የኢትዮጵያ መንግስት ከሶማሌላንድ ጋር የተፈራረመውን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ በያዘው ጥረት የሚገፋ ከሆነ፣ አገራቸው ኢትዮጵያ ውስጥ በመዋጋት ላይ ያሉ አማፂያንን መደገፍ ትጀምራለች ሲሉ የሶማሊያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተናገሩ።
የሶማሊያው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አህመድ ሞዓሊም ፊቂ፤ ይኸንን ያሉት ዩኒቨርሳል ከተሰኘ የሀገር ውስጥ ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር በነበራቸው ቆይታ ወቅት ነው። “ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የታጠቁ አማጽያንን አልያም የኢትዮጵያን መንግስት የሚታገሉ ወገኖችን መደገፍ የሚለው አማራጭ ለሶማሊያ ክፍት የሆነ በር ነው” ብለዋል።
“ከዚያ ደረጃ ላይ አልደረስንም” ያሉት የሶማሊያው ሚንስትር አያይዘውም “አሁንም ‘መፍትሄ አለው’ የሚል ተስፋ አለ። ነገር ግን ኢትዮጵያ በጀመረችው የምትገፋ ከሆነ፤ ከአማጺያኑጋር ግንኙነት መፍጠር፣ እነሱን ማነጋገሩ እና ከጎናቸው አብሮ መቆም ትክክለኛ እና ለእኛ ክፍት የሆነው አማራጭ ነው” ብለዋል።
“ያ የሚሆነው ግን በጠበኝነት እና ስምምነት የሚሉትን ነገር ለማስፈጸም በያዙት ጥረት ከቀጠሉ ነው” ሲሉም እቅዳቸውን አብራተዋል።
የሶማሊያ መንግስት ከህወሃት ጋር ግንኙነት የመመስረት ዕቅድ ይኖረው እንደሆነ የተጠየቁት የሶማሊያው ሚንስትር፣ በተባለው ጉዳዩ ዙሪያ መወያየታቸውን አምነው፤ ሆኖም በአሁን ሰዓት የኢትዮጵያ መውደቅ የሶማሊያም ሆነ የአፍሪካ ቀንድ ፍላጎት አይደለም፤ ነገር ግን እነሱ የሶማሊያን ተቃዋሚዎች እና አስገንጣዮችን መደገፋቸውን እና ከተዋዋሏቸው ጋር ግንኙነታቸውን ከቀጠሉ እሱም አማራጫችን ይሆናል” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
የሶማሊያ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አስተያየት የተቹት በአፍሪካ ህብረት እና በመንግስታቱ ድርጅት የኢኮኖሚ ኮሚሽን የኢትዮጵያ ምክትል ቋሚ ተወካይ አቶ ነቢዩ ተድላ በበኩላቸው “ከባናዲር ግዛት (የሞቃዲሾ ዙሪያ) ፈቅ ያላለ ብቃት ያለው ሥራ መስራት የማይችሉ የመንግስት ባለስልጣናት ተመስለው የተቀመጡ የአልሸባብ ተላላኪዎች፣ በባዶ የብሔርተኝነት ስሜት ተሞልተው ሲናገሩ ማየት በጣም አስቂኝ ነው” ሲሉ በኤክስ ማኅበራዊ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል። አክለውም “እንዲህ ያለው ድርጊት ሶማሊያ በዓመታት ያሰመዘገበችውን እመርታ ገደል የሚከት ነው” ብለውታል።
ከዚህ ቀደም በታሪካቸው ሁለት ትላልቅ ጦርነቶችን ያስተናገዱት ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ አንዳቸው ሌላውን የሚዋጋ አማጺ ቡድን የመደገፍ ታርክም እንዳላቸው የሚታወስ ነው።
መድረክ / ፎረም