በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ ከእስር ተለቀቀ


ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ
ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ

- ሲፒጄ የጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ እስር አውግዟል

"ኢትዮጵያን ኢንሳይደር" የተባለው የኢተርኔት ጋዜጣ መስራች እና ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ ከሦስት ቀናት እስር በኋላ በዛሬው ዕለት ተለቋል።

ባለፈው ቅዳሜ በአዲስ አበባ የተከበረውን የአሮሞ የምስጋና ቀንኢሬቻን በመዘገብ ላይ የነበረው ጋዜጠኛው፣ የደረሰበት ሳይታወቅ ሰዓታት ከተቆጠሩ በኃላ በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ቅጽር ታስሮ እንደሚገኝ የሥራ አጋሮቹ ለአሜሪካ ድምጽ ይፋ አድርገው ነበር።

በፖሊስ ቁጥጥር ስር መሆኑን ያረጋገጠው የፌዴራል ፖሊስ በበኩሉ “አንዳችም የሚያሳስብ ነገር የለም” ማለቱ ተዘግቦ ነበር። ሆኖም ፖሊስ እስራቱን አስመልክቶ ተጨማሪ ማብራሪያ አልሰጠም።

ተስፋለም አዲስ አበባ ላይ የተካሄደውን የኢሬቻ አከባበር ሥነ ስርዓት ከዘገበ በኋላ በዝግጅቱ ከተሳተፉ ውስጥ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስተዳደር ላይ ያላቸውን ትችት ሲገልጹ የሚያሳይ ቪዲዮ ኢትዮጵያ ኢንሳይደር የፌስቡክ ገጹ ላይ አውጥቶ ነበር።

ተስፋለም በ2007 ዓ.ም “በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው” ከተከሰሱት ሦስት ጋዜጠኞች እና ስድስት ጦማሪያን የነበሩበት የዞን ዘጠኝ ጦማሪያን አንዱ ነበር።

አምስት አባላቱ ከአንድ ዓመት በላይ ለሚሆን ጊዜ ታስረው የተለቀቁት ዞን ዘጠኝ በ2008 ዓ.ም ለጋዜጠኞች መብት የቆመው ሲፒጄ ተሸላሚ ለመሆን መብቃቱም ይታወሳል።

የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቾቹ፣ ሲፒጄ እና ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ተቋማት የጋዜጠኛውን መታሰር በማውገዝ በአስቸኳይ እንዲፈታ ጠይቀው ነበር።

XS
SM
MD
LG