በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሁለት ስዊድናዊ ጋዜጠኞች በኦጋዴን በኢትዮጵያ የጸጥታ ሃይሎች ቆስለው ታሰሩ


ሰኔ 23 ቀን ኢትዮጵያን በሚያዋስነው የፑንትላንድ ድንበር በጋልቃዮ በኩል ሁለቱ ስዊድናዊ ጋዜጠኞች ከከኦጋዴን ብሄራዊ ነጻአውጭ ግንባር (ኦብነግ) ታጣቂዎችና ሌሎች አጋዦቻቸው ጋር ሲጓዙ ነበር የኢትዮጵያ የጸጥታ ሃይሎች በደረሳቸው መረጃ መሰረት ተከታትለው ያገኟቸው።

ወዲያውኑ ተኩስ ተከፈተ። የኢትዮጵያ መንግስት ቃል አቀባይ አቶ በረከት ስምዖን የሆነውን ለVOA እንዲህ ያስረዳሉ።

“ተኩስ ነበር። በዚህ የተኩስ ልውውጥ 15 የአሸባሪ ድርጅቱ ታጣቂዎች ወዲያውኑ ተገድለዋል። ስድስቱ ተማርከዋል። ከዚህ በተጨማሪም ሁለት የውጭ አገር ዜጎች ተይዘዋል” ብለዋል አቶ በረከት ስምዖን።

አቶ በረከት “ሁለቱ የውጭ አገር ዜጎች” ያሏቸው ዮሃን ፐርሰን እና ማርትን ሽቢየ የተባሉ የስዊድን ዜጎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

በፑንትላንድ በኩል ጋዜጠኞቹን ለማሳለፍ አጃቢዎችና መሪዎች መላኩን ያስታወቀው በኢትዮጵያ ሶማሊ ክልል የሚንቀሳቀሰው የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻአውጭ ግንባር (ኦብነግ) ከጋዜጠኞቹ ጋር ከሰኔ 24 ቀን ወዲህ ግንኙነቱ መቋረጡንና፤ የኢትዮጵያ ሃይሎች የጋዜጠኞቹን ረዳቶች ገድሎ፤ ስዊድናዊ ጋዜጠኞቹን አስሯል ሲል በዛሬውለት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

በሶማሊ ክልል የሚንቀሳቀሱት የኦብነግ አማጺያን አራሷን የቻለች ነጻ አገር መመስረት ይፈልጋሉ
በሶማሊ ክልል የሚንቀሳቀሱት የኦብነግ አማጺያን አራሷን የቻለች ነጻ አገር መመስረት ይፈልጋሉ

አቶ በረከት ስምዖን የኢትዮጵያ የጸጥታ ሃይሎች ሁለቱን ጋዜጠኞችና ሌሎች 21 ሰዎች ከማግኘታቸው በፊት በጋልቃዮ በኩል ወደ ኦጋዴን ለመግባት ሲሞክሩ በጀሌዎና በሊወርድ የአካባቢው ፖሊስና የጸጥታ ሃይሎች ድርሰው ተኩስ እንደከፈቱባቸው ነው የተናገሩት። በዚህ የተኩስ ልውውጥ መካከል ሁለቱም ጋዜጠኞች ቆስለዋል።

“በተኩስ ልውውጡ አንዱ….በእርግጥ ሁለቱም በመጠኑ ቆስለዋል። አንዱ ትንሽ ጠለቅ ያለ ቁስል አለው፤ ግን ለሞት የሚያበቃው አይደለም” ብለዋል አቶ በረከት።

በዛሬውለት መግለጫ ያወጣው ኦብነግ በኢትዮጵያ አሸባሪ ድርጅት ተብሎ የተፈረጀ ነው። ድርጅቱ እንደሚለው ሁለቱ ጋዜጠኞች “ኮንቲነንት ፎቶጆርናሊስት ኤጀነሲ” ለተባለ የፎቶ አንሽ ጋዜጠኞች ድርጅት የሚሰሩ ናቸው።

በፑንትላንድ በኩል ጋዜጠኞቹ ወደ ኢትዮጵያ የገቡት፤ የኢትዮጵያ መንግስት ጋዜጠኞች ወደ ኦጋዴን ሄደው እንዳይዘግቡ በመከልከሉ እንደሆነ ኦብነግ አስታውቋል። ይሄም የሚደረገው የኢትዮጵያ ወታደሮች በኦጋዴን የሚፈጸሙትን የሰብዓዊ መብት ረገጣና ግድያ ለማድበስበስ እንደሆነ ኦብነግ በመግለጫው አስታውቋል።

አቶ በረከት ስምዖን መንግስታቸው ለውጭ አገር ጋዜጠኞች የሚሰጠው የዘገባ ፈቃድ እንዲህ ያለ መንግስታቸው እንደሚያምነው “የልዖላዊ ድንበርን የመሻገር ወንጀል አያካትትም” ብለው ጋዜጠኞቹ ክስ እንደሚመሰረትባቸው ገልጸዋል።

“እነዚህ ሰዎች ህጋዊ ፓስፖርት የላቸውም። ከዚያ በተጨመሪ ከአሸባሪ ድርጅት ጋር ሲሰሩ ተይዘዋል። ስለዚህ ህጉ በሚደነግገው መሰረት፤ ህገ-ወጥ ናቸው ስለዚህ እንደ ህገወጥ እናያቸዋለን” ብለዋል አቶ በረከት ስምዖን።

አቶ በረከት አክለውም ከሁለቱ ጋዜጠኞች መካከል ዮሃን ፐርሶን ከዚህ በፊት በኦጋዴን መያዙን ተናግረዋል።

“ሚስተር ጆን በድንበሩ በኩል ተሾልኮ ሲገባ ይሄ ሶስተኛ ጊዜው ነው። ይሄን አምኗል። በ2000ዓም በአካባቢው ፖሊስ ተይዞ ነበር። ለአካባቢው ፖሊስ የነገረውን ከግምት በማስገባት ወዲያውኑ ተለቋል። ከዚያም በኋላ ስለ ኦብነግና የኢትዮጵያ መንግስት የተሳሳተ መረጃ ሲያሰራጭ ቆይቷል። አሁንም ለሶስተኛ ጊዜ ከአማጺያኑ፤ ከአሻባሪዎች ጋር ድንበር ሲሻገር ተይዟል”

የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻ አውጭ ግንባር ለኢትዮጵያ መንግስት መረጃውና አቀብሏል ያለው የፑንትላንድ አስተዳድርና የኢትዮጵያ መንግስት ላይ የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ድርጊቱን በማውገዝ መተባበር አለበት ብሏል። የኢትዮጵያ መንግስትም ታጋቾቹን እንዲለቅ ጫና ማድረግ ያስፈልጋል ብሏል ኦብነግ።

ኢትዮጵያ በቅርቡ ባወጣችው የጸረ-ሽብር ህግ፤ መንግስቱ አሸባሪ ብሎ ከፈረጃቸው ነፍጥ ካነሱ አንጃዎችና ከተወሰኑ ተቃዋሚዎች ጋር ጋዜጠኞች እንዳይሰሩ ይከለክላል።

ባለፈው ሳምንት የአውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ምክትል ዋና አዘጋጅ ውብሸት ታዬና የፍትሕና አዲስ ፕሬስ ጋዜጦች፣ የፖለቲካ አምደኛ ወይዘሪት ርዕዮት ዓለሙ ታስረው ለፍርድ ቀርበዋል።

በኒውዮርክ መሰረቱን ያደረገው የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት ሲ.ፒጄና የመብት ተሟጋች ቡድኑ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፤ የኢትዮጵያ መንግስት ጋዜጠኞችንና ተቃዋሚዎችን “አሸባሪዎች” በሚል እንዲያስር የሚያደርገው ህግ ለመብት ረገጣና ለአፈና የተመቼ ነው ሲሉ ጉዳዩ በብርቱው እንዳሳሰባቸው አስታውቀዋል።

ሲ.ፒ.ጄ በጸረ-ሽብር ህግ ጋዜጠኞችን አሸባሪዎችን አነጋግራችኋል አብራችሁ ሰርታችኋል በማለት ማዋከብና ማሰር በኢትዮጵያ እንዲቆም ጠይቋል።

XS
SM
MD
LG