በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል ባለው ውጥረት የዩናይትድ ስቴትስ አቋም


ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ የሶማሌላንድ አስተዳደር ጋር የተፈራረመችውን አወዛጋቢ የመግባቢያ ሥምምነት ተከትሎ፤ በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ መካከል ለተፈጠረው ውጥረት ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ ይገኛል የሚል ተስፋ ማሳደራቸውን አንድ የዩናይትድ ስቴትስ ዲፕሎማት ገለጡ።

በሞቃዲሾ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ሪቻርድ ራይሊ ከአሜሪካ ድምጽ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ሃገራቸው “ለዚህ ወቅታዊ ሁኔታ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ ለማፈላለግ ከሌሎች ጋር በትብብር እየሰራች ነው” ብለዋል።

"በጣም አሳዛኝ እና የነገሮችን አካሄድ በእጅጉ የሚያደናቅፍ ሁኔታ ነው” ያሉት አምባሳደር ራይሊ አያይዘውም፤ ከአጋር ሀገራት ጋር በመሆን እዚህ ከሶማሊያ ፌደራል መንግሥት፣ አዲስ አበባ ላይ ደግሞ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ሁኔታውን በዲፕሎማሲያዊ መንገዶች እንዲቋጭ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እያደረግን ነው” ብለዋል።

“በመካሄድ ላይ ያሉ ድርድሮች አሉ።” ያሉት ራይሊ ቱርክ እነዚህን በዙር የሚካሄዱ ድርድሮች እያስተናገደች መሆኗን ጠቁመው፤ “ቀጣዩም በቀናት እድሜ ይጀመራል። ‘ይህም አዲስ ዙር ድርድር ዲፕሎማሲያዊ እልባት ያስገኛል’ የሚል ታላቅ ተስፋ አሳድረናል” ሲሉ በሞቃዲሾው የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ ባደረጉት በዚህ ቃለ ምልልስ ዘርዝረዋል።

የሶማሊላንድ ባለሥልጣናት እንዳስረዱት፤ ሁለቱ ወገኖች የተፈራረሙት የመግባቢያ ሰነድ ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ የነጻ ሃገርነት እውቅና በመስጠት የመጀመሪያዋ ሀገር ሲያደርጋት፣ ሶማሌላንድም በምላሹ ኢትዮጵያ የባህር ኃይል ጦር ሰፈርነት የምትጠቀምበት 20 ኪሎ ሜትሮች ርዝማኔ ያለው መሬት ከባሕሯ ለኢትዮጵያ ለ50 ዓመታት በኪራይ የሚያስገኝ ነው።

በሌላ በኩል፤ የሶማሌላንድን የሶማሊያ አካል አድርጋ የምትመለከተው ሞቃዲሾ፣ እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር ጥር 1/2024 የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና የሶማሌ ላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ ያደረጉት ስምምነት ሉዓላዊነቴን የሚጻረር ነው ስትል መቃወሟ አይዘነጋም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ “ሁኔታው ሁለቱን አገሮች ወደ ጦርነት ሊያመራ ይችላል” የሚል ስጋት እንዳላቸው የተጠየቁት ራይሊ “የለም” ሲሉ መልሰዋል። "ጦርነት ቀርቶ ምንም ዓይነት ግጭት የመቀስቀሱን ዕድል ማንም አይቀበልም። ለዚህም ነው ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ፣ ሁሉም፤ ለጉዳዩ እልባት ለማበጀት ሳያቋርጥ በትጋት እየሰራ ያለው። የዩናይትድ ስቴትስም ጥረት በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል ላለው ሁኔታ ሁነኛ መፍትሄ ለማግኘት ነው” ብለዋል።

“ፍፁም አስፈላጊው ጉዳይም ይህ ነው። በፍጥነት እና አሁኑኑ እውን መሆን አለበት” ሲሉ አጠቃለዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG