በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አድዋ ላይ በፖሊስና በወጣቶች መካከል ግጭት ተፈጥሮ ነበር


በትግራይ ክልል አድዋ ከተማ በመንግሥት በተጠራ የወጣቶች ኮንፈረንስ ላይ ለተገኙ ተሣታፊዎች ይከፈላል ከተባለ የውሎ አበል ክፍያ ጋር በተያያዘ የተፈጠረ አለመግባባት ወደ ፖሊስና ወጣቶች ግጭት አምርቶ በአንድ ወጣት ላይ ከባድ ድብደባ እንደፈፀመ፤ በሁለት የፖሊስ አባላት ላይም ጉዳት እንደደረሰ ታውቋል።

ከግንቦት 19 እስከ ግንቦት 21 በተካሄደ ስብሰባ ላይ እንዲገኙ ሲደረግ የውሎ አበል እንደሚከፈላቸው ተነግሯቸው እንደነበርና በስብሰባው የመጨረሻ ቀን በቀን 26 ብር እንደሚከፈላቸው የተገለፀላቸው መሆኑን ወጣቶቹ ገልፀዋል።

ይሁን እንጂ የተነገራቸቸው የአበል መጠን የቀን ሥራ ሠርተው ከሚያገኙት በእጅጉ ያነሰ መሆኑን በማመልከት ስብሰባው ላይ ለነበሩት ከንቲባ ጥያቄ ማቅረባቸውን ተናግረዋል።

ምንም አይነት ሥራ እንደሌለውና በፖሊስ ከፍተኛ ድብደባ እንደተፈፀመበት የተናገረው ወጣት ዮሃንስ ገብረኪዳን ስለ ሁኔታው ሲያብራራ “800 የሚሆን ተሳታፊ ነበር። ሰዉ የውሎ አበል አለ ብሎ ሲሰበሰብ ከቆየ በኋላ ስብሰባው በሦስተኛው ቀን ሲጠናቀቅ የውሎ አበሉን መጠን አሳውቁን ብሎ ጠየቀ። በቀን 26 ብር ነው እሚከፈላችሁ አሉን። ሥራ አጥ ብላችሁ ከሰበሰባችሁን በኋላ የቀን ሥራ ሰርተን ከ80 ብር እስከ 100 ብር የምናገኝበትን ጊዜያችንን አባከናችሁብን እያሉ ከንቲባውን መልስልን እያሉ ማናገር ጀመሩ። እሱም ለማረጋጋት እየሞከረ ሳለ አብረውት የነበሩት ጥለውት ሄዱ። በዚህ ጊዜ ነበር ፖሊሶች የመጡትና ወጣቱም ድንጋይ መወርወር የጀመረው” ብሏል።

ፖሊስ ዱላ ሲጀምር ወጣቱም ወደ ሽሽት እንደገባ፤ እርሱም በቅርቡ ወዳገኘው ቤት እንደገባ፤ ያኔ የፖሊስ አባላት ከቤት አውጥተው ነፍሱን እስኪስት እንደደበደቡት ተናግሯል።

“ከቤት አውጥተው መንገድ ላይ ዘረጉኝ። አራት ጊዜ ራሴ ላይ መቱኝ፤ ከዚያ ማጅራቴን በዱላ ሲመቱኝ አዕምሮየን ስቼ ወደቅኩኝ። ሰዉ ተዉ እያላቸ እያገላበጡ መቱኝ። ራሴን ስቼ ስለነበር በፖሊስ መኪና ጭነው ወደ ጣቢያ ወስደው ውጭ ጣሉኝ። ደሜ እየፈሰሰ ከቆየሁ ብኋላ በሰንሰለት አስረው ወደ ሆስፖታል ወሰዱኝ” ብሏል ወጣት ዮሃንስ።

ከአንገቱ በታች ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት የገለፀው ዮሃንስ ከሆስፒታል ወደ እሥር ቤት እንደመለሱትና በመጨረሻ በአምስት ሺህ ብር ዋስ እንደለቀቁት ተናግሯል። ሌሎች 13 ወጣቶች እንደታሰሩም ገልጿል።

ስለ ጉዳዩ የተጠየቁት የአድዋ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ዘሥላሴ ዘረአውሩክ የተፈጠረው አለመግባባት ከስብሰባው አጀንዳ ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለውና ስብሰባው በመግባባት ማለቁን አመልክተዋል።

ይሁን እንጂ በመንግሥት የፋይናንስ አሠራር የከተማ የቀን አበል ስለማይከፈል ክፍያው የቀን አበል ሳይሆን የሻይ እንደነበር ገልፀው ሆኖም ግን ይኸው ቀድሞ ሊነገራቸው ይገባ እንደነበረ አምነዋል። ስለሆነም “የወጣቶቹ ጥያቄ ተገቢ ነበር፤ ለተፈጠረው ችግር ኃላፊነቱ የኛ ነው” ብለዋል።

ተፈፀመ የተባለውን ድብደባና እሥራት አስመልክቶ ድንጋይ መወርወርና ሌሎችም አላስፈላጊ አድራጎቶች በወጣቶቹ ተፈፅሟል ያሉት የአድዋ ከተማ ምክትል ከንቲባ ፖሊስ ሥርዓት ለማስከበር የወሰደው እርምጃ ከመጠን በላይ መሆኑን አለመሆኑን ለማጣራት ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን ገልፀዋል።

በወጣት ዮሃንስ ላይ የተፈፀመውን ድብደባ እንደሚያውቁና ወደ ህክምና የተወሰደው በፀጥታ አስከባሪዎቹ መሆኑን፤ ግጭቱ ወቅት በሁለት የፀጥታ ጥበቃ አባላት ላይ በድንጋይ ጉዳት እንደደረሰ ከንቲባው አመልክተዋል።

“የተወሰደው እርምጃ ከመጠን በላይ ነው ወይ? ለሚለው ወጣቱ ራሱ ምስክር ነው። ወጣቱ ቆሞ እያለ ወይም ተይዞ እያለ ወይም ደግሞ ምንም ሳያደርግ እንዲህ ዓይነት በደል ተፈፅሞበት ከሆነ በህግም የሚያስጠይቅ ስለሆነ አጣርተን ከመጠን በላይ የሆነ እርምጃ የወሰደው አካል ተጣርቶ ህጋዊ እርምጃ መወሰድ አለበት በሚለው እኔም እስማማለሁ” ብለዋል ከንቲባው።

የታሠሩትን ቁጥር አስመልክቶ በማኅበራዊ መገናኛ እንደተሠራጨው 13 ሳይሆኑ ሰባት እንደነበሩና ከአንድ ቀን በኋላ በዋስ እንደተለቀቁ ከንቲባ ዘሥላሴ ዘረአውሩክ ገልፀው አበሉም 26 ብር ሳይሆን ለሦስቱ ቀናት በድምሩ አንድ መቶ ብር እንደተከፈላቸው ለቪኦኤ ገልፀዋል።

የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።

አድዋ ላይ በፖሊስና በወጣቶች መካከል ግጭት ተፈጥሮ ነበር
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:39 0:00

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG