በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአዲሱ የመገናኛ ብዙሃን ፓሊሲ ፋይዳ


ባሳለፍነው 2012ዓ.ም. ማጠናቀቂያ ላይ የኢትዮጵያ ሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ፖሊሲ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ፀድቆ በስራ ላይ እንዲውል ወስኗል። የመገናኛ ብዙሃን ሲመራበት የቆየው ህግ ማሻሻያ ፀድቆ እንዲወጣ በሚጠበቅበት ወቅት ቀድሞ የወጣው የሚዲያ ፖሊሲ ለምን አስፈለገ? ፖሊሲው እየተሻሻለ ላለው የሚዲያ ህግና ዘርፈ ብዙ ችግሮች ላሉበት የኢትዮጵያ ሚዲያስ የሚጨምረው ነገር አለ ወይ? ፓሊሲውን አዘጋጅቶ ያቀረበውን የብሮድካስት ባለስልጣንና፣ የሚዲያ ባለሙያዎችን አነጋግረናል ።

ባሳለፍነው ነሐሴ ወር መጨረሻ ላይ ፀድቆ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ስራ ላይ የዋለው የመገናኛ ብዙሃን ፓሊሲ መንግስት በሚዲያው ዙሪያ ህግ የሚያወጣበትን አቅጣጫ የሚጠቁምና ወደፊት ዘርፉ ሊደርስበት የሚገባውን ደረጃ የሚጠቁም መሆኑን ፖሊሲውን ያዘጋጀው የብሮድካስት ባለስልጣን አስታውቋል።

በቀጣይ የሀገሪቱን የሚዲያ ሁኔታ የሚመራው ፓሊሲ ከህትመትና ከብሮድካት ሚዲያ በተጨማሪ ከዚህ ቀደም በመገናኛ ብዙሃን ህጎች ላይ ያልነበሩትን በበይነ መረብ አማካኝነት የሚሰራጭ የኦንላይን ሚዲያንና እና የማህበራዊ ሚዲያን እንደ መገናኛ ብዙሃን ዘርፍ አካቷል፡፡ ይህም በቀጣይ ፀድቆ ይወጣል ተብሎ ለሚጠበቀው አስገዳጅ የሚዲያ ህግ መስመር የሚጠርግ መሆኑን የብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ ያስረዳሉ።

በቀጣይ ይወጣል ተብሎ የሚጠበቅው የሚዲያ ህጉ ማሻሻያ ሲወጣም የብሮድካስት ባለስልጣን መስሪያ ቤት ስያሜውንና የስራ ሀላፊነቱን ቀይሮ የመንገናኛ ብዙሀን ባለስልጣን እንደሚባልም ዶክተር ጌታቸው ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።

እስካሁን የመገናኛ ብዙሃን የሚመራበት ፖሊሲ አለመኖሩ ዘርፉን ለብዙ ችግሮች ዳርጎታል የሚሉት ዶክተር ጌታቸው የፖሊስው መኖር ቀጥሎ ለሚወጡት ህጎችና መመሪያዎች መሰርት ሆኖ ተግዳሮቶችን መፍታት ያስችላል ይላሉ።

በፖሊሲው ዙሪያ አስተያየታቸውን እንዲሰጡን የጠየቅናቸው በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የጋዜጠኝነትና ኮሚዩኒኬሽን ትምህርት ቤት ሀላፊ የሆኑት መኩሪያ መካሻ በበኩላቸው ፓሊሲው የሚዲያ ህጉ ፀድቆ ከመውጣቱ በፊት ስራ ላይ መዋሉ እየተሻሻለ ላለው ህግ ግብዓት ይሆናል ይላሉ።

በኢትዮጵያ እስካሁን የሚወጡት የሚዲያ ህጎች በምን መሰረት ላይ ተመስርተው እንደሚወጡ አይታወቅም ነበር የሚለው ደግሞ በሪፖርተር ጋዜጣ ለበካታ አመታት ጋዜጠኛ ሆኖ ያገለገለው ዩሀንስ አምበር ነው። ዩሀንስ በኢትዮጵያ እስከዛሬ የሚዲያ ፖሊሲ አለመኖሩ ዘፍሩን ጎድቶታል ብሎ ያምናል።

አዲሱ የሚዲያ ፓሊሲ በማህበራዊ ሚዲያ የተሰራጩ የወንጀል ድርጊቶችንመመርመርና ተጠያቂ ማድረግ በጣም አስቸጋሪ ሆኖ መቆየቱን ጠቅሶ የኢትዮጵያ የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን ወይም ኦላይን ሚዲያ አገልግሎት ሰጪዎች ገቢ በሚያስገኝ ስራ ላይ ከተሰማሩ በንግድ ቢሮና በታክስ ባለስልጣን መመዝገብ እንዳለባቸው፣በመገናኛ ብዙሃን ሬጉላቶሪ አካል ምዝገባና ፈቃድ ማግኘት እንደሚኖርባቸውም አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

ይህ አንድ እርምጃ ነው የሚሉት የሚዲያ ባለሙያ አቶ መኩሪያ በኢተርኔት የሚሰራጩ መረጃዎችን ለመቆጣጠር ግን የተለያዩ ዘርፎች በቅንጅት መስራትን ይጠይቃል ይላሉ።

አዲሱ የሚዲያ ፖሊሲ የመገናኛ ብዙሃን ባለቤትነትን ለኢትዮጵያውያን ብቻ ይሰጥ የነበርው ህግ ተሻሽሎ ትውልደ ኢትዮጵያውያንም በመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ ላይ እንዲሳተፉ ሊደረግ እንደሚገባ ይጠቅሳል። ይህ በተለይ ዘርፉን በኢኮኖሚ ለማሳደግ ትልቅ ሚና እንዳለው ዶክተር ጌታቸው ይጠቅሳሉ።

እርምጃው ጥሩ ነው የሚሉት አቶ መካሻ ይህ የባለቤትነት ፈቃድ ግን በትውልደ ኢትዮጵያውያኖች ብቻ ሊወሰን አይገባም ብለውም ይከራከራሉ።

ለአመታት የኢትዮጵያ ሚዲያን ፈተና በሙያው የተጋፈጠው ዩሀንስም የሚዲያ ፓሊሲውም ሆነ የህግ ማሻሻያ አዋጁ ብቻውን ትርጉም እንደማይኖረውና የመረጃ መብትን የመሳሰሉ ሌሎች አብረው መታየት ያለባቸው የህግ ማዕቀፎችም ጎን ለጎን ሊሰራባቸው እንደሚገባ ያሳስባል።

ከሚዲያው ፖሊሲ ቀጥሎ ይወጣል ተብሎ የሚጠበቀው የተሻሻለው የሚዲያ ህግ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ቶሎ ሊያያቸው ሲገባቸው ከዘገዩት ህጎች አንዱ ነው። ምክር ቤቱ በአዲሱ አመት ከእረፍት ሲመለስ፣ ከቀረበለት ወራትን ያስቆጠረውን የሚዲያ ህግ፣ ፖሊሲው ያስቀመጣቸውን አቅጣጫዎች አካቶ ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ

የአዲሱ የመገናኛ ብዙሃን ፓሊሲ ፋይዳ
please wait

No media source currently available

0:00 0:08:41 0:00


XS
SM
MD
LG