(ሙሉ ዘገባውን ከላይ ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያገኛሉ)
ተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ሥልጣን እየተመለሱ ባሉበት ወቅት ከአፍሪካ ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት በተለይ ከፀጥታ እና ደህንነት ትብብር አንፃር ምን ሊመስል ይችላል የሚለው ጥያቄ ጎልቶ ይነሳል። አፍሪካ ለአሜሪካ ቀዳሚ የፖለቲካ፣ የደህንነት እና የስትራቴጂ አቅጣጫ አለመሆኗን የሚገልጹት የአፍሪካ ጉዳይ ተንታኞች፣ ትራምፕ በአፍሪካ ላይ ያላቸው ትኩረት እንደ ሩሲያ እና ቻይና ያሉ ሀያል ሀገራትን በመገዳደር ላይ የተመሰረተ ሊሆን እንደሚችል አመልክተዋል።
የአፍሪካ ቀንድ
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለሁለተኛ ጊዜ ወደስልጣን ለመመለስ እየተዘጋጁ ባሉበት ወቅት፣ በቀደመው የስልጣን ዘመናቸው በአፍሪካ የሳህል ቀጠና ልዩ መልዕክተኛቸው አድርገው ሾመዋቸው የነበሩትን ፒተር ፓም፣ የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አድርገው ሊሾሟቸው እንደሚችሉ እየተገለፀ ነው። ፒተር ፓም ደግሞ ከሶማሊያ ተገንጥላ በራስ ገዝ አስተዳደር የምትመራው ሶማሌላንድ እንደሀገር እውቅና እንድታገኝ ተሟጋች መሆናቸው ይነገራል።
በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የአፍሪካ እና እስያ ጥናት እና ምርምር ማዕከል ተባባሪ ፕፎፌሰር የሆኑት ዶክተር ሳሙኤል ተፈራ እንደሚያስረዱት፣ የሶማሌላንድ ጂኦፖለቲካል አቀማመጥ፣ አሜሪካ በቀይ ባህር ዙሪያ ላላት ፍላጎት አመቺ ስለሚሆን አዲሱ የትራምፕ አስተዳደር ለሶማሌላንድ እውቅና ሊሰጥ የሚችልበት እድል እንዳለ ያመለከታሉ።
አሜሪካ በሶማሊያ ሰላምና መረጋጋትን ለመፍጠር እና ሽብርተኝነትን ለመከላከል፣ ለረጅም ጊዜ ስትከተል የቆየችውን 'አንድ ሶማሊያ' ፖሊሲ የምትቀርይርበት እድል በጣም ጠባብ መሆኑን የሚገልጹት ደግሞ የአፍሪካ ቀንድ እና መካከለኛው ምሥራቅ ጉዳዮች ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር በለጠ በላቸው ናቸው። ዶክተር በለጠ ትራምፕ ይህን ፖሊሲ በመቀየር ለአሜሪካ የሚያስገኙት የተለየ ጥቅም እንደሌለ ያምናሉ።
ሶማሌላንድ እራሷን የቻለች ሀገር ሆና እውቅና ለማግኘት የሚያስችላት የቀይ ባህር ወደብ ከኢትዮጵያ ጋር መፈራረሟ፣ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል ለአንድ አመት የዘለቀ ውጥረትን ፈጥሮ ቆይቷል። ምንም እንኳን ሁለቱም ሀገራት ልዩነታቸውን በውይይት ለመፍታት ስምምነት ላይ ቢደርሱም፣ የእርስ በእርስ ጦርነቶች በተዛመቱበት የአፍሪካ ቀንድም ተጨማሪ ስጋት ደቅኖ ቆይቷል። ይህ የፖለቲካ አለመረጋጋት ለአሜሪካ እምብዛም የራስ ምታት ያልሆነ ሲሆን፣ በተለይ የትራምፕን ትኩረት እንደማያገኝ ዶክተር በለጠ ያሰምሩበታል።
በዚህ የሚስማሙት ዶክተር ሳሙኤልም በተለይ ኢትዮጵያን እንደምሳሌ ያነሳሉ። በኢትዮጵያ ለዓመታት የዘለቀው የጸጥታ እና ደህንነት ችግር ትራምፕ ቅድሚያ ለሚሰጡት የንግድ እና ኢንቨስትመንት ትብብር አመቺ አይሆንም ይላሉ።
ሱዳን
ሌላው የአፍሪካ ትልቁ ራስ ምታት ሁለት አመት ሊሞላው ጥቂት ወራት ብቻ የቀሩት የሱዳን ጦርነት ነው። የባይደን አስተዳደር የስልጣን ዘመናቸውን እያገባደዱ ባሉበት ወቅት፣ በሱዳኑ ፈጥኖ ደራሽ ኃይል መሪ መሀመድ ሃምዳን ዳጋሎ ሄሚት እና በጦር አዛዡ አብደል ፋታህ አል-ቡርሃን ላይ የተለያዩ ማዕቀቦችን ጥለዋል። የአፍሪካን የጸጥታ ጉዳዮች የሚከታተሉት ባለሞያዎች ግን ይህ ጦርነት ትራምፕን ብዙም ያሳስባቸዋል ብለው አያስቡም። ሆኖም በቀደመው የትራምፕ ስልጣን ዘመን ከኬንያ ጋር የነበራቸውን ትስስር በመመልከት፣ ኬንያ በአፍሪካ ቀንድ የሰላም እና ደህንነት ተፅእኖ ፈጣሪ ሊያደርጓት ይችላሉ ይላሉ።
ምዕራብ አፍሪካ
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በርካታ መፈንቅለ መንግስቶች በተካሄዱበት ምዕራብ አፍሪካ የተመሰረቱት ወታደራዊ መንግስታት ከምዕራቡ ዓለም ጋር ያላቸውን ግንኙነት እያቋረጡ ይገኛሉ። ዩናይትድ ስቴትስም በኒጀር የነበሯትን ሁለት የጦር ካምፖች ዘግታ እንድትወጣ ተደርጋለች። ሽብርተኝነትን መዋጋት አሜሪካ ብቻ ሳትሆን አለም ትኩረት የሚሰጥበት ጉዳይ መሆኑን የሚያመለክቱት ዶክተር ሳሙኤል፣ ትራምፕ ከሌሎች የሳህል ሀገራት ጋር ትብብራቸውን ሊያስቀጥሉ ይችላሉ ብለው ይገምታሉ።
ዶክተር በለጠ በበኩላቸው፣ የትራምፕ አስተዳደር በምዕራብ አፍሪካ ለሚኖረው ትኩረት፤ ከአውሮፓ ሀገራት እና በተለይ ሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል-ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት ወሳኝ ይሆናል ይላሉ።
ምሁራኖቹ የሚስማሙበት ትልቁ ነጥብ፣ የአሜሪካ መንግስታት በአፍሪካ ላይ የሚከተሉት ፖሊሲ፣ ሌሎች ኃያል ሀገራት በአህጉሩ ላይ የሚኖራቸውን ተፅእኖ በመገዳደር ላይ የተመሰረተ መሆኑን ነው። በተለይ ደግሞ ትራምፕ፣ ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድ እና ቻይና የመሰረቱትን እና በኃላ ደቡብ አፍሪካ የተቀላቀለችውን የብሪክስ ቡድን እንቅስቃሴ ለመግታት ልዩ ፍላጎት እንደሚኖራቸው ዶክተር በለጠ ያሰምሩበታል።
አሜሪካ በኢኮኖሚ፣ ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ አቅም የጎለበተች ልዕለ ሀያል ሀገር ናት የሚሉት ተንታኞቹ፣ ሁሉም የአፍሪካ ሀገራት ከአሜሪካ ጋር ትስስር ለመፍጠር የሚያችላቸውን አቅም መመዘንና መዘጋጀት እንደሚኖርባቸው ያሰምሩበታል። በተለይ ደግሞ በአፍሪካ ህብረት ስር ወሳኝ የሆኑ ማዕቀፎችን ማራመድ የሚችሉበትን አቅም ሊገነቡ እንደሚገባም ይመክራሉ።
መድረክ / ፎረም