በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ተደራዳሪዎቹ መግባታቸው ከመነገሩ በቀር ከደቡብ አፍሪካ የወጣ ወሬ የለም


ተደራዳሪዎቹ መግባታቸው ከመነገሩ በቀር ከደቡብ አፍሪካ የወጣ ወሬ የለም
please wait

No media source currently available

0:00 0:09:08 0:00

ተደራዳሪዎቹ መግባታቸው ከመነገሩ በቀር ከደቡብ አፍሪካ የወጣ ወሬ የለም

በአፍሪካ ኅብረት መሪነት ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ይካሄዳል ለተባለው የሠላም ንግግር ልዑካኑን ዛሬ መላኩን የኢትዮጵያ መንግሥት አስታውቋል።

የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት ዛሬ ባወጣው መግለጫ መንግሥቱ የሠላም ንግግሩን ግጭቱን በሠላም ለመፍታት እንደዕድል እንደሚመለከተው ገልፆ “ንግግሩ በመከላከያ ኃይል መሥዋዕትነት እየተስተካከለ የመጣውን ሁኔታ የበለጠ ለማጠናከር ምቹ አጋጣሚ የሚፈጥር አድርጎ ይወስደዋል” ብሏል።

በሌላ በኩል የህወሓት ተደራዳሪ ቡድን ደቡብ አፍሪካ ትናንት መግባቱን የህወሓት ከፍተኛ አመራር አባል የሆኑት ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረህይወት አስታውቀዋል።

ሮይተርስም ማንነቱን ያልጠቀሰው አንድ ባለስልጣን “የህወሓት ተደራዳሪ ልዑካን ቡድን ከዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ጋር ሆኖ ትናንት ዕሁድ ደርሷል” ማለቱን ዘግቧል።

ፕሮፌሰር ክንደያ የህወሓት ልዑካን ደቡብ አፍሪካ መግባታቸውን ባረጋገጡበት በትናንት ትዊታቸው “እጅግ አንገብጋቢ ጉዳዮች” ሲሉ ባሠፈሩት ዝርዝር ሥር “ግጭት በአስቸኳይ እንዲቆም፣ ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦትና የኤርትራ ኃይሎች መውጣት” የሚሉ ነጥቦችን ዘርዝረዋል። ይሁን እንጂ እነዚህ ነጥቦች ቅድመ ሁኔታ ይሁኑ አይሁኑ የጠቆሙት ነገር የለም።

“ወታደራዊ መፍትኄ ሊኖር አይችልም” ሲሉም በትዊታቸው ማጠቃለያ ላይ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ዩናይትድ ስቴትስና የአውሮፓ ኅብረትን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ አካላትም መሰል መልዕክት ማስተላለፋቸውን የቀጠሉ ቢሆንም የኢትዮጵያ መንግሥት ግን ወታደራዊ እርምጃውን እንደሚቀጥል ጠቁሟል።

የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት በዛሬው መግለጫው “መከላከያ ሠራዊት ቁልፍ የሚባሉ የትግራይ ከተሞችን መቆጣጠሩን ቀጥሏል” ሲል የውጊያውን መቀጠል አመላክቷል። የመከላከያ ሠራዊቱ “ይህንን ሲያደርግ በከተሞች ውጊያ ሳይደረግ የህወሓትን ወታደራዊ ዐቅም ለማሽመድመድ የሚያስችል ስልት ተጠቅሟል” ሲልም አክሏል።

መከላከያው ከሽሬ፣ አላማጣና ኮረም በኋላ ስለያዛቸው ከተሞች ግን አገልግሎቱ በመግለጫው አልጠቀሰም። ሆኖም አሶሲየትድ ፕረስ አንድ የሰብዓዊ ሠራተኛን ዋቢ በማድረግ ትናንት ባወጣው ዘገባ “ታሪካቷ አድዋ ከተማ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መያዟን” ገልጿል።

የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ባለፈው ዓርብ ጥቅምት 11/2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ላሉ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት በሰጡት ማብራሪያ “የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በትግራይ ክልል ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ወደነበረበት ለመመለስ፣ አውሮፕላን ጣቢያዎችንና የሌሎችም ፌዴራል ተቋማትን ደኅንነት ለመጠበቅ ቅድሚያ በመስጠት እርምጃ እየወሰደ ነው” ማለታቸው ይታወሳል።

ውጊያው በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ መንግሥት በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች ከግብረ ሰናይ ተቋማት ጋር በመቀናጀት እርዳታ እንዲደርስ እየሠራ መሆኑን ገልጿል።

በእነዚህ አካባቢዎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ሥራ ለማስጀመር የሚያስችል ዝግጅት እያደረገ መሆኑንም በኮምዩኒኬሽን መሥሪያ ቤቱ በኩል አመልክቷል። ከየአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በመነጋገር ሕዝባዊ አስተዳደር የሚቋቋምበትንና ማኅበራዊ አገልግሎቶች የሚጀምሩበትን መንገድ እያመቻቸ መሆኑንም ጠቁሟል።

የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ከተጫረበት ከጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ወዲህ በፌዴራሉ መንግሥትና በህወሓት መካከል ለመጀመሪያ ጊዜ ፊት ለፊት ይካሄዳል የተባለው የሠላም ንግግር በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ ከማንም ወገን የወጣ መረጃ የለም።

ተደራዳሪዎቹ ደቡብ አፍሪካ ከደረሱ በኋላ ያለውን ሁኔታ በተመለከተም ከአፍሪካ ኅብረትም ቢሆን በይፋ የተሰጠ መረጃ እስካሁን የለም።

ሆኖም የዛሬው መርኃ ግብር አደራዳሪዎቹ ስለ ውይይቱ አካሄድ ስልት ለመንደፍ የሚገናኙበት እንደሆነ የደቡብ አፍሪካ የመገናኛ ብዙኃን ቅርበት ያላቸው ያሏቸውን ምንጮች ጠቃቅሰው ዘግበዋል።

ንግግሮቹ በይፋ የሚጀመሩት ነገ፤ ማክሰኞ እንደሆነ የጠቆሙት እነዚሁ መገናኛ ብዙኃን የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥትና ህወሓት በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ቢያንስ ግጭት የማቆም ሥምምነት ላይ እንዲደርሱ አደራዳራዎቹ ተስፋ ማድረጋቸውንም ዘግበዋል።

ስለሰላም ንግግሩ አስተያየታቸውን የጠየቅናቸው የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ቃል አቀባይ ኤባ ካሎንዶ አዲስ መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል፤ ይልቅ ባለፈው ሃሙስ ወደሰጡን ምላሽ መርተውናል። ይኸውም “ኅብረቱ የሁለቱን አካላት የሰላም ንግግር ለማስጀመር በሂደት ላይ መሆኑን” አረጋግጠው “ዝርዝሩን እንደአስፈላጊነቱ ከተወያዮቹ ጋር በመመካከር እናቀርባለን” የሚል ነው።

የኢትዮጵያ መንግሥትና ህወሓትም ስለድርድሩ መጀመር አለመጀመር እስካሁን የገለፁት ነገር የለም። ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ መንግሥት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራና ዶ/ር ጌድዮን ጢሞቲዎስ፣ አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ አምባሳደር ሃሰን አብዱልቃድር፣ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ ጀኔራል ብርሀኑ በቀለና ዶ/ር ጌታቸው ጀምበር በአባልነት የተካተቱበት ተደራዳሪ ቡድን ማቋቋሙን ከዚህ ቀደም ማሳወቁ አይዘነጋም። ህወሓት በበኩሉ በጄነራል ፃድቃን ገብረትንሳይ እና በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራ ተዳራዳሪ ቡድን ማቋቋሙን መግለፁ ይታወሳል።

በተያያዘ ዜና የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ስለ ድርድሩ ከኬንያው ፕሬዚዳንት ዊልያም ሩቶና ከደቡብ አፍሪካ የዓለምአቀፍ ግንኙነቶችና ትብብር ሚኒስትር ናሌዲ ፓንዶር ጋር ትላንት ተነጋግረዋል።

ሚስተር ብሊንከን ከውይይቶቻቸው በኋላ ባወጧቸው ትዊቶች “ከኬንያ ፕሬዚዳንት ዊልያም ሩቶ ጋር ዛሬ ተነጋግረናል፤ በኢትዮጵያና በቀጣናው ሠላምና ደኅንነት ጉዳይ ላይ እርሳቸው ስላላቸው ቁልፍ ሚና አድንቄአቸዋለሁ” ብለዋል።

ከናሌዲ ፓንዶር ጋር ያደረጉትን ንግግር በተመለከተ ደግሞ “ከደቡብ አፍሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፓንዶር ጋርም የኢትዮጵያ የሠላም ንግግሮች በሚሳኩባቸው ሁኔታዎች ላይ ተወያይተናል። ደቡብ አፍሪካ በድርድሮቹ ውስጥ ስላላት ጠቃሚ ሚናም አመስግኛቸዋለሁ” ብለዋል።

የኬንያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታና የደቡብ አፍሪካ የቀድሞ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፉምዚሌ ምላምቦ-ንጉካ የአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይና የናይጄሪያ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ድርድሩን እንደሚመሩ ተነግሯል።

በሌላ በኩል፣ “ዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ሕብረትን በመደገፍ በዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ላይ በሙላትና በንቃት ትሳተፋለች” ያሉት በተመድ የሀገሪቱ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ ደግሞ “የዚህን ግጭት እልባት በሚያደናቅፉ አካላት ላይ ተገቢውን እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ ነን” ሲሉም ትዊት አድርገዋል።

የካቶሊካዊት ቤተክርስትያን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፍራንሲስ ደግሞ “በኢትዮጵያ እየቀጠለ ያለውን የግጭት ሁኔታ በጭንቀት እየተከታተልኩ ነው” ብለዋል። ተፋላሚ ወገኖች "ለውይይት የሚያደርጉት ጥረት ወደ እውነተኛ የዕርቅ መንገድ የሚመራቸው ይሁን” ሲሉ ምኞታቸውን የገለፁት አቡነ ፍራንሲስ “ፀሎታችን፣ አጋርነታችንና አስፈላጊው ሰብዓዊ እርዳታ ኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችንን አይለያቸው” ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከካናዳው አቻቸው ጋር መወያየታቸውን ገልፀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ከጓደኛዬ ከካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነታችንን ማጠናከርን ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውጤታማ የስልክ ውይይት አድርጊያለሁ” ሲሉ በማኅበራዊ መገናኛ ገፆቻቸው ገልፀዋል። ይሁን እንጂ ስለተወያዩባቸው ጉዳዮች በዝርዝር የጠቀሱት ነገር የለም።

በሌላ ዜና በትግራይ ክልል በተደረገው ጦርነት “በአሥሮች የሚቆጠሩ ሴቶችና ልጃገረዶች ተደፍረዋል” በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች ደግሞ ተገድለዋል” ሲል የክልሉ የድንገተኛ አደጋ ማስተባበሪያ ማዕከል መግለፁን አሶሲየትድ ፕረስ ዘግቧል።

ኤፒ፣ ከክልሉ በተጨማሪ የተመድ ተቋማትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም የተካተቱበት ያለው ይሄው ተቋም ያዘጋጀው ሰነድ “በሽራሮ ከተማ ዕድሜያቸው ከ13 እስከ 80 የሆኑ ወደ 40 የሚጠጉ ልጃገረዶች እና ሴቶች እንደተደፈሩ ይገልፃል” ብሏል። “ሰነዱ ጥቃቱ በማንና መቼ እንደተፈፀመ አይገልፅም” ያለው አሶሲትድ ፕረስ በትግራይ ክልል ታህታይ አዲያቦ፣ ደደቢትና ፀለምቲ አካባቢዎች 159 ሰዎች በጥይት መገደላቸውም በሰነዱ መካተቱን አመልክቷል።

“በነዚህ አካባቢዎች የኢትዮጵያና የኤርትራ መከላከያ ኃይሎች በአየር ጥቃትና በከባድ መሳሪያ ድብደባ ብዙ ሲቪሎችን ገድለዋል” ሲል ህወሃት በተደጋጋሚ መክሰሱ ይታወሳል። ይሁን እንጂ “የአየር ኃይሉን ጨምሮ የመከላከያ ሠራዊቱ ሰላማዊ ሰዎችን ዒላማ አያደርግም” ሲል በተደጋጋሚ ያስተባበለው የኢትዮጵያ መንግሥት ህወሓት ሲቪሎችን እንደጋሻ ይጠቀማል ሲል ይከስሳል።

በመሆኑም ሰላማዊ ሰዎችና የረድዔት ሠራተኞች በህወሓት ይዞታ ሥር ካሉ ወታደራዊ ዒላማዎችና አካባቢዎቻቸው እንዲርቁ ያሳሰበው ፌዴራሉ መንግሥት በሲቪሎችና በረድዔት ሠራተኞች ላይ የተፈፀመ ጥቃት ካለ መርምሮ እርምጃ እንደሚወስድ መግለፁ ይታወሳል።

በሌላ በኩል በአሜሪካ የአማራ ማኅበር ባለፈው ሣምንት ባወጣው ሪፖርት የትግራይ ክልል አዋሳኝ በሆነው በአማራ ክልል ቆቦ አካባቢ “የህወሓት ታጣቂዎች ካለፈው ነኀሴ ጀምሮ በትንሹ 193 ሲቪሎችን ገድለዋል፤ 143 ሴቶችን እና ልጃገረዶችን ደፍረዋል” ማለቱንም አሶሲየትድ ፕረስ በዘገባው አካትቷል።

ይሁን እንጂ ታጣቂዎቹ “በሲቪሎች ላይ የመብቶች ጥሰት ይፈፅማሉ” በሚል የሚቀርቡ ውንጀላዎችን ህወሓት በተደጋጋሚ ማስተባበሉ ይታወቃል።

[ሙሉውን ዘገባ ከተያያዘው ፋይል ያገኛሉ]

XS
SM
MD
LG