“በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት በተደረገው ጦርነት ወቅት ለተፈጸመው የመብት ጥሰት በተለየና ኢፍትሃዊ በሆነ ሁኔታ የኢትዮጵያን መንግሥት ተጠያቂ አድርጋለች” ስትል ኢትዮጵያ አሜሪካንን ወቀሰች።
አሜሪካ ኢትዮጵያን በተለይ ተጠያቂ ማድረጓ “ወገናዊነት” የታየበትና ከአሜሪካ መንግሥት በኩል የወጣው ውንጀላም “ተንኳሽ” ነው ሲል የኢትዮጵያው የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።
የአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ትናንት በሰጡት መግለጫ በጦርነቱ የተሳተፎት ሁሉም ወገኖች የጦር ወንጀል ፈጽመዋል ብለው ነበር።
ብሊንከን መግለጫ በሰጡበት ወቅት የኢትዮጵያ መንግሥት፣ የኤርትራና የአማራ ኃይሎች በሰብዓዊነት ላይ ወንጀል መፈፀሙን የገለፁ ሲሆን፣ በዚህ ጉዳይ የትግራይ አማጽያንን ሳይጠቅሱ አልፈዋል።
ባለፈው ሳምንት ኢትዮጵያን ጎብኝተው የነበሩት ብሊንከን ወደ ዋሽንግተን ከተመለሱ በኋላ በጦርነቱ ለተፈጸሙ በደሎች ተጠያቂነት እንዲኖር ጠንከር ይለ ጥሪ አቅርበዋል።
ብሊንከን በመግለጫቸው እንዳሉት መሥሪያ ቤታቸው “ሕግጋትንና የነበረውን ሁኔታ በጥንቃቄ ከተመለከተ” በኋላ “የኢትዮያና የኤርትራ ኃይሎች እንዲሁም የትግራይ አማጽያንና የአማራ ኃይሎች የጦር ወንጀል ፈጽመዋል” ብለዋል።
ብሊንከን ዓመታዊ የሰብዓዊ መብትን የተመለከተውን ሪፖርት ሲያቀርቡ እንዳሉት፣ “የተፈጸሙት ወንጀሎች ድንገት የተፈጸሙ ወይም ጦርነት ያመጣቸው ጉዳቶች ሳይሆኑ፣ ሆን ተብለው ታቅደው የተፈጸሙ ናቸው” ብለዋል።
ብሊንከን ጨምረውም በጦርነቱ ከተሳተፉት ሦስቱ ማለትም የኢትዮጵያ፣ ኤርትራና አማራ ኃይሎች ግድያና ጾጣዊ ጥቃትን ያካተቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ፈጽመዋል ብለዋል። በሰብዓዊ መብት ጥሰቱ ጉዳይ የትግራይ አማጽያንን በመግለጫቸው አላነሱም ነበር።
የኢትዮጵያው የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ለዚህ በሰጠው ምላሽ የብሊንከን መግለጫ ኢፍትሃዊ በሆነ ሁኔታ ጥፋተኝነቱን አደላድሏል ሲል ከሷል።
መግለጫው አያይዞምክ “በተለይም እንደ አስገድዶ መድፈርና የጾታ ጥቃት የመሰሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን የሚያሳዩ በርካታ ማስረጃዎች እያሉ በአሜሪካ ወገን የወጣው ሪፖርት አንድን ወገን ከጥፋተኝነት ነጻ ለማድረግ ሞክሯል” ብሏል።
የኢትዮጵው የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ “ወገናዊነት የተንጸባረቀበትና ከፋፋይ የሆነው የአሜሪካ መግለጫ ብልህነት የጎደለውና ኢፍትሃዊ ነው” ሲል አክሏል።
ብሊንከን በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ተጠያቂነት እንዲኖር አበክረው ተናግረው የነበረ ቢሆንም፣ የጦር ወንጀልና የሰብዓዊ መብት ጥሰትን በተመለከተ አላነሱም ነበር። ይልቁንም ሰላምን በተመለከተ ያላቸውን የወደፊት ተስፋ ሲናገሩ ተደምጠው ነበር።
የኤኤፍፒ ሪፖርት እንዳለው በአሜሪካ በኩል በወጣው ሪፖርት ላይ የህወሃት ወገን አስተያየት እንዲሰጥ ጠይቆ መልስ አላገኘም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በአሜሪካው የህግ መወሰኛ ምክር ቤት (ሴኔት) የውጪ ግንኙነት ኮሚቴ አባል የሆኑት ሪፐብሊካኑ የአይዳሆ ተወካይ ጂም ሪሽ፣ በአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ኢትዮጵያ የጦር ወንጀል ስለፈመፈጸሟ የወጣው መግጫ ዘግይቶ የወጣ መሆኑን ጠቁመው፣ ሆኖም ግን ወደፊት ተመሳሳይ ጥሰቶች እንዳይፈጸሙ አሜሪካ ተግባራዊ እርምጃ መውሰድ አለባት ብለዋል።
እንደራሴው ዛሬ ባወጡት መግለጫ እንዳሉት "አሜሪካ ተጠያቂነትን ለማስፈንና የመብት ጥሰቶች ወደፊት እንዳይፈጸሙ ለማረጋገጥ በእጇ ያሉትን አማራጮች ተጠቅማ እርምጃ መውሰድ ይጠበቅባታል።" ብለዋል።