ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድብ አሞላልና አጠቃቀም ጉዳዮች ላይ ከግብፅ እና ከሱዳን ጋር እያደረገች ባለችው ድርድር ስምምነት ላይ ሳይደረስ ግድቡን በተናጠል ለመሙላት በመወሰኗ አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምሰጠውን ወደ 100 ሚሊዮን ዶላይ ይጠጋል የተባለ የድጋፍ ገንዘብ በጊዜያዊነት ይዛለች። ይህንን ውሳኔ ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት ከአሜሪካ መንግሥት ማብራሪያ መጠየቁን የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስትር ደኤታ አቶ እዮብ ተካልኝ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል። የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ ያወጣውን መግለጫና ሳይመን ማርክስ ከአዲስ አበባ ያጠናቀረውን ዘገባ አካትታ ስመኝሽ የቆየ የሚከተለውን አዘጋጅታለች።
ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድብ አሞላልና አስተዳደር ዙሪያ የሚደረገው የሶስትዮሽ ድርድር ሳይጠናቀቅ የአባይን ግድብ ለመሙላት በመውሰኗ አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን እርዳታ በጊዜያዊነት ያገደችው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሰጡት አመራር መሆኑን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያቤት አስታውቋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ሞርጋን ኡርታገስ ለአሜሪካ ድምፅ በላኩት መግለጫ፣ አሜሪካ በህዳሴ ግድብ ድህንነት ዙሪያ ላይ ስምምነት ሳይደረስ የሚጀመር የውሃ ሙሌት በተፋሰሱ ዙሪያ የሚገኙ ሀገራትና ህዝቦች ላይ አደጋ ሊያደርስ ይችላል የሚል ስጋት እንዳላት በተደጋጋሚ መግለጿን ጠቅሰዋል። የውሃ ሙሌቱ ኢትዮጵያ በሐምሌ ወር ላይ የተናጠል ርምጃ ላለመውሰድ የገባችውን ውስኔ የሚጥስ ነውም ብለዋል።
ኢትዮጵያ የህዳሴውን ግድብ ለመሙላት መወሰኗን ተከትሎ ባሳለፍነው ሳምንት አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን በሚሊዮኖች የሚቆጠር የገንዘብ ርዳታ ለጊዜው ማገዷን አስታውቃለች። እገዳው በቀጠናዊና የድንበር ፀጥታ ጉዳዮች የሚደረጉ ድጋፎችን እንደሚያካትት ተገልጿል።
ይሄን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግስት አሜሪካ ያሳለፈችው ጊዜያዊ ውሳኔ ላይ ማብራሪያ እንድትሰጥ መጠይቋን የኢትዮጵያ ገንዘብ ሚኒስቴር፣ ሚኒስቴር ዲኤታ አቶ እዮብ ተካልኝ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።
"ኢትዮጵያና ከአሜሪካ ካላቸው ጠንካራ ትስስር አንፃር፣ አሜሪካ ጉዳዩን በጥንቃቄ ያሰበችበት አይመስለንም። ይሄ ጉዳዩን በደንብ ያለመረዳት ይመስለናል። ቀጣይነት ያለውም አይመስለንም። ኢትዮጵያ እያደረገች ያለችው በየትኛውም ህግም ሆነ የሞራል ጥያቄ ቢመዘን ትክክል ስለሆነ ውሳኔያቸውን እንደገና ያስቡበታል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።"
አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ርዳታ ለማቋረጥ የወሰደችው ርምጃ በዋሽንግተን ሳምንታት የፈጀ ክርክር የተደረገበት ሲሆን አንዳንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለስልጣናት ርምጃው ያልተፈለገ የዲፕሎማሲ ቅራኔ ሊያስከትል ይችላል ሲሉ ተያውመውታል። ለኃይት ሃውስና ለፕሬዝዳንት ትራምፕ ቅርበት ያላቸው ደግሞ ኢትዮጵያ ከግብፅና ሱዳን ጋር ስምምነት ላይ ሳትደርስ ውሃ ሙሌት በመጀመሯ ማስተማሪያ ልትደረግ ይገባል ሲሉ ተሟግተዋል።
አሜሪካ ያገደችው የገንዘብ እርዳታ ለድርቅ፣ ለኤች አይ ቪ፣ ለፍልሰት፣ ለስደተኞች እና እንዱም ለተለያዩ ሰብዓዊ ርዳታዎች የሚደረገውን ድጋፍ እንደማያካትት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መግለጫ ገልጿል።
ለ ኮቪድ 19 ወረርሽኝ መከላከያ እንዲውል ቃል የተገቡት የመተንፈሻ መርጃ መሳሪያዎችና ለአስተዳደራዊ ድጋፍ የሚደረገው የገንዘብ ርዳታም በተቋረጠው ድጋፍ ውስጥ አልተካተተም።
ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።