በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በህወሃት ምክንያት እሥር ቤት ያለ የለም - የአማራ ክልል ፍትኅ ቢሮ


በህወሃት ምክንያት እሥር ቤት ያለ የለም - የአማራ ክልል ፍትኅ ቢሮ
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:40 0:00

በህወሃት ምክንያት እሥር ቤት ያለ የለም - የአማራ ክልል ፍትኅ ቢሮ

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት ከህወሃት ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ተጠርጥረው ተይዘው ከነበሩ ሰዎች “አንዳቸውም እሥር ቤት አይደሉም” ሲል የአማራ ክልል ፍትህ ቢሮ አስታውቋል።

“ከመቶ በላይ የትግራይ ተወላጆች ለሦስት ዓመታት ታስረው ይገኛሉ” በሚል ከአንድ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ቡድን የተሰማው መረጃ "የተሳሳተ ነው" ሲሉ የክልሉ ፍትኅ ቢሮ የሥራ ኃላፊ ለቪኦኤ ተናግረዋል።

ከፌደራሉ መንግሥት ጥያቄ ከቀረበ ክሣቸው ሊቋረጥ እንደሚችል ኃላፊው ጠቁመዋል።

የአማራ ክልል ዛሬ የሰጠው ምላሽ መነሻ “ህዩመን ራይትስ ፈርስት” የሚባል የመብቶች ተሟጋች ቡድን “በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት ከህወሃት ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ተጠርጥረው የታሠሩ ከአንድ መቶ በላይ የትግራይ ተወላጆች ከፕሪቶሪያው የሠላም ስምምነት በኋላም እንደታሠሩ ናቸው” ሲል የሰጠው መግለጫ ነበር።

የአማራ ክልል ፍትህ ቢሮ የወንጀል ዘርፍ ምክትል ኃላፊ ዶ/ር አያሌው አባተ ቢሻው ዛሬ ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት ማብራሪያ “ከመቶ በላይ” የተባለው ትክክል እንዳልሆነ ተናግረዋል።

ከተፈረመ ዓመት ያለፈው የፕሪቶሪያው ስምምነት ፌደራል መንግሥቱ ህወሃትን ከሽብር መዝገብ እንደሚፍቅ እንደሚጠቅስ ህዩመን ራይትስ ፈርስት አስታውሶ ከድርጅቱ ጋራ ግንኙነት ነበራቸው የተባሉ እሥረኛችም መፈታት እንደነበረባቸው ስለማመልከቱም ዶ/ር አያሌው መልስ ሰጥተዋል።

ከህወሃት ጋራ ባልተገናኘ ጉዳይ በሌሎች ወንጀሎች የተጠረጠሩ ካሉ ግን ተጠያቂነቱ ይቀጥላል ብለዋል ዶር. አያሌው።

ከሃያዎቹ ተከሳሾች አሥራ ሁለቱ በአካል ስላልቀረቡ መዝገባቸው መዘጋቱንና በእርሣቸው አባባል “ሁኔታዎች ሲፈቅዱ” እንደገና ሊከፈት እንደሚችል ገልፀዋል።

“ስምንቱ ተከሳሾች ደግሞ በዋስ ወጥተው ጉዳያቸውን በውጭ እየተከታተሉ ናቸው፤ እሥር ቤት ውስጥ የሚገኙ ሰዎች የሉንም” ብለዋል ዶ/ር አያሌው።

የተሟጋቹ ድርጅት ምክትል ዳይሬክተር አቶ መብርሂ ብርሀነ “ክልሉ ውስጥ ታሥረዋል” የሚሏቸው “ሦስት ዓይነት” መሆናቸውን ከዚህ ቀደም ገልፀውልን ነበር።

በእነ ፋሲል ታምራት የሚጠራ የክሥ መዝገብ "በክልሉ ፍርድ ቤቶች ከሚገኙት ስድስት ዶሴዎች አንዱ ነው" የሚለው ህዩመን ራይትስ ፈርስት "በሌሎች አምስት ዶሴዎች ደግሞ በርከት ያሉ ተከሳሾች ይገኛሉ" ብሏል።

ስድሣ የሚሆኑ ሌሎች የትግራይ ተወላጆች “ያለ ክስ” ታስረው ከቆዩ በኋላ ካለፈው ዓመት ጥቅምት ወዲህ “ደብዛቸው ጠፍቷል” ሲል ድርጅቱ ከስሷል።

የፍትኅ ቢሮው ዶ/ር አያሌው አባተ ቢሻው "የተደራጀ አቤቱታ ይቅረብልን" ብለዋል።

ስለ ጉዳዩ ከፍትኅ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ በስልክ በአጭር የፅሑፍ መልዕክት ምላሽና አስተያየት ለማግኘት ቪኦኤ ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG