በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ዩናይትድ ስቴትስ በኢትዮጵያ የጦር ወንጀሎች መፈፀማቸውን ይፋ አደረገች


የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር የ2022 ዓ.ም የዩናይትድ ስቴትስ የሰብዓዊ መብቶች ሪፖርትን ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ ይፋ ባደረጉበት ወቅት
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር የ2022 ዓ.ም የዩናይትድ ስቴትስ የሰብዓዊ መብቶች ሪፖርትን ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ ይፋ ባደረጉበት ወቅት

የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ሰሜን ኢትዮጵያ ውስጥ በተካሄደው አስከፊ ጦርነት ሁሉም ወገኖች የጦር ወንጀሎች መፈፀማቸውን ማረጋገጡን አስታወቀ። በሰብዓዊነት ላይ ወንጀል ወንጀል በመፈፀምና በዘር ማጽዳት ተግባርም ተጠያቂ አድርጓቸዋል።

ይህ የአስተዳደሩ ውሳኔ በአሜሪካ ፖሊሲ ላይ ቀጥተኛ አንድምታ ባይኖረውም፣ እነደነዚህ ዓይነት ውንጀላዎች ለክስ እንዲቀርቡ ለሚደረጉ ጥሪዎች ክብደት ይሰጣል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ውሳኔውን ያሳወቁት በኢትዮጵያ ያደረጉትን ጉብኝት ጨርሰው ከተመለሱ አንድ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ነው። ብሊንከን በጉዟቸው ከኢትዮጵያ መንግሥት እና ከትግራይ ባለሥልጣናት እንዲሁም በግጭቱ ጥቃት ከደረሰባቸው ጋራ የተገናኙ ቢሆንም ዩናይትድስ ስቴትስ በተጠያቂነት ዙሪያ ያላትን ተስፋ የሚያመላክት ሐሳብ አመለካከት ብዙም አላንፀባረቁም።

የአሜሪካ ውሳኔ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ጦር ሰራዊት እንዲሁም የህወሃት ኃይሎች እና የአማራ ክልል አባላት የፈፀሟቸውን ጥቃቶች የሚያጠቃልል ሲሆን ብሊንከን "የጭካኔ ድርጊቶችን የፈፀሙ አካላት ተጠያቂ መሆን አለባቸው" ብለዋል።

ብሊንከን አክለው ብሊንከን "ሕጉን እና ያሉትን እውነታዎች በጥንቃቄ ከገመገምን በኋላ ጦርነቱ ውስጥ የተሳተፉት ፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ የኤርትራ መከላከያ ሠራዊት፣ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ኃይሎች እና የአማራ ኃይሎች በሰሜን ኢትዮጵያው በተካሄደው ጦርነት የጦር ወንጀል መፈፀማቸውን አረጋግጠናል" ብለዋል።

አያይዘውም " የኤርትራ መከላከያ ኃይሎች እና የአማራ ኃይሎች አባላትም ግድያን፣ አስገድዶ መድፈር እና ሌሎች ፆታዊ ጥቃቶች እና ከቤት ንብረት ማፈናቀልን ጨምሮ በሰብዓዊነት ላይ ወንጀል ፈፅመዋል" ካሉ በኋላ "የአማራ ኃይሎችም በምዕራብ ትግራይ ለትግራይ ተወላጆች በነበራቸው አያያዝ በግዳጅ የማፈናቀል፣ ዘር የማፅዳት እና በሰው ልጆች ላይ የሚፈፀም ወንጀል ፈፅመዋል።" ብለዋል።

ብሊንከን እነዚህን ውሳኔዎች ይፋ ያደረጉት የዓለም ሀገሮችን የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ አስመልክቶ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በየዓመቱ የሚያወጣውን የ2022 ዓ.ም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት ነው።

"በሰሜን ኢትዮጵያ በሲቪሎች ላይ የደረሰውን ለመናገር የሚከብድ ጥቃት እና ውድመት አወግዛለሁ" ያሉት ብሊንከን "በሁሉም ወገኖች ለተፈፀመው አሰቃቂ ግፍ እና በደል እውቅና መስጠት ሰላም ለማስፈን ወሳኝ እርምጃ ነው። በአዛዥነት ቦታ ላይ የሚገኙትችን ጨምሮ ለጭካኔ ተግባራቱ ተጠያቂ የሆኑት በሕግ መጠየቅ አለባቸው" ብለዋል።

ይፋ የተደረገው መደበኛ ውሳኔ ብሊንከን ሁለት ዓመታት በፈጀው ግጭት ወቅት ቀደም ብለው "በአንዳንድ የትግራይ አካባቢዎች የዘር ማፅዳት እየተፈፀመ ነው" ሲሉ ከተናገሩት የበለጠ ሚዛን የሚደፋ ይሆናል።

ብሊንከን አያይዘው "አሁን በኢትዮጵያ የሚታየው ሁኔታ በሌሎች የዓለም ክፍሎች ካለሁ ሁኔታ በእጅጉ የተለየ ነው። ባለፉት አራት ወራት ሁሉም ወገኖች የወሰዷቸው እርምጃዎች የሰውን ህወት ታድገዋል፣ በአስር ሺዎች የሞቆጠሩ ሰዎችን ህይወት ቀሯል። ይህ ግን ባለፉት ሁለት ዓመታት የሆነውን ሁኔታ አያጠፋውም። ለዚህ ነው ይህን የሽግግር ፍትህ ሂደት ወደፊት ማራመድ እና ተጠያቂነት እና እርቅ እንዲኖር አስፈላጊ የሚሆነው።" ብለዋል።

ባለፈው ዓመት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አጣሪ ኮሚሽን በኢትዮጵያ መንግሥት ኃይሎች፣ በትግራይ ኃይሎች እና በኤርትራ ሰራዊት የጦር ወንጀል እና በሰው ልጆች ላይ ወንጀል መፈፀማቸውን የሚያረጋግጡ መረጃዎች አቅርቦ ነበር። ሆኖም ኮሚሽኑ የኢትዮጵያ ኃይሎች "ሲቪሎችን ማስራብ"ን እንደጦር መሳሪያነት መጠቀሙን እና የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ኃይሎች "ወሲባዊ ባርነት" መፈፀማቸውን፣ የትግራይ ኃይሎች ግን አለመፈፀማቸውን ገልፆ ነበር።

በህዳር ወር በሰላም ስምምነት የተጠናቀቀው ግጭት በትግራይ ብቻ ግማሽ ሚሊየን ሰላማዊ ዜጎች መሞታቸውን ጌንት የተሰኘ ዩንቨርስቲ ጥናት አጥኚዎች ይፋ ያደረጉ ሲሆን የአሜሪካ ባለ[ልጣናትም ይህንኑ ቁጥር ጠቅሰዋል።

ብሊንከን ሁሉም ወገኖች የሰላም ስምምነቱን አክብረው "አካታች እና ሁሉን አቀፍ የሽግግር ፍትህ ሂደትን" ተግባራዊ ለማድረግ የገቡትን ቃል እንዲፈፅሙ ጥሪ አቅርበዋል።

"የዚህ ሪፖርት ዓላማ ወሬ ማውራት ወይም ማሳፈር አይደለም። ዓላማው በዓለም ዙሪያ የሰዎች ክብር በብዙ መንገድ ስጋት ሲገጥመው ክብሩን ለማስጠበቅ ለሚሠሩ ግለሰቦች የሚያስፈልጋቸውን ግብዓት ማቅረብ ነው። በርግጥ ይህ ሪፖርት በዓለም ዙሪያ በውጪ ያሉት ሀገሮች እይታ ቢሆንም ዩናይትድ ስቴትስ በሰብዓዊ መብቶች ዙሪያ የራሷ የሆኑ ፈተናዎች እንዳሉባት እናውቃለን።" ብለዋል።

ብሊንከን ይፋ ያደረጉት የአውሮፓውያን አቆጣጠር የ2022 ዓ.ም ሪፖርቱ በሁሉም የዓለም ክፍል በሚገኙ ሀገራት የሰብዓዊ መብቶችን ሁኔታ ወደ ኋላ ማሽቆልቆል መቀጠሉን ያመላከተ መሆኑንን ተናግረዋል።

ሪፖርቱ የኢራን መንግሥት ከማህሳ አሚኒ አሳዛኝ ግድያ በኋላ በሕዝቡ ላይ እየፈፀመ ያለውን አሰቃቂ በደል በዝርዝር መያዙን ብሊንተን ጠቁመዋል። ባለስልጣናት በደርዘን የሚቆጠሩ ህጻናትን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ተቃዋሚዎችን መግደላቸውን፤ በሺሆች የሚቆጠሩ ደግሞ በዘፈቀደመታሰራቸውንና የኢራን ኃይሎች የታሰሩ ተቃዋሚዎች ላይ የማሰቃየት እና ፆታን መሰረት ያደረገ ጥቃት መፈፀማቸውን የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ ይፋ አድርጓል።

XS
SM
MD
LG