ሃያ ስድስት ሺህ ቶን ወይም ከ265 ሺህ በላይ ኲንታል በቆሎ ጭኖ ከዩክሬን ኦዴሳ ወደብ ከትናንት በስተያ፤ ሰኞ የተነሳው መርከብ ዛሬ በቱርክ የተደረገበትን ፍተሻ አልፎ ጉዞውን ወደ ሊባኖስ ቀጥሏል። ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ እህል ጭኖ ከዩክሬን በተነሳው በዚህ መርከብ ላይ ዘጠና ደቂቃ የቆየ ፍተሻ ማድረጋቸውን የቱርክ የመከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል።
መርማሪዎቹ የተውጣጡት ከዩክሬን፣ ከሩሲያ፣ ከቱርክና ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሲሆን እነዚሁ ወገኖች በዓለም ላይ የተፈጠረውን የምግብ ቀውስ ለማርገብ የሚያችል እህል ከዩክሬን እንዲወጣ ለማድረግ ባለፈው ወር ስምምነት ላይ ደርሰው ነበር።
የዩክሬን መሠረተ ልማት ሚኒስቴር እንዳለው ሌሎች 17 መርከቦች ተጭነው ዩክሬንን ለመልቀቅ ፈቃድ በመጠባበቅ ላይ ናቸው።
ከአውስትራሊያውያን ተማሪዎች ጋር ዛሬ በቪዲዮ የተወያዩት የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ “የመጀመሪያው ጭነት ምንም ማለት አይደለም፤ እህል መጫኑ ይቀጥላል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል።