግኘቱን አመልክቷል።

(ዘገባውን በድምፅ ለማድመጥ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ይጫኑ)

XS
SM
MD
LG