ዛሬ ረቡዕ፣ ግንቦት 14 ቀን 2016 ዓ.ም.፣ በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ወረዳ አንድ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የተከሠተው የእሳት አደጋ፣ የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያን እንቅስቃሴ እንዳላስተጓጎለ፣ ኮሚሽኑና አየር መንገዱ አስታውቀዋል።
የቃጠሎ አደጋው፣ ከአውሮፕላን ማረፊያው ቅጽር ውጭ መከሠቱን፣ የአዲስ አበባ ከተማ እሳት እና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ባለሞያ አቶ ንጋቱ ማሞ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።
አደጋው የተከሠተው ከቀኑ 9 ሰዓት ከ41 ደቂቃ ላይ እንደነበረ፣ የሕዝብ ግንኙነት ባለሞያው ከቀኑ 12 ሰዓት ገደማ ከስፍራው በስልክ በሰጡን አስተያየት አስረድተዋል።
የአደጋው መንሥኤ እና ያደረሰው አጠቃላይ ጉዳት ተጣርቶ ይፋ እንደሚደረግም፣ አቶ ንጋቱ ማሞ ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድም፣ የእሳት አደጋው፥ ከአውሮፕላን ማረፊያው አጥር ውጭ ባሉ የመኖሪያ ቤቶች ላይ እንደተከሠተ፣ በማኅበራዊ የትስስር ገጾቹ ባወጣው መረጃ አስታውቋል።
የቃጠሎ አደጋው፣ “በዕለታዊ እንቅስቃሴዎቹ ላይ ምንም ዓይነት መስተጓጎል እንዳልፈጠረ” እና በቁጥጥር ሥር መዋሉንም አረጋግጧል፡፡
መድረክ / ፎረም