በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኢራን ውስጥ ለአመታት ታስረው የቆዩ አሜሪካውያን ተለቀቁ


በዩናይትድ ስቴትስ እና ኢራን መካከል በተደረገው የእስረኞች ልውውጥ ስምምነት ከእስር የተፈቱ አሜሪካዊ ኢማድ ሻርጊን ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሲገናኙ ፎርት ቤልቮር ቨርጂኒያ፣ እአአ መስከረም 19/2023
በዩናይትድ ስቴትስ እና ኢራን መካከል በተደረገው የእስረኞች ልውውጥ ስምምነት ከእስር የተፈቱ አሜሪካዊ ኢማድ ሻርጊን ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሲገናኙ ፎርት ቤልቮር ቨርጂኒያ፣ እአአ መስከረም 19/2023

ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በተፈጸመ ወንጀል የተከሰሱ እና አንዳንዶቹም የተፈረደባቸው አምስት ኢራናውያንን በልዋጩ ለመልቀቅ በተደረሰ ስምምነት፣ ኢራን ውስጥ ለአመታት እስር ላይ የነበሩ አሜሪካውያን ተለቀቁ።

ሲማክ ናማዚ፣ ኢማድ ሻርጊ እና ሞራድ ታህባዝ ከሌሎች በቤተሰቦቻቸው ጥያቄ ማንነታቸው ይፋ ካልተደረገ ሁለት አሜሪካውያን ጋር፣ ኳታር ዶሃ ላይ በትላንትናው ዕለት አጭር ቆይታ ካደረጉ በኋላ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ አቅንተዋል። ኢራን ውስጥ የጉዞ እገዳ ተጥሎባቸው የነበሩት የናማዚ እናት እና የታህባዝ ባለቤትም ከእስረኞቹ ጋር አብረው ከአገር እንዲወጡ ተፈቅዶላቸዋል።

ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ታስረው ከነበሩት እና በስምምነቱ መሠረት ከተለቀቁት ኢራናውያን መካከል ሁለቱ ቴህራን ከመድረሳቸው አስቀድሞ በተመሳሳይ በዶሃ በኩል ማለፋቸውን መንግስታዊው የቴህራን ዜና ወኪል ዘግቧል። እንደ ኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተጨማሪ መግለጫ ሌሎች ሁለት ኢራናውያን በዩናይትድ ስቴትስ የሚቆዩ ሲሆን የተቀሩት ደግሞ ወደ ሌላ ሀገር እንዲጓዙ ተደርጓል።

የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጉዳዩን አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት፡ ከእስር የተለቀቁት አሜሪካውያን “ለዓመታት በስቃይ እና ቀጣይ ዕጣቸውን ባለማወቅ የደረሰባቸውን እንግልት ተቋቁመው በመጨረሻው የሚወዷቸውን ቤተሰቦቻቸውን ይቀላቀላሉ” ብለዋል።

ባይደን አያይዘውም “ይህን ውጤት እንድናገኝ ያላሰለሰ ጥረት አደረጉ” ያሏቸውን የኳታር፣ የኦማን፣ የደቡብ ኮሪያ እና የስዊዘርላንድ መንግስታትን አመስግነዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር “አፈና እና የዘፈቀደ እስራት ስጋት” እንዳለ ማስታወቁን የጠቀሱት ባይደን፣ “አሜሪካውያን ወደ ኢራን እንዳይጓዙ” ሲሉም አስጠንቅቀዋል።

ሁሉም አሜሪካውያን ለእነዚህ ቃላት ትኩረት ሰጥተው ሊያጤኗቸው ይገባል”

“ሁሉም አሜሪካውያን ለእነዚህ ቃላት ትኩረት ሰጥተው ሊያጤኗቸው ይገባል” ያሉት ባይደን፤ “ማስጠንቀቂያውን የማይከተሉ ከሆነ ግን ከእስር እንደሚለቀቁ ተስፋ ባያሳድሩ ይበጃል” ብለዋል።

የኢራኑ ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ በበኩላቸው፡ ሁለቱ አገሮች በትላንትናው ዕለት የደረሱት የእስረኞች ልውውጥ “በእኛ እና በዩናይትድ ስቴትስ መካከል ለሚደረግ የሰብአዊ እርምጃ እንደ አዎንታዊ እርከን ሊታይ ይችላል” ብለዋል።

“በእርግጠኝነት መተማመንን ለማጎልበት ይረዳል” ሲሉም በኒውዮርኩ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ወቅት ለጋዜጠኞች በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG