በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ብሊንከን ስለኢትዮጵያ ጉዳይ ከፕሬዚዳንት ሩቶና ከደቡብ አፍሪካ ሚኒስትር ጋር ተነጋገሩ


ፎቶ ፋይል፦ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን
ፎቶ ፋይል፦ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ከሰዓታት በኋላ ይጀመራል ተብሎ በሚጠበቀው የሠላም ድርድር ጉዳይ ላይ ከኬንያው ፕሬዚዳንት ዊልያም ሩቶና ከደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ፣ የዓለምአቀፍ ግንኙነቶችና ትብብር ሚኒስትር ናሌዲ ፓንዶር ጋር ዛሬ ተነጋግረዋል።

ሚስተር ብሊንከን ከውይይቶቻቸው በኋላ ባወጧቸው ትዊቶች “ከኬንያ ፕሬዚዳንት ዊልያም ሩቶ ጋር ዛሬ ተነጋግረናል፤ በኢትዮጵያ አካባቢያዊ ሰላምና ደኅንነት ጉዳይ ላይ እርሳቸው ስላላቸው ቁልፍ ሚና አድንቄአቸዋለሁ” ብለዋል።

ከናሌዲ ፓንዶር ጋር ስላደረጉት ንግግርም “ከደቡብ አፍሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፓንዶር ጋርም የኢትዮጵያ የሠላም ንግግሮች በሚሳኩባቸው ሁኔታዎች ላይ ተወያይተናል። ደቡብ አፍሪካ በድርድሮቹ ውስጥ ስላላት ጠቃሚ ሚናም አመስግኛቸዋለሁ” ብለዋል።

የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ዛሬ ባወጡትና በመሥሪያ ቤቱ ዌብ ሳይት ባሠፈሩት ፅሁፍ ብሊንከን ከፕሬዚዳንት ሩቶ ጋር በተነጋገሩበት ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥና በመላ ምሥራቅ አፍሪካ ሠላምና ደኅንነት ጉዳይ ላይ ‘ኬንያ አላት’ ባሉት ቁልፍ ሚና ላይ የተወያዩ ሲሆን የፊታችን ታኅሣስ ውስጥ ዋሺንግተን ላይ በሚደረገው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በጠሩት የዩኤስ-አፍሪካ መሪዎች ጉባዔንም መመርመራቸውን የቃል አቀባዩ መግለጫ አመልክቷል።

በሌላ በኩል “ሚኒስትሩ [አንተኒ ብሊንከን] ባለፈው መስከረም 6/2015 ዓ.ም. የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፖሳና ፕሬዚዳንት ባይደን ዋሺንግተን ዲሲ ላይ ያካሄዱትን ፍሬያማ ስብሰባ ተከትሎ በደቡብ አፍሪካና በዩናይትድ ስቴትስ መካከል በመላ የጋራ ጥቅም ጉዳዮቻቸው ላይ ጠንካራ ትብብራቸውን በድጋሚ አረጋግጠዋል” ይላል የቃል አቀባዩ ቢሮ መግለጫ።

XS
SM
MD
LG