በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ገና በላሊበላ


ፎቶ ፋይል - ላሊበላ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጥር ጥር 7 2022 ዓ.ም የገና በዓል ሲከበር።
ፎቶ ፋይል - ላሊበላ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጥር ጥር 7 2022 ዓ.ም የገና በዓል ሲከበር።

የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት - ገና በዓል በልዩ ኹኔታ ከሚከበርባቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች በቀዳሚነት የምትጠቀሰው፣ በዐማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ላስታ ወረዳ የምትገኘው የላሊበላ ከተማ ናት።

በዩኔስኮ የሰው ልጆች ቅርስ ኾኖ የተመዘገቡት የ11 ውቅር አብያተ መቅደሶች መገኛዋ ላሊበላ፣ በገና በዓል ሰሞን፣ ዐያሌ የአገር ውስጥ እና የውጭ ጎብኚዎችንና ተሳላሚ ምእመናንን በሞቀ አቀባበል ታስተናግዳለች።

በዐማራ ክልል የቀጠለው በትጥቅ የተደገፈ ግጭት ከመቀስቀሱና ከመስፋፋቱ በፊት፣ ለክብረ በዓሉ ከተለያዩ ስፍራዎች ወደ ላሊበላ ከተማ የሚጎርፉት ጎብኚዎች ብዛት በሚሊዮኖች የሚቆጠር እንደነበር፣ የከተማዋ አስተዳደር መረጃ ያመለክታል።

የከተማዋ ነዋሪዎች፣ "ከወትሮው የተቀዛቀዘ ነው፤" ብለዋል። የሰሜን ወሎ ዞን ባህል እና ቱሪዝም መምሪያ ሓላፊ ገነት ሙሉጌታ ደግሞ፣ በዓሉ በተለመደው መልኩ እንዲከበር አስቀድመው ጥሪ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጸው፣ "በዓሉን የሚያከብሩ ሰዎች ወደ ከተማ እየገቡ ነው፤" ብለዋል። በተጨማሪም፣ የበዓሉን ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ይዘት የሚያስረዱ ባለሞያዎች በፕሮግራሙ ላይ መካተታቸውን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የባሕረ ሐሳብ ሊቃውንት፣ "ተረፍ/ተውሳክ" እያሉ የሚጠሯት ጳጉሜን የምትጨምረውን የቀናት ቁጥር ተከትሎ የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት - ገና፣ በየአራት ዓመቱ ታኅሣሥ 28 ቀን ከዚያ በቀር ግን ታኅሣሥ 29 ላይ ይውላል። ዘንድሮም፣ ነገ ታኅሣሥ 29 ቀን ይከበራል።

በኢትዮጵያ የክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ከሚከበሩት በዓላት፣ ገና በደማቅነቱ ይወሳል፡፡ ስያሜው፣ "ጌና" ከሚለው የግሪክ ቃል የተወረሰ ሲኾን፣ ትርጉሙም ልደት ማለት ነው። ቃሉ የአረብኛም መሠረት እንዳለውና ምስጋና፣ ብልጥግና የሚል ትርጉምም እንዳለው ሊቃውንቱ ያስረዳሉ።

በቤተ ልሔም የክርስቶስ መወለድ የተበሠረበት፣ መላእክት እና እረኞች በአንድነት ያመሰገኑበት፣ ሦስቱ የጥበብ ሰዎች እጅ መንሻ ያቀረቡበት ገናናው ገና፣ ከመንፈሳዊ ይዘቱ ባሻገር ያለው ማኅበራዊ እና ባህላዊ ክንዋኔው በብዙኀኑ ዘንድ ተናፋቂ እንደሚያደርገው ሊቃውንቱ ያስረዳሉ።

ከወጥ አለት የተፈለፈሉትን ዐሥራ አንዱን ውቅር አብያተ መቅደስ እንዳነፃቸው የሚታመነውና ከ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የዛጉዌ ነገሥታት አንዱ የነበረው የቅዱስ ላሊበላም ልደት፣ ታኅሣሥ 29 ቀን እንደሚከበር፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መዛግብት በሰሜን ወሎ አገረ ስብከት የደብረ ሮሃ የቅዱስ ላሊበላ ገዳም ጽ/ቤት የሕዝብ ግንኙነት ሓላፊ ዲያቆን ተስፋ ውቤ ገና ያስረዳሉ።

በላሊበላ የበዓለ ገና አከባበር፣ "ቤዛ ኩሉ" ተብሎ የሚጠራው በጠዋቱ የሚደረገው የሊቃውንቱ ዝማሬ፣ ልዩ እና ታላቅ የክብረ በዓሉ ትዕይንት ነው። የሚከናወነውም ከጸሎተ ቅዳሴው በኋላ ቤተ ማርያም በተባለው ቤተ መቅደስ ሲኾን፣ ከታች ባለነጭ ካባ ካህናት፣ ከላይ ደግሞ ባለጥቁር ካባ ካህናት በቅዱስ ያሬድ ዜማ "ቤዛ ኩሉ ዓለም ዮም ተወልደ" ማለትም "የዓለም ኹሉ መድኃኒት ዛሬ ተወለደ" እያሉ ይዘምራሉ።

በጥቅሉ፣ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች ቅዱስ መካን በኾነችውና በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ደግሞ የቅርስ ማእከል ኾና በተመዘገበችው ላሊበላ፣ ገና የገነነ ስፍራ አለው፡፡ አማኞች ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍል ወድ ሥፍራው በመሔድ ያከብራሉ።

ኾኖም “የዘንድሮውን ገና በጸጥታ መደፍረስና በኑሮ ውድነት ምክንያት በቀድሞ ድምቀቱ ለማክበር ይቸግራል፤” ይላሉ ለአሜሪካ ድምፅ አስተያየታቸውን የሰጡ ምእመናን፡፡
የዐማራ ክልል መንግሥት ደግሞ “በዓሉን አብረን እናክብር” የሚል መልእክት ሲያስተላልፍ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መደረጉን በመጥቀስ ነው፡፡

ዘገባውን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።

please wait

No media source currently available

0:00 0:12:18 0:00

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG