በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ባይደን፣ የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ እና የውጭ ፖሊሲያቸው


የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን

ፕሬዚዳንት ባይደን በነገው እለትና ከነገ በስቲያ የሚካሄደውን የአፍሪካ ህብረት 34ኛውን፣ የመሪዎች ጉባኤ አስመልክቶ በዛሬው እለት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ በመልዕክታቸው አስተዳደራቸው ከአፍሪካ ህብረት ጋር ኮቪድ 19 ወረርሽኝና የጸጥታ ጉዳዮችን ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች አብረው እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

በሌላም በኩል ፕሬዚዳንት ባይደን ትናንት ሀሙስ፣ የዩናይትድ ስቴትስን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዋና መሥሪያ ቤት በመጎብኘት ለአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ያላቸውን ራዕይ ይፋ አድርገዋል፡፡

በየመን ለሚካሄደው የወታደራዊ ዘመቻ ጥቃት፣ የናይትድ ስቴትስ የምታደርገውን ድጋፍ እንድታቋርጥ በማዘዝ፣ አጠቃላይ ፖሊሲውም ወደ ዴፕሎማሲው መርህ እንዲቀየር አሳሰበዋል፡፡

ለአፍሪካ ህብረት ጉባኤ

“ጤና ይስጥልኝ ለሁላችሁም፤ ለመጭው የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ የዩናይትድ ስቴትስ ህዝብ የላቀ ምኞት ስገልፅላችሁ ኩራት ይሰማኛል።”

ባይደን ለአፍሪካ ህብረት 34ኛውን የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ ባስተላለፉት መልዕክታቸው መግቢያ ላይ ነበር ይህን ያሉት፡፡

አያይዘውም “ይህ ያሳለፍነው ዓመት ያሳየን ነገር ቢኖር ዓለማችን ምን ያህል የተገናኘች መሆኑን ነው፡፡ እጣችን እንዴት የተሳሳረ እንደሆነ አይተንበታል፡፡ የኔ አስተዳደር በዓለም ላይ ያለውን ትብብር መልሶ ለማጠንከር ፣ እንደ አፍሪካ ህብረት ካሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር መልሶ ለመገናኘት ቆርጦ መነሳቱም” ለዚህ ነው በማለት ተናግረዋል፡፡

“የወደፊት ተስፋችንን እውን ለማድረግ ሁላችንም አብረን መስራት ይኖርብናል” ያሉት ባይደን ፣ ለምን አብሮ መስራት እንደሚገባም ሲያስረዱ ይህን ብለዋል

“ለሃገሮቻችን ሁሉ ብልፅግናን የሚያራምድ የአዳጊ ንግድና መዋዕለ ነዋይ መፃዒ ጊዜ፤ ለዜጎቻችን ሁሉ የሰላምና የደኅንነትን ህይወት የሚያበዛ መፃዒ ጊዜ፤ በዴሞክራሲያዊ ተቋሞቻችን ላይና ለሁሉም ሰዎች ሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ፣ ለሴቶችና ልጃገረዶች፣ ለተመሣሣይ ፆታ ፍቅረኞች ወይም ፆታቸውን ለለወጡ ግለሰቦች፣ የአካል ጉዳይ ላለባቸውና የማንም ጎሣ አባል ለሆኑና የቱንም ዓይነት አመጣጥ ላላቸው ሁሉ ሃብትና አቅማችንን የምናፈስበት መፃዒ ጊዜ ይሆናል፡፡”

“ካሰብንበት ለመድረስ እነዚህን የገጠሙንን ፈነታዎች ሁሉ መቋቋም ይኖርብናል” ያሉት ባይደን በዓለም ጤና ላይ ኢንቨስት ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ መግታትና መከላከልን ጨምሮ የወደፊቱ የጤና ቀውስ የሆኑትን ለይቶ ለማወቅና ምላሽ ለመስጠት እንደሚገባ አስታውሰው፣ ለዚህም መንግሥታቸው ከአፍሪካ የበሽታዎች ቁጥጥርና መከላከል ማዕከል እና ከሌሎች ተቋማት ጋር በመተባበር እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

የአየር ንብረትን ለማሻሻል አስመልክቶ ያለውን ህልም ለማሳካትና እስካሁን ያለው፣ ብክለት ያደረሰውን ጉዳት ለማሻሻል፣ ከታዳጊ አገሮች ጋር እንደሚሰሩም አስታውቀዋል፡፡

በአፍሪካ የሰዎችን ህይወት በመቅጨት ላይ ያሉትን ግጭቶች ሁሉ ለማስወገድ የሚቻልበትን ዘላቂ የሆኑ ዲፕሎማሲን ለማስፈን ከአፍሪካ ህበረት ጋር በመነጋገር እንደሚሰሩም ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡፡፡

ባይደን እነዚህ የዘረዘሯቸው ነገሮች በሙሉ በቀላሉ የሚከናውኑ አለመሆናቸውን በመግለጽ በንግግራቸው ማጠቃለያ የሚከተለውን ብለዋል

"ከእነዚህ አንዱም ቢሆን እንኳ ቀላል አይደለም፤ ይሁን እንጂ ዩናይትድ ስቴትስ ከእናንተ ጋር በአጋርነት ለመቆምና ለጋራ መከባበር ዝግጁ ሆና ትገኛለች።

እጅግ የሰፋ የሥራ ፈጠራና አዲስ ነገር አፍላቂነት ባለባቸው በአፍሪካ ሃገሮች ላይ እምነት አለን።

ፈተናዎቹ እጅግ የገዘፉ ቢሆኑም፣ ሃገሮቻችን፣ ህዝቦቻችንና የአፍሪካ ኅብረት ይጋፈጧቸው ዘንድ ብቃቱ አላቸው።

በሚቀጥለው ጉባዔያችሁ ላይ በአካል እገኛለሁ የሚል ተስፋ አለኝ። ለአሁን ላመሰግናችሁ እሻለሁ። አመሰግናለሁ።

አምላክ ሁላችሁንም ይባርክ!

ባይደን፣ የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ እና የውጭ ፖሊሲያቸው
please wait

No media source currently available

0:00 0:08:22 0:00

“አሜሪካ ተመልሳለች፤ ዲፕሎማሲ ተመልሷል”

በሌላም በኩል ትናንት ሀሙስ፣ የዩናይትድ ስቴትስን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዋና መሥሪያ ቤት የጎበኙት፣ ፕሬዚዳንት ባይደን በአሜሪካም ሆነ በመላው ዓለም ለሚገኙ የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዲፕሎማቶችና ሠራተኞች እንዲህ የሚልአስቸኳይ መልዕክት ነበራቸው፡፡

“አሜሪካ ተመልሳለች፡፡ ዲፕሎማሲ ተመልሷል፡፡ መስራት ለምፈልገው ነገር ሁሉ ምሶሶው እናንተ ናችሁ፡፡

ባይደን በሳኡዲ አረብያ መሪነት በየመን የእርስ በርሱ ጦርነት ለሚደረገው ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት፣ በቀድሞ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ይሰጥ የነበረውን ድጋፍ እንዲቀለበስ አድርገውታል፡፡

“ይህ ጦርነት መቆም አለበት፡፡ የገባነውን ቃልም ተግባራዊ ለማድረግ ከየመን ጦርነት ጋር የተያያዘውን ወታደራዊ የመሣሪያ ሽያጭን ጨምሮ፣ በየመን በሚካሄዳው ጦርነት፣ አሜሪካ ለወታደራዊ የጥቃት ዘመቻው የምትስጠውን ድጋፍ ሁሉ እያቋረጥን ነው፡፡

ባይደን የየመን ጉዳይ የሚከታተል፣ የዩናትይትድ ስቴትስ ልዩ መልከተኛ ያቋቋሙ ሲሆን፣ የብዙ ዘመን አገልግሎት ያላቸውን ድፕሎማት ቲም ሌንደርኪንግን ሥራውን እንዲመሩ ሰይመዋል፡፡

ሴንተር ኦፍ አሜሪካን ፕሮግረስ ከሚባል ተቋም ብራያን ካቱሊስ ይህ ትልቅ ለውጥ መኖሩን ያሳያል ይላሉ፡፡

“በዚያ ቦታ የዩናይትድ ስቴትስ ዲፕሎማትን መመደብ ማለት ትልቅ መልእክት የሚያስተላልፍ ይመስለኛል፡፡ አሜሪካ ከልቧ ግጭቱ እንዲያበቃ የምትፈልግና አንድ ለውጥ እንዲኖር ቁርጠኝነቱ ያላት ይመስለኛል፡፡”

ባይደን በግጭትና ዕልቂት ከታመሱ እንደ የመን ካሉት አገሮች የሚመጡ ስደተኞችን አስመልክቶ የሚያስታውቁት ሌላ አንድ ትልቅ ዜናም ነበራቸው፡፡

“ከዚህ በፊት በዓለም ላይ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ የተከስተውን ፍላጎት ለማሟላት፣ ስደተኞችን የመቀበል ፕሮግራማችንን መልሶ የመገንባቱ ከባድ ሥራ እንዲጀመር የአፈጻጸም ትዕዛዝ አውጥቻለሁ፡፡”

ባይደን በማይነማር የተካሄደውን ወታደራዊ መፈንቀል መንግሥትም አውግዘዋል፡፡ ወታደሮቹ ሥልጣን እንዲለቁና ሲቪል መሪዎችንም እንዲፈቱ የኢንተርኔት አገልግሎትን መልሰው በመልቀቅ ግንኙነቱን ክፍት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ በመላው ዓለም ያሉ የዩናይትድ ስቴትስ ወታደራዊ ኃይሎችን ሁኔታ እንዲቃኝ ያዘዙ ሲሆን፣ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የዩናይትድ ስቴትስ ወታደሮች ከጀርመን ለቀው እንዲወጡ የሰጡትን ትዕዛዝ እንዲገታ አዘዋል፡፡

ከሴንተር ኦፍ አሜሪካን ፕሮግረስ ብራየን ካቱሊስ፣ በቀድሞ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ይወስዷቸው ከነበሩት ያልተለመዱ እርምጃዎች አንጻር፣ የባይደን ውሳኔዎች ለጀርመንና የአሜሪካ የቅርብ አጋር ለሆኑ የአውሮፓ አገራት መተማመኛን ይሰጣል፡፡ እንዲህ ብለዋል ብራያን

“እና ደግሞ እንደሚመስለኝ ይህ ውሳኔ፣ የሚያደርገው ነገር ቢኖር፣ የአሜሪካንን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ፣ ከዩናይትድ ስቴትስ አጋሮች፣ በተለይም ዲሞክራሲያዊ ከሆኑ አገራት ጋር፣ በቅርበትና ተባብሮ መሥራት ወደ ተመለደበት የቀደመው አሠራር የሚመልሰው ይመስለኛል፡፡”

ፕሬዚዳንት ባይደን ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሠራተኞች ሲናገሩ፣ ሙያዊ አስተዋጽኦቸውን እንድሚያከብሩና በግል እንደማያጠቋቸው፣ በሥራቸውም ያልተገባ ፖሊካዊ ትርጉም እንደማይሰጧቸው ገልጸውላቸዋል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ለአፍሪካ ህብረት ያስተላለፉት መልዕክት
please wait

No media source currently available

0:00 0:02:14 0:00


XS
SM
MD
LG