በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ መዘዝ እየተባባሰ ነው


አቶ ነጋሽ ተክሉ፦የኢትዮጵያ ሥነ ህዝብ፣ ጤናና አካባቢ ጥበቃ ጥምረት /ፒኤችኢ/ ዋና ዳይሬክተር
አቶ ነጋሽ ተክሉ፦የኢትዮጵያ ሥነ ህዝብ፣ ጤናና አካባቢ ጥበቃ ጥምረት /ፒኤችኢ/ ዋና ዳይሬክተር

ኢትዮጵያ ውስጥ በድርቅ ይጠቁ የነበሩ የተለያዩ አካባቢዎች ሰሞኑን በጣለው ከባድ ዝናብ በጎርፍ ተጥለቅልቀዋል። በነዚህ የጎርፍ አደጋዎች የበርካቶች ህይወት ሲጠፋ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት(OCHA) በነሀሴ ወር ባወጣው ሪፖርት በያዝነው ክረምት እያጣለ ያለው ከባድ ዝናብ በሚያስከትለው ጎርፍ፣ ከ2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች እንደሚጠቁ አስታውቋል። የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎች የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለው ያለው ተደጋጋሚ የድርቅና የጎርፍ አደጋ በህብረተስቡ ላይ ትልቅ ተፅእኖ እያደረሰ እንደሆነ ጠቁመው፣ መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል ።

በደቡብ ክልል፣ ኦሞ ዞን፣ ዳሰነች ወረዳ፣ የኦሞ ወንዝ ውሃ ሞልቶ በመጥለቅለቁ ከቤት ንብረታቸው ከተፈናቀሉ ከ43 ሺህ በላይ ሰዎች መሀከል አንዱ ጆን ሎማላ ነው። በዳሰነች ወረዳ ከሞራቴ አካባቢ ተወልዶ ያደገው ጆን እንደአብዛኛው የአካባቢው ህብረተሰብ በከብት እርባታና አሳ ማስገር ይተዳደር ነበር። ባለፈው ሚያዚያ በላይኛው የኦሞ ሸለቆ አካባቢዎች የጣለው ከባድ ዝናብ ባደረሰው የጎርፍ አደጋ ግን እሱና ቤተሰቦቹ የመኖሪያ አካባቢያቸውን ሸሽተው በኬንያ ድምበር አካባቢ ተጠልለው ይገኛሉ።

ከሚያዚያ ጀምሮ የጣለው ከፍተኛ ዝናብ ያስከተለው የወንዝ መጥለቅለቅ በዳሰነች ወረዳ ዙሪያ በሚገኙ 20 ደሴቶችና 19 ቀበሌዎች ላይ ጉዳት ሲያደርስ፣ 43 ሺህ 670 ሰዎችን ደግሞ አፈናቅሏል። በደሴቶቹ ላይ ይኖሩ የነበሩ ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉ ከብቶችም አደጋ ላይ ናቸው። ይህ ከፍተኛ ዝናብ ያስከተለው የጎርፍ አደጋ በአካባቢው በ30 አመት ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ እንደሆነ የነገሩን የወረዳዋ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቀብራራው ተክሌ ናቸው።

ከድንገተኛ የጎርፍ አደጋው ጎን ለጎን በየጊዜው እየተባባሰ የሚሄደው የአየር ንብረት ለውጥ በከብት እርባታ የሚተዳደረውን የህብረተሰብ ክፍል ለግጦሽ መሬት እጦት ይዳርገዋል። በዳሰነች ወረዳ የግጦሽ መሬት በድርቅ ምክንያት በሚራቆትበት ወይም በውሃ በሚጥለቀለቅበት ወቅት ህብረተሰቡ የግጦሽ መሬት ፍለጋ የሚደረገው ጥረትም በኬንያ ድምበር ክልል ካለው የቱርካና ህብረተሰብ ጋር እንደሚያጋጫቸው ጆን ይናገራል።

የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት (OCHA) ባለፈው ሳምንት ያወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ከሐምሌ ወር አጋማሽ ጀምሮ በአፋር፣ በጋምቤላ፣ ኦሮሚያ እና ደቡብ ክልሎች በተከሰተ ጎርፍ 30 ሺህ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል። በተለይ የአዋሽ ወንዝ ሙላት በአፋር ክልል ባደረሰው አደጋ ወደ 20 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች መፈናቀላቸውን መረጃው ያሳያል።

ይህ መሰሉ ያልተለመደ ከፍተኛ ዝናብና ጎርፍ በኢትዮጵያ ውስጥ የአየር ንብረት ለውጥ ከሚያደርሳቸው ተፅእኖዎች አንዱ መሆኑን የኢትዮጵያ ስነ-ህዝብ፣ ጤናና አካባቢ ጥበቃ ወይም በምፅህረ ቃሉ ፒ ኤች ኢ ኢትዮጵያ በመባል የሚታወቀው ጥምረት ዋና ዳይሬክተር አቶ ነጋሽ ተክሉ ያስረዳሉ።

አለማችን ከመቼውም ግዜ በላይ እየሞቀች ነው። ይህ የሙቀት መጠን መጨመር ደግሞ በርካታ ስጋቶችን ፈጥሯል። አቶ ነጋሽ የከባቢ አየር ሙቀት መጨመር እያስከተለ ያለው የአየር ንብረት ለውጥ በኢትዮጵያ የግብርና ምርት ላይ ስጋት ለደቀነው የአምበጣ መንጋ መፈልፈል አመቺ ሁኔታ ከመፍጠር አንስቶ የህዝቡን የኑሮ ዋስትና የሚፈታተኑ በርካታ አደጋዎችን እንደደቀነ ያስረዳሉ።

በአንድ ወቅት በደን ተሸፍነው የነበሩት የኢትዮጵያ ተራራማ ቦታዎች በህዝብ ብዛት ቁጥር መጨመርና ያንን ተከትሎ በሚመጡ የእርሻ መስፋፋቶች አሁን ተራቁተዋል። ህልውናዋ ከተፈጥሮ ሀብት ለተያያዘው ኢትዮጵያ ይህ ትልቅ ስጋት ነው የሚሉት አቶ ነጋሽ፣ ሀገሪቱ የአየር ንብረትን ለመዋጋት የተፈጥሮ ጥበቃ ላይ ማተኮር እንዳለባት ይመክራሉ።

ጆንና ሌሎች ከዳሰነች የተፈናቀሉ ህብረተሰቦች በመንግስት እርዳታ እየተደረገላቸው ቢሆንም፣ የህውናቸው መሰረት ለሆኑት ከብቶቻቸው የግጦሽ መሬት ማግኘት ግን አሁንም ያሳስባቸውል። ለዛም ነው አቶ ነጋሽ በአንድ ወቅት የአየር ንብረት ለውጥን ለመግታት በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚደረጉ በርካታ ድርድሮች ላይ አፍሪካን ወክላ ትሳተፍ የነበረችው ኢትዮጵያ ዘላቂ ልማት ማምጣት የምትችለው የተፈጥሮ ሀብትን መንከባከብ ላይ መሰረት ያደረገና የተቀናጀ ፓሊሲን መተግበር ከቻለች ብቻ ነው ሲሉ የሚመክሩት።

ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።

በኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ መዘዝ እየተባባሰ ነው
please wait

No media source currently available

0:00 0:08:57 0:00


XS
SM
MD
LG