የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ አውጥቷል።
የክልሉ መንግሥት በዚሁ መግለጫው "በሠሞኑ በክልላችን የተፈጠረው የሽብር ተግባር ጀርባ ሲገለጥ የሚገኘው ሃቅ በሠላም ወዳዱ የአማራና የቅማንት ማህበረሠብ ላይ የተለየ ግጭት ኖሮ ሳይሆን ህዝባችንን እንደመዥገር ተጣብቀው ሲመጡት የኖሩና የሁከት ነጋዴ የሆኑ የጥፋት ሀይሎች በተቀናጀ መልኩ “ኢትዮጵያን ለማፍረስ አማራውን በልዩ ልዩ መልኩ ማዳከም” በሚል በሚከተሉት ያሮጌ ዘመን ቆሞ ቀሮች እቅድ መሆኑ በግልጽ ሁሉም ሊያውቀው ይገባል፡፡ ይህ እቅድ የጦር መሣሪያ በማስታጠቅ፣ በፋይናንስና ሆን ተብለው ለጥፋት በተከፈቱ ሚዲያዎቻቸው አማካኝነት በተቀናጀ ዘመቻ ታስቦበት የተሠራና የአማራን ህዝብ አንድ እንዳይሆን ለማድረግ ንጹሀንን በመግደል፣ በአማራና በቅማንት ህዝቦች መካከል ተጀምሮ በመላው ህዝባችን ዘንድ የሚቀጣጠል እሣት በመለኮስ፣ የአማራ ህዝብና መንግስትን ሥም በማጠልሸት የከሸፈውን የሀሰት ትርክታቸውን ለመመለስ እና አማራ ውስጣዊ አንድነት እንዳይኖረው በአጠቃላይ የአማራ ክልል ህዝብ በአንድነት እንዳይቆም ጽንፈኛ ሚዲያዎችንና የተለያዩ የቁማርተኞች መሣሪያ የሆኑ በአማራ ስም የተከፈቱ ማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም ጭምር እርስ በርስ እንድንባላ ጥረዋል፤ ሌት ተቀን እየባዘኑም ይገኛሉ" ብሏል።
በሌላ በኩል ባለፉት ቀናት በጎንደር ከተማና በአካባቢዋ ተከስቶ በነበረው የሰላም መደፍረስ የፀጥታው ሁኔታ ወደነበረበት መመለሱን የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር አበረ አዳሙና ዕማኝ ነን ያሉ ለአሜሪካ ድምፅ ገልፀዋል።
የአሜሪካ ኤምባሲ ዛሬ ለዜጎቹ ባወጣው የደህንነት ማሳሰቢያ በጎንደር ከተማና በዙሪያዋ የተኩስ ድምፅ ይሰማ እንደነበረ፣ መንገድ መዘጋቱን፣ ንብረት መውደሙን የሚያመለክቱ ሪፖርቶች እንዳሉ ጠቁሟል።
የአማራ ክልል ባለሥልጣናት ለአሜሪካ ድምፅ በሰጧቸው አስተያየቶች ሰሞኑንና ከዚያም በፊት በተከሰቱ ግጭቶች "የህወሃት እጅ አለበት" ሲሉ ይከስሳሉ።
ለአማራ ክልል ባለሥልጣናት ክሥ ምላሽ የሰጡት የህወሓት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል አቶ ጌታቸው ረዳ ፓርቲያቸው የተባለውን "እንዳልፈፀመ ፖሊስ ኮሚሽነሩ ጭምር ያውቃሉ" ብለዋል።
"የአማራ ክልል የፀጥታ አካላት በህፃናትና በሴቶች ላይ ጥቃት ለማድረስ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ከተጠቂዎች መልስ ሲሰጣቸው ሁሌም የሚናገሩት ነው" በማለት አክለዋል።
"የቅማንት ህዝብ ሕጋዊ ጥያቄ እንደግፋለን" ብለዋል አቶ ጌታቸው።
ለሙሉው ዘገባ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ