ኢራን ከዩናይትድ ስቴትስ ጋራ፣ ዛሬ ሰኞ፣ የእስረኞች ልውውጥ እንደምታደርግ አስታውቃለች። የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ናስር ካናኒ ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃለ ምልልስ፣ በዩናይትድ ስቴትስ ማዕቀብ ተጥሎበት የነበረው ስድስት ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር፣ ደቡብ ኮርያ ከሚገኝ የባንክ ሒሳቧ ወደ ኳታር ባንክ እንዲዘዋወር ስትጠብቅ እንደቆየች ገልጸዋል፡፡
የገንዘብ ዝውውር ስምምነቱ፣ በኢራን ታስረው ለሚገኙ አምስት አሜሪካውያንና በዩናይትድ ስቴትስ ለሚገኙ አምስት ኢራናውያን የእስረኞች ልውውጥ መንገድ እንደከፈተ ተናግረዋል። ጉዳዩን በቅርብ የሚያውቁ ግለሰቦችን ጠቅሰው የወጡ ዘገባዎች እንዳመለከቱት፣ ኳታር፣ ገንዘቡ ዛሬ ሰኞ እንደተላለፈ ለኢራንና ለአሜሪካ አሳውቃለች።
በጉዳዩ ላይ፣ እስከ አሁን ከዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናት የተገኘ ማረጋገጫ የለም፡፡ የዋይት ሐውስ የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ቃል አቀባይ ጆን ከርቢ፣ ባለፈው ሳምንት ለአሜሪካ ድምፅ ሲናገሩ፣ የባይደን አስተዳደር፣ የእስረኛ ልውውጡ በቅርብ ጊዜ እንደሚከናወን ያለውን ተስፋ አመልክተው ነበር።
በእስረኛ ልውውጡ የሚለቀቁት ሦስቱ አሜሪካውያን፥ ሲያማክ ናማዚ፣ ኢማድ ሻርጊ እና ሞራድ ታህባዝ ናቸው፡፡ እኒኽ ሦስቱ፣ ከሌላ ስማቸው ካልተገለጹ ሁለት አሜሪካውያን ጋራ፣ ከነበሩበት በታህራን ከሚገኝ እስር ቤት ወጥተው በመኖሪያ ቤት ውስጥ እንደታሰሩ ተገልጿል።
ዩናይትድ ስቴትስ፣ አምስቱም አሜሪካውያን ያለአግባብ መታሰራቸውን ትከራከራለች። ኢራን በበኩሏ፣ በስምምነቱ መሠረት እንዲፈቱ የምትፈልጋቸውን አምስት ኢራናውያንን ለይታ አሳውቃለች።
ወደ ኳታር የተላለፈው የኢራን ገንዘብ፣ ለሰብአዊ ጉዳዮች ብቻ ጥቅም ላይ እንዲውል ነው የተወሰነው፡፡ ኢራን፣ ገንዘቡን ለሌላ ተግባር ልትጠቀምበት ትችላለች፤ የሚለውን ጥርጣሬ፣ የባይደን አስተዳደር፣ ገንዘቡ ለተፈቀደለት ጉዳይ ብቻ ስለመውጣቱ ክትትል ይደረጋል፤ ሲል ውድቅ አድርጓል።
መድረክ / ፎረም