በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

"ዩናይትድ ስቴትስ ለአፍሪካ ሀገሮች አንድ ሚሊዮን የኤም ፖክስ ክትባት ትለግሳለች" ፕሬዚደንት ባይደን


የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን በ79ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጀት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን በ79ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጀት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ

ዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ሀገሮች የያዙት የጸረ ኤም ፖክስ ወረርሽኝ ትግል ለመደገፍ አንድ ሚሊዮን ክትባቶችን እና ቢያንስ የአምስት መቶ ሚሊዮን ዶላር እርዳታ መስጠቷን ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ዛሬ አስታወቁ።

ዛሬ ማክሰኞ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ባሰሙት ንግግር እርዳታውን ይፋ ያደረጉት ፕሬዚደንት ባይደን ሊሎች ሀገሮችም ተመሳሳይ እርዳታ እንዲያደርጉ ተማጽነዋል። "ኤምፖክስን ለመጋፈጥ ፈጥነን መንቀሳቀስ አለብን " ብለዋል ባይደን።

የዓለም የጤና ድርጅት ቀድሞ የዝንጀሮ ፈንጣጣ ተብሎ ይጠራ የነበረውን ኤምፖክስን በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ዓለም አቀፍ የጤና አጣዳፊ ስጋት ብሎ ባለፈው ነሃሴ አውጇል።

ኮንጎ ዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ውስጥ የተቀሰቀሰው በቫይረስ ተላላፊው ወረርሽኝ ወደአጎራባች ሀገሮች ብቻ ሳይሆን ህንድን ጨምሮ ወደሌሎች ሀገሮች ተዛምቷል።

በቅርቡ የዩናይትድ ስቴትስ ኮንግሬስ ዓለም አቀፍ ወረርሽኞችን ለመታገል የሚውል ገንዘብ መቁረጡ "በሀገር ውስጥ ለወረርሽኙ የሚሰጡ ምላሾችን መጉዳቱ እንደማይቀር" የተናገሩ አንድ የዩናይትድ ስቴትስ ባለስልጣን" ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ኤም ፖክስ የተያዘ ሰው ቢገኝ ብዙም ሊያስገርም አይገባም" ብለዋል።

ኮንጎ ላይ የተቀሰቀሰው ኤምፖክስ "ክላድ ኤ" የሚል ስያሜ የተሰጠው የቫይረሱ ዓይነት ሲሆን ከዚያ ወዲህ "ክላድ ቢ" የሚል ስያሜ በተሰጠው አዲስ የቫይረሱ ዝርያ ዓይነት ተከስቷል። ይኼኛው ወሲባዊ ግንኙነትን ጨምሮ በወትሮአዊ የሰው ለሰው የቅርብ ንክኪ በቀላሉ የሚተላለፍ መሆኑ ተገልጿል።

ባለጸጎቹ ሀገሮች ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ሊረዳ የሚችል የብዙ መቶ ሚሊዮን ክትባት ክምችት አላቸው። ቢሆንም ሮይተርስ የመንግሥታት መግለጫዎች፥ ሰነዶች እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ዋቢ አድርጎ ባጠናረው መረጃ መሠረት እስካሁን ሀገሮቹ የተላከላቸው የክትባት እርዳታ መጠን ከሚፈለገው በእጅጉ ያነሰ ነው።

ዩናይትድ ስቴትስ ለአፍሪካ ሀገሮች የምትለግሰው ክትባት በአብዛኛው ከራሷ የክትባት ክምችት የሚወጣ ባቬሪያን ኖርዲክ የሚባለው የኤምፖክስ ክትባት እንደሚሆን ይጠበቃል።

የዩናይትድ ስቴትሱ ባለስልጣን እንዳሉት አስተዳደሩ ክትባቱን ለሀገሮቹ የማከፋፈሉን ሥራ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ሀገሮች የሚቀርቡ ክትባቶችን ግዢ በጋራ የሚሸፍነው ጋቪ የተባለው የመንግሥታዊ እና የግል ዘርፍ ጥምረት እንደሚያከናውን ይጠብቃል።

ጋቪ ባለፈው ሳምንት በሰጠው መግለጫ የኤምፖክስ ክትባት ሲገዛ የመጀመሪያው የሚሆኑትን 500 ሺህ ባቬሪያን ኖርዲክ ክትባቶች እንደሚገዛ አስታውቆ ነበር።

የባይደን አስተዳደር ተጨማሪ ክትባቶች በዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው ሀገሮች እንዲመረቱ ግፊት በማድረግ ላይ ሲሆን የቡድን ሀያ አባል ሀገሮች ማሕበር የኤምፖክስ ወረርሽኝ ምላሾችን እንዴት ለማገዝ እንደሚችሉ ከብራዚል ጋር በመወያየት ላይ መሆኑን ባለስልጣኑ አመልክተዋል።

አፍሪካ ውስጥ ለኤምፖክስ ክትባት መሥሪያ የሚያስፈልገውን እና በአቀማመሙ፥ በአሰጣጡ እና በሚጨመሩት በዋናዎቹ መቀመሚያዎች ውስብስብ የሆነውን መድሃኒት ለማምረት የሚችል አንድም ሀገር እንደሌለ የዩናይትድ ስቴትሱ ባለስልጣን አስረድተዋል።

በጆርጅታውን ዩኒቨርስቲ የዓለም አቀፍ ጤና ህግ አዋቂ ባለሞያው ሎረንስ ጎስቲን "ባይደን ባለዝቅተኛ ገቢ ሀገሮች የራሳቸውን ክትባት እንዲያመርቱ በአደባባይ ድጋፋቸውን ሰጥተዋል። ትልቁ ነገር እርሱ ነው። ያ እንዲሳካ የመድሃኒት አምራች ኩባኒያዎች ላይ ቴክኖሎጂውን ለሀገሮቹ እንዲያጋሩ ግፊት ማድረግ ይኖርባቸዋል" ብለዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG