በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ተደራዳሪዎቹ ደቡብ አፍሪካ ገብተዋል


የኢትዮጵያ ካርታ
የኢትዮጵያ ካርታ

በኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥትና በህወሓት መካከል ነገ፤ ሰኞ ይጀመራል ለተባለው የሠላም ንግግር የሁለቱም ወገኖች ተደራዳሪዎች ደቡብ አፍሪካ መግባታቸው እየተሰማ ነው።

ምንም እንኳ ድርድሩ የሚካሄድበት ትክክለኛ ቦታና ሰዓት በጥብቅ ምሥጢር የተያዘና እስካሁንም ያልተገለፀ ቢሆንም የህወሓት ቃል አቀባይ ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረህይወት ዛሬ ባወጡት ትዊት ተደራዳሪዎቻቸው ደቡብ አፍሪካ መግባታቸውን አስታውቀዋል።

“በአፍሪካ ኅብረት በሚመራው የኢትዮጵያ ትግራይ የሠላም ንግግር ላይ ለመገኘት የትግራይ መንግሥት ልዑካን ቡድን ደቡብ አፍሪካ ገብቷል” ብለዋል።

ቃል አቀባዩ በዚሁ ትዊታቸው ላይ አክለውም “እጅግ አንገብጋቢ ጉዳዮች” (Pressing) ሲሉ ባሠፈሩት ዝርዝር “ፀቡ [ውጊያ] ፈጥኖ እንዲቆም፣ ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦትና የኤርትራ ኃይሎች መውጣት” ብለዋል። ይሁን እንጂ እነዚህ ነጥቦች ቅድመ ሁኔታ ይሁኑ አይሁኑ የጠቆሙት ነገር የለም።

ፕሮፌሰር ክንደያ ትዊታቸውን የዘጉት “ወታደራዊ መፍትኄ ሊኖር አይችልም” በሚል መልዕክት ነው።

ከህወሓት ተደራዳሪዎች መካከል ጄነራል ፃድቃን ገብረትንሳይ እና አቶ ጌታቸው ረዳ እንደሚገኙበት ተዘግቧል።

ይህ ዜና እስከተጠናቀረበትና እስከወጣበት ደቂቃ ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል የተሰማ የመጨረሻ ይፋ መረጃ ወይም መግለጫ ባይኖርም የተደራዳሪው ቡድን አባል እንደሚሆኑ ቀደም ሲልም ተገልፆ የነበረው የብሄራዊ ፀጥታና ደኅንነት አማካሪው አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ሃሙስ፣ ጥቅምት 10/2015 ዓ.ም. ባወጡት ትዊት ድርድሮቹ ጥቅምት 14/2015 እንዲካሄዱ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን እንዳሳወቃቸው ጠቁመው ለመሳተፍም ያላቸውን ቁርጠኛነት በድጋሚ ማረጋገጣቸውን አመልክተዋል።

አምባሳደር ሬድዋን በዚሁ ትዊታቸው ላይ አያይዘው በስም ያልጠሯቸውና “አንዳንድ” ያሏቸው “ከሰላም ንግግሮች አፈንግጠው በመከላከያ እርምጃዎቹ ላይ የሃሰት ክሶችን መንዛታቸው አስደምሞናል” ብለዋል።

የድርድሩ ነጥቦችና ጭብጦች ምን ሊሆኑ እንደሚችሉ እስካሁን የወጣ መረጃ የለም።

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ዩናይትድ ስቴትስን በእጅጉ እንደሚያሳስባት የተናገሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ አንተኒ ብሊንከን የሰኞው የደቡብ አፍሪካ ድርድር በቅን መንፈስ እንዲካሄድ ጥሪ አድርገው ተኩስ በአስቸኳይ እንዲቆም፣ ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት እንዲኖር፣ የኤርትራ ኃይሎች ከሰሜን ኢትዮጵያ እንዲወጡ ማሳሰባቸውን ቃል አቀባያቸው ኔድ ፕራይስ ገልፀዋል።

ከአፍሪካ ኅብረት በይፋ የተሰጠ መግለጫ እስካሁን የለም።

በድርድሩ ዙሪያ የሚኖሩና የሚደርሱንን የመጨረሻ መረጃዎች በቅርበት እየተከታተልን ፈጥነው እንዲደርሷችሁ እየጣርን ነው።

XS
SM
MD
LG