በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ትግራይ ውስጥ በመቶዎች ሲቪሎች ላይ ጭፍጨፋ ለመካሄዱ ማስረጃ  እንዳለው አምነስቲ አስታወቀ


ትግራይ ውስጥ በመቶዎች ሲቪሎች ላይ ጭፍጨፋ 
ለመካሄዱ ማስረጃ  እንዳለው አምነስቲ አስታወቀ
ትግራይ ውስጥ በመቶዎች ሲቪሎች ላይ ጭፍጨፋ  ለመካሄዱ ማስረጃ  እንዳለው አምነስቲ አስታወቀ

ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽ ዛሬ ባወጣው አዲስ ሪፖርት፤ በትግራይ ክልል ደቡብ ምዕራብ ዞን በምትገኘው ማይካድራ ከተማ ውስጥ በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ አስክሬኖች ማክሰኞ ዕለት መገኘታቸውን፣ ግድያውም ጥቅምት 30/2013 ዓ.ም ምሽት ላይ መፈፀሙን ማስረጃ እንዳለው አስታወቀ።

የድርጅቱ የምስራቅና የደቡብ አፍሪካ ዲሬክተር ዲፕሮስ ሙቼና፤ “በመካሄድ ላይ ካለው ጦርነት ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸውና የቀን ሠራተኛ የሚመስሉ ቁጥራቸው እጅግ የበዛ ሲቪሎች መጨፍጨፋቸውን አረጋግጠናል።” ካሉ በኋላ “ይህ ትግራይ ውስጥ ግኙነት በመቋረጡ ምክኒያት አሁን ልናውቀው ያልቻልነውን የዚህ ዘግናኝ አሳዛኝ ሁኔታ ትክክለኛ ስፋት ሊያሳየን የሚችለው 'ጊዜ' ብቻ ነው።” ብለዋል።

ድርጅቱ የቀውስ ጊዜ የማስረጃ ማረጋገጫ ቤተ ሙከራ፣ የዲጂታል ፎቶ ማረጋገጫ ዘዴን እና የሳተላይት ምስሎችን በመጠቀም ባደረገው ማጣራት በየቦታው ተጥለው እና በቃሬዛ ላይ ተቀምጠው የሚታዩት አሰቃቂ ቪዲዮዎች እና ፎቶግራፎችን በተጠቀሰው ቀን ማይካድራ ውስጥ የተነሱ መሆናቸውን ማረጋገጡን አስታውቋል።

የአምነስቲ የአፍሪካ ቀንድ የሰብዓዊ መብቶች ጉዳዮች አጥኚ አቶ ፍሰኃ ተክሌ ከእነዚህ ምስሎች በተጨማሪ ጉዳዩ የሚያስረዱ ምስክሮችን ማነጋገራቸውን ለአሜሪካ ድምፅ ገልፀዋል።

“በወቅቱ የሟቾቹን ሰዎች አስክሬን በመሰብሰብ እና የቆሰሉ ሰዎችን በመለየት ወደ ሆስፒታል በማመላለስ የተሳተፉ ሰዎችን አነጋግረናል።” ያሉት አቶ ፍሰኃ “ጭፍጨፋው የተፈፀመው በጦርነት ውስጥ ያልነበሩ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ነው” ብለዋል።

“በወቅቱ የሟቾቹን ሰዎች አስክሬን በመሰብሰብ እና የቆሰሉ ሰዎችን በመለየት ወደሆስፒታል በማመላለስ የተሳተፉ ሰዎችን አነጋግረናል።” ያሉት አቶ ፍሰኃ “ጭፍጨፋው የተፈፀመው በጦርነት ውስጥ ያልነበሩ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ነው” ብለዋል።

የአምነስቲው አቶ ፍሰኃ ለድርጅታቸው መረጃን የሰጡትን ምንጮች ጠቅሰው፤ ለሁመራ ቀረብ ባለችውና ትግራይ ውስጥ በምትገኘው ማይካድራ ተፈፅሟል ያሉትን ሲያስረዱ፤ “ማይካድራ ከመደረሱ በፊት በሚገኙ ሉግዲ እና ባናት በተሰኙ ቦታዎች ሰኞ ጥቅምት 30/2013 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ የትግራይ ክልል ልዩ ኃይልና በአካባቢ የሚገኙ ሚሊሺዎች ከፌደራል መንግሥት መከላከያ ሠራዊት ጋር ውጊያ እያካሄዱ ነበር። በዚህ ውጊያ ላይ የፌደራል መንግሥት ኃይሎች በመበርታታቸው የትግራይ መንግሥት ልዩ ኃይል እና የአካባቢ ሚሊሺያዎች እንደሸሹ መረጃው ስለነበር ለሊቱን ከተማው ተከቦ ማደሩን ምስክሮቻችን ገልፀውልናል” ይላሉ።

በማግሥቱ ኅዳር 1/2013 ዓ.ም የመከላከያ ሠራዊቱ አባላት ማይካድራ ከተማ ሲገቡ በዘግናኝ ሁኔታ የተገደሉ ሰዎች አብዛኛው አስክሬን መሃል ከተማ በሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አቅራቢያ እና ከማይካድራ ወደ ሁመራ በሚወስደው መንገድ ላይ መገኘቱን ምስክሮቹን ጠቅሶ የዘረዘረው የድርጅቱ መግለጫ ከጥቃቱ የተረፉ ተጎጂዎች መገኘታቸውን አስታውቋል።

ከመከላከያ ሠራዊት አባላት ጋር በመሆን በአስክሬን መሰብሰብ እና የቆሰሉትን ወደ ሆስፒታል በማጓጓዝ ሥራ ላይ የተሰማሩ ምስክሮች ለአምነስቲ እንዳስረዱት ከሆነ፤ አስክሬኖቹን ከመንገድ ላይ መሰብሰብ ከመጀመራቸው በፊት የቆሰሉት ሰዎች ለከተማዋ ቅርብ ወደ ሆኑት አብርሃ- ጅራ እና ጎንደር ሆስፒታል እንዲወሰዱ አድርገዋል።

አምነስቲ ለዚህ ጭፍጨፋ በቀጥታ ኃላፊነቱን ማን እንደሚወስድ ማረጋገጥ እንዳልቻለ ገልፆ ነገር ግን ከምስክሮቹ እንዳገኘው መረጃ ከሆነ "የድርጊቱ ፈፃሚዎች የህወሓት ታማኝ ኃይሎች መሆናቸውን" ጠቅሷል።

ከጭፍጨፋው የተረፉ ሰዎች የነገሯቸውን ጠቅሰው ሦስት ሰዎች ለአምነስቲ እንደተናገሩት፤ ጥቃቱን ያደረሱባቸው የትግራይ ልዩ ኃይል እና የህወሓት አባላት መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የአሜሪካ ድምፅ ያነጋገራቸው የትግራይ ክልል የኮሙኒኬሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሐዱሽ ካሱ ደግሞ፤ “በትግራይ ሕዝብ ላይ የተጀመረው ከባድ የዘር ማጥፋት ወረራን ለመቀጠል ኾን ተብሎ የተሰራጨ የሐሰት ዜና ነው። የትግራይ ክልል ልዩ ኃይል ብሔርን መሠረት ያደረገ ጥቃት የመፈፀም ባህል የለውም። ይህ የእነሱ ባህል ነው ብለዋል። ጡረተኛ ጄነራሎችን ጭምር ‘ትግርኛ ተናጋሪ’ በማለት በሕዝብ ላይ የዘር ማጥፋት ዐዋጅ ተናግረዋል” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

አያይዘውም “በትግራይ ውስጥ በርካታ የሌላ ብሔር ተወላጆች አሉ። በሰላምም እየኖሩ ይገኛሉ” ካሉ በኋላ “ይህ መረጃ ግን በሌላ አካባቢ የሚገኘውን የትግራይ ተወላጅ ለመጨፍጨፍና በትግራይ ላይ ለተከፈተው ወረራ ሕዝብ ለማነሳሳት ነው። ሆኖም ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ አልተቀበላቸውም” ብለዋል።

በሌላ በኩል በሁመራ አቅራቢያ በምትገኘው ማይካድራ ከተማ በአማራ ተወላጆች ላይ አሰቃቂ የዘር ማጥፋት ወንጀል የፈፀመው የሕወሓት ቡድን እንደሆነ የአማራ ክልል ገዢ ፓርቲ አስታውቋል። የአማራ ብልፅግና ፓርቲ ባወጣው መግለጫ እንዳለው፤ህወሓት ግድያውን የፈፀመው በሕዝቦች መካከል የእርስ በርስ ጦርነት (Civil War) እንዲቀሰቀስ ለማድረግ ብሏል።

አዲሱ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር ደግሞ፤ “ድርጊቱ በዓለም አቀፍ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት (ICC) የሚያስጠይቅ ወንጀል መሆኑን እናምናለን” ብለዋል።

የአምነስቲው አቶ ፍሰኃ ከተማው ላይ የስልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎት በመቋረጡ ምክኒያት ተጨማሪ ማጣራት የሚያስፈልጋቸው መረጃዎች አለመገኘታቸውን ገልፀው፤“ነገር ግን እነዚህ ሰዎች ሞተው በተገኙበት አካባቢ ላይ የፌደራል መከላከያ ሠራዊት እስከሚገባ ድረስ ማይካድራ ከተማ ለትግራይ ክልል መንግሥት ወይም በሕወሓት በሚታዘዙ የትግራይ ክልል ልዩ ኃይል እና በአካባቢው ሚሊሺያ ሥር እንደነበር ይታወቃል።” ብለዋል።

አያይዘውም፤ “የእነዚህ ሰዎች አስክሬን በመከላከያ የተገኘበት እና የተገደሉበትን ቀን ስናስተያየው የትግራይ ክልል ሠራዊት ባለበት እንደተፈፀመ ያሳያል። የስልክ ግንኙነት ስለተቋረጠ የከተማዋን ነዋሪዎች ለማነጋገር እክል ስልገጠመን እና በጠራ ሁኔታ ለማረጋገጥ ስላልቻልን እንጂ ድርጊቱ በትግራይ ክልል ልዩ ኃይል መፈፀሙን የሚጠቁሙ መረጃዎች አሉ” ብለዋል።

የአምነስቲ የምስራቅና የደቡብ አፍሪካ ዲሬክተር ዲፕሮስ ሙቼና፤ “ የኢትይጵያ መንግሥት ይህንን በሰላማዊ ዜጎች ላይ የተፈፀመን ጥቃት፤ በግልፅ፣ በገለልተኝነት፣ በብቃት እና በፍጥነት ምርመራ እንዲካሄድበት በማድረግ ፈፃሚዎቹ በአስቸኳይ ለፍርድ እንዲቀርቡ ማድረግ አለበት” ብለዋል።

አያይዘው ባሰፈሩት መልዕክት፤ “የህወሓት አዛዦች እና ኃላፊዎች በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች በዓለም አቀፍ የጦር ሕግ መሠረት በፍፁም የተከለከሉ እና የሚያስቀጡ የወጀል ድርጊት መሆናቸውን ለፀጥታ ኃይላቸውና ለደጋፊዎቻቸው ግልፅ ማድረግ አለባቸው” ብለዋል።

ትግራይ ክልል ባለው ግጭት ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም አካላት፤ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕግ እና የሰብዓዊ መብቶች ሕግን ማክበር እንደሚገባቸው ድርጅቱ አሳስቧል። ከምንም ነገር በላይ የሲቪሎች ደህንነት መጠበቁ መረጋገጥ አለበትም ብሏል።

XS
SM
MD
LG