በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አፈ ጉባኤ አቶ አባ ዱላ ገመዳ የሥልጣን መልቀቂያ ማስገባታቸው ተሰማ የኢሕአዴ ጽ/ቤት አስተባብሏል


አፈ ጉባኤ አቶ አባ ዱላ ገመዳ
አፈ ጉባኤ አቶ አባ ዱላ ገመዳ

የቀድሞ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንትና የአሁኑ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አባዱላ ገመዳ የሥልጣን መልቀቂያ ደብዳቤ ማስገባታቸውን ስማቸውና ማንነታቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ አንድ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ ለአሜሪካ ድምጽ ተናግረዋል።

አቶ አባዱላ አሁን ካለው የአፈ ጉባኤነት ሥልጣን በፍቃዳቸው ለመልቀቅ የጠየቁበትን ደበዳቤ ካስገቡ ቀናት መቆጠራቸውን ኃላፊው ጠቁመዋል። ነገር ግን ሥልጣናቸው የፌደራል አካል እንደመሆኑ ደብዳቤውን ካስገቡ በኋላ ድርጅታቸው ኢሕዴግ በይፋ ተሰብስቦ የወሰነው ነገር አለመኖሩን ኃላፊው ጨምረው ገልፀዋል።

አፈ ጉባኤ አቶ አባ ዱላ ገመዳ የሥልጣን መልቀቂያ ማስገባታቸው ተሰማ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:01 0:00

አቶ አባዱላ ሥልጣናቸውን ለመልቀቅ ጥያቄ ባቀረቡበት ደብዳቤ ላይ የምክኒያታቸውን ዝርዝር ማቅረባቸውን ኃላፊው ለቪኦኤ ቢጠቁሙም ምን እንደሆኑ ሊገልጹልን ፈቃደኛ አልሆኑም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ አፈ ጉባኤ አባዱላ ገመዳ ሰሞኑን በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች መካከል ሲስተዋል በቆየው ግጭት ሳቢያ በብዙዎች ሞትና በጅምላ መፈናቀል ላይ ቅሬታ እንደነበራቸውና ቅሬታቸውንም በስብሰባ ላይ ሲያንፀባርቁ እንደቆዩ አንድ ሌላ ቅርበት ያላቸው ኃላፊ ለቪኦኤ ተናግረዋል።

መረጃዎቹን ለአሜሪካ ድምጽ የሰጡት የሥራ ኃላፊ አክለው፤ አቶ አባዱላ ለመልቀቂያ ጥያቄያቸው እስካሁን ውሳኔ ስላላገኙ ፓርላማው ከነገ በስቲያ ሰኞ ሲከፈት በመክፈቻው ላይ ሊገኙ እንደሚችሉ ጠቁሞናል።

አፈጉባኤ አባዱላ ገመዳ በዚህ ጉዳይ ላይ ምላሽ እንዲሰጡኝ በእጅ ስልካቸው ተደጋጋሚ ሙከራ አድርጌ ስልካቸው አይመልስም። ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱ ምክትል አፈጉባኤ ለወ/ሮ ሽታዬ ምናለም ተደጋጋሚ ሙከራ አድርጌ ስልካቸው ዝግ ነው። የፌደራሉን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮንም ምላሽ እንዲሰጡን ተደጋጋሚ ሙከራ አድጌያለሁ የሳቸውም ስልክ አይመልስም።

ከፓርቲያቸ የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) ምላሽ ለማግኘት ያደረኩት ጥረት አልተሳካም። በሌላ በኩል ግን አንድ በቴክስት ምልልስ ያገኘኋቸው የኦሕዴድ ባለስልጣን “በእነዚህ ቀናት ብርቱ የሆነ የፓርቲ ስብሰባ ላይ በመሆኔ ላናግርሽ አልችልም” ብለው በቴክስት መልሰውልኛል።

ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽ/ቤትም መረጃ ለማግኘት ሞክረናል አልተሳካም።

በመጨረሻ ያገኘናቸው የኢሕዴግ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ እኛ ጋር የደረሰ ነገር የለም ብለውኛል።

ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉት የሥራ ኃላፊ ጋር በድጋሚ ደውዬ ነበር። አፈ ጉባኤ አቶ አባ ዱላ ገመዳ የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤ ማስገባታቸውን በአጽንኦት አረጋግጠውልኛል።

ለአሜሪካ ድምፅ - ጽዮን ግርማ ዋሽንግተን ዲሲ

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG