በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በሶማሊ ክልል አቁስሎ ያሰራቸውን ስዊድናዊ ጋዜጠኞች እንዲፈታ የኢትዮጵያ መንግስት ተጠየቀ


የፎቶ ጋዜጠኛው ጆና ፐርሽን በኦጋዴን
የፎቶ ጋዜጠኛው ጆና ፐርሽን በኦጋዴን

በኢትዮጵያ የሶማሊ ክልል በአካባቢው በሚንቀሳቀስ አማጺ ቡድን አጃቢነት ድንበር አቋርጠው ወደ ኢትዮጵያ የገቡት ሁለት ስዊድናዊ ጋዜጠኞች እንዲለቀቁ ድርጅታቸውና የጋዜጠኞች ተሟጋች ቡድኖች ጠየቁ።

ከሓሙስ ጀምሮ በኢትዮጵያ መንግስት ቁጥጥር ስር የሚገኙት ጋዜጠኞች ህጋዊ ተጠያቂነትና የጤና ሁኔታቸው እንዳሳሰባቸው ባልደረቦቻቸው አስታውቀዋል።

በሰሜናዊቷ የሶማሊያ ራስ ገዝ ፑንትላንድ በኩል ድንበር ተሻግረው ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ያቀኑት ስዊድናዊ ጋዜጠኞች ከኦጋዴን ብሄራዊ ነጻአውጭ ግንባር ታጣቂዎች አጃቢነት ባለፈው ሀሙስ ድንበር ሲሻገሩ የኢትዮጵያ የጸጥታ ሃይሎች ተኩስ ከፍተው 15 አማጺያኑን ገድለው ስድስቱን ሲማርኩ፤ ጋዜጠኞቹም ቆስለው የተያዙት ያኔ ነው።

ሁለቱ ስዊድናዊያን የፎቶ ጋዜጠኛው ዮሃን ፐርሽን እና ዘጋቢው ማርትን ሼበ የሚሰሩበት ኮንትነንት የፎቶ ጆርናሊስት ኤጀንሲ ኤዲተር ተርየ ሊንድብሉም ለቪኦኤ እንዲህ ብሏል።

“የስራ ባልደረቦቼን ዮሃን ፐርሽንና ማርትን ሸበን የኢትዮጵያ መንግስት እንዲለቅ እጠይቃለሁ። እነዚህ ሰዎች ጋዜጠኞች እንጂ መንግስቱ እንደሚለው አሸባሪዎች አይደሉም፤ እንደዚህ አይነት አመለካከት ካላቸው ሰዎች ጋር አይሰሩም” ብሏል ሊንድብሉም።

ማርቲን ሼበ
ማርቲን ሼበ

የ29 ዓመቱ ዮሃን ፐርሽንና የ30 ዓመቱ ማትን ሼበ በሰሜን ሶማሊያዋ ራስ ገዝ በፑንትላንድ በኩል በኢትዮጵያ ሶማሊ ክልል የሚንቀሳቀሰው የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻአውጭ ግንባር (ኦብነግ) ታጣቂዎች ጋር ያመሩበትን ምክንያት የስራ ባልደረባቸው ተርየ ሊንድብሉም ሲገልጽ

“ዮሃን ፐርሽንና ማርትን ሼበ በኢትዮጵያ የኦጋዴን ግዛት ስደተኞች የሚደርስባቸውን የመብት ረገጣ አስመልክቶ፤ የተጣራ መረጃ ደርሷቸው ነው ወደዚያ ያመሩት።”

እነዚህ የመብት ጥሰቶች በሂውማን ራይት ወች መረጋገጣቸውን የገለጸው ተርየ ሊንድብሉም፤ ከሶስት አመት በፊት በወጣ ሪፖርት በሶማሊ ክልል የሚደርሱ የመብት ጥሰቶችን፣ የጦር ወንጀልና በሰው ዘር ላይ የሚፈጸሙ ግፎች ያላቸውን ሂውማን ራይትስ ወች ዘርዝሯል። የተቃጠሉ መንደሮችን፣ የተደፈኑ የውሃ ጉድጓዶችን ሁሉ የሳተላይት ምስልን አስደግፎ መረጃውን አቅርቧል ይላል።

በዚሁ ተመሳሳይ ዓመት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ መንግስት ወደ ኦጋዴን የሚላከውን እርዳታ ማገዱን አስታውቆ ነበር።

እነዚህ ጋዜጠኞች ታዲያ ይሄንን ሁኔታ ማጣራት ፈለጉ። እውነት ከሆነ ከራሳቸው ከስደተኞቹ ለመስማት በሶማሊያ በኩል ተሻግረው ወደ ኢትዮጵያ ኦጋዴን አቀኑ።

በኒው ዮርክ መሰረቱን ያደረገው የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት CPJ የጋዜጠኞቹ መያዝ በእጅጉ አሳስቦታል።

“በኦጋዴን አካባቢ የታሰሩት ሁለት የስዊድን ጋዜጠኞች ጤንነት፣ የት እንደሚገኙና የታሰሩበት የህግ አግባብ በእጅጉ አሳስቦናል፣ እረፍት ነስቶናል” ሲል የሲ. ፒ. ጄ የአፍሪካ መረጃ አጠናቃሪ ሞሃመድ ኬታ ለቪኦኤ ተናግሯል።

“የኢትዮጵያ ሃይሎችና አማዚያኑ ሲታኮሱ ጋዜጠኞቹ መቁሰላቸውን ሰንሰማም በእጅጉ ተጨንቀናል። አሁን ባሉበት ሁኔታ የሚደረግላቸው የህክምና ክትትል አናሳ መሆኑ በእጅጉ አሳስቦናል።”

ጋዜጠኞቹ ዮሃን ፐርሽንና ማርትን ሼበ ሀሙስለት ከቆሰሉ በኋላ በጂጂጋ የህክምና እርዳታ እንደተደረገላቸውና በዚያ የስዊድን አምባሳደር እንደጎበኟቸው የስራ ባልደረቦቻቸው ለዝግጅት ክፍላችን ተናግረዋል።

ሆኖም ጋዜጠኞቹ ወደ አዲስ አበባ መጥተው ክስ ይመሰረትባቸዋል ተብሎ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የተሰጠው አስተያየት እንዳሳሰባቸው የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅቶቹ ሲፒጄና በፓሪስ መሰረቱን ያደረገው ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን RSF ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን በጸረሽብር ህጓ ማሰርና ማዋከቧ አሳስቦኛል ያሉት ድርጅቶቹ፤ የኢትዮጵያ መንግስት ሁለቱን ስዊድናዊ ጋዜጠኞች በአስቸኳይ እንዲፈታ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ጋዜጠኞችንና ተቃዋሚዎችን “አሸባሪዎች” በሚል እንዲያስር የሚያደርገው ህግ ለመብት ረገጣና ለአፈና የተመቼ ነው ሲሉ ጉዳዩ በብርቱው እንዳሳሰባቸውም ገልጸዋል።

XS
SM
MD
LG