በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ለእስር ስለታደረጉት ፖለቲከኛ አብርሃ ደስታ እንዲሁም ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ


በቅርቡ ለእስር የተዳረጉት አብርሃ ደስታ እና ጋዜጠኛ ተስፋለም ወ/የስ
በቅርቡ ለእስር የተዳረጉት አብርሃ ደስታ እና ጋዜጠኛ ተስፋለም ወ/የስ

በትግራይ ክልል ውስጥ ይንቀሳቀሱ ከነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አንዱ የሆነው አረና ለልዑላዊነት እና ዴሞክራሲ ፓርቲ ሊቀመንበር የነበሩት አቶ አብርሃ ደስታ በቁጥጥር ስር ከዋሉ አራት ቀናት አልፈዋል።
የአቶ አብርሃ ጠበቃ የሆኑት አቶ ተስፋለም በርሄ እንደሚሉት አቶ አብርሃ ቅዳሜ ዕለት ፍርድ ቤት ቀርበዋል። በዚያም የተከሰሱበት ምክንያት ይፋ ተደርጎላቸዋል።ክሳቸው በማህበራዊ መገናኛዎች ላይ ከሚያሰራጩት መልዕክት ጋር ከመያያዙ በተጨማሪ ህገወጥ የጦር መሳሪያ በመያዝ ወንጀል ተጠርጥረው መያዛቸው እንደተገለጸላቸው ነግረውናል።

ጠበቃ ተስፋለም አቶ አብርሃ በቁጥጥር ስር ከዋሉበት ቀን ጀምሮ ከሌሎች ታሳሪዎች በተለየ ለአካል ጉዳትም ሆነ ለሌላ ኢሰብዓዊ አያያዝ አለመዳረጋቸውን ተናግረዋል። ከዚህ ይልቅ ከጉዳዩ ጋር ንክኪ የላቸውም የተባሉት ታናሽ ወንድማቸው አብረው መታሰራቸው እንዳሳሰባቸው አክለዋል። ጉዳዩን የበለጠ ለማጣራት ተጨማሪ ጊዜ እንደተጠየቀም ተሰምቷል።

በሌላ ዜና ፣ኢትዮጵያን ኢንሳይደር የተሰኘ የበይነ መረብ ላይ የዜና አውታር መስራቹ ዕወቁ ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንደሚገኝ መስማቷን የስራ አጋሩ በዕምነት የወንድወሰን ለአሜሪካ ድምጽ ተናግራለች።

ይሄ ዘገባ እስከ ተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ በዕምነት ተስፋለምን በአካልም ለማግኘት፣ የታሰረበትንም ምክንያት ለማወቅ እንዳዳገተ ታስረዳለች።

በተለያዩ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገራት የዜና አውታሮች ላይ በጋዜጠኝነት የሰራው ተስፋለም ወልደየስ እስር የመጀመሪያው አይደለም ። በ2007 ዓመተምህረት እሱ እና ዞን 9 ተብለው የሚጠሩ የጦማሪ ቡድን አባላት ከ500 በላይ ቀናትን በእስር አሳልፈዋል።

የጸረ -ሽብር ህጉ ተጣቅሶ የቀረበባቸው ክስ፣በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ወደ ስልጣን መምጣት ዋዜማ ከተነሳ እንዲሁም ከእስር ከተለቀቀ በኃላ ፣ ተስፋለም ወደ ጀርመን ቦን በማቅናት ለጀርመን ድምጽ በጋዜጠኝነት ሰርቷል። በቅርቡ ወደ ሀገር ቤት በመመለስ ኢትዮጵያን ኢንሳይደር የበይነ መረብ ላይ አውታር በመመስረት ዘገባዎችን ሲያጋራ ሰንብቷል።

ከወጣቱ ጋዜጠኛ እስር ጋር በተገናኛ ማብራሪያ ለመጠየቅ ፣የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ባለስልጣናትን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለዛሬው አልተሳካም። መልሳቸውን እንዳገኘን እንመለስበታለን፥

ለአሜሪካ ድምጽ ፣ሀብታሙ ስዩም

ዋሺንግተን ዲሲ

ለእስር ስለታደረጉት ፖለቲከኛ አብርሃ ደስታ እንዲሁም ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:39 0:00


XS
SM
MD
LG