በቅርቡ በጂቡቲ ባሕር ዳርቻ ሰጥመው የሞቱት ፍልሰተኞችን ጉዳይ በተመለከተ የዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት (IOM) ለቪኦኤ በሰጠው ተጨማሪ መረጃ፣ ፍልሰተኞቹ ባሕር ውስጥ የሰጠሙት ጀልባዎቹ ዳር ሳይደርሱ ሕገ ወጥ አስተላላፊዎቹ ፍልሰተኞቹን እንዲወርዱ በማስገደዳቸው ነው ብሏል።
የአይኦኤም የአፍሪካ ቀንድ እና ደቡባዊ አፍሪካ ዲሬክተር የሆኑት ፍራንትዝ ሰለስቲን ለቪኦኤ እንዳስታወቁት፣ በሁለት ጀልባዎች ውስጥ ተሳፍረው ከነበሩት 310 ፍልሰተኞች ውስጥ 48 ሲሞቱ፣ 154 የሚሆኑት ደግሞ ከአደጋው ተርፈዋል። 108 ደግሞ የደረሱበት አልታወቀም ወይም ሕይወታቸው አልፏል።
በአንደኛው ጀልባ ላይ 100 ፍልሰተኞች ተሳፍረው የነበር ሲሆን በሁለተኛው ጀልባ ላይ ደግሞ 210 ፍልሰተኞች ተሳፍረው እንደነበር ዲሬክተሩ አስታውቀዋል።
ፍልሰተኞቹ ከየመን ወደ ጂቡቲ በማቅናት ላይ የነበሩ ሲሆን፣ የጂቡቲን ባሕር ዳርቻን በመቃረብ ላይ ሳሉ ሕገወጥ አስተላላፊዎቹ ጀልባዎቹ ባሕሩ መሃል ላይ ሳሉ ፍልሰተኞቹን እንዲወርዱ ማስገደዳቸውን ሃላፊው ተናግረዋል። በርካታ ቁጥር ያላቸውና መዋኘት ያልቻሉት ፍልሰተኞች ሰጥመው መምታቸውንም ሃላፊው ለቪኦኤ አስታውቀዋል።
ባለፈው ሰኞ በተፈጠረው በዚህ ክስተት እስከ አሁን ያልተገኙትን በተመለከተ ፍለጋው መቀጠሉን፣ ነገር ግን ከተቆጠሩት ቀናት አንጻር ሕይወታቸው ሊያልፍ ይችላል ብለው እንደሚሰጉ ፍራንትዝ ሰለስቲን ለቪኦኤ ተናግረዋል።
በሕይወት የተረፉት ፍልሰተኞች ድርጅቱ በጂቡቲ መጠለያና የሕክምና ዕርዳታ እንደሰጣቸው የገለጹት ኃላፊው፣ በባሕር መሥመሩ የሚተላለፉት ኢትዮጵያያንና ሶማሊያውያን እንደሆኑ፣ በአብዛኛው ግን ኢትዮጵያውያን እንደሆኑ ገልፀዋል።
መድረክ / ፎረም