በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሶማሊያ ታጣቂ ቡድኖች እና በኢትዮጵያ ላይ የደቀኑት ስጋት


 ፋይል- የአልሸባብ ተዋጊዎች ከሞቃዲሾ፣ ሶማሊያ በስተደቡብ 18 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ላፎፌ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር የካቲት 17 ቀን 2011 ዓ.ም. ወታደራዊ ልምምድ ሲያደርጉ።
ፋይል- የአልሸባብ ተዋጊዎች ከሞቃዲሾ፣ ሶማሊያ በስተደቡብ 18 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ላፎፌ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር የካቲት 17 ቀን 2011 ዓ.ም. ወታደራዊ ልምምድ ሲያደርጉ።

የኢትዮጵያ መንግሥት፣ መሠረታቸውን ሶማሊያ ውስጥ ያደረጉ ታጣቂ ቡድኖች፣ ኢትዮጵያውያንን ለተዋጊነት መመልመልን ጨምሮ የሚደቅኑትን ስጋት አሳሳቢነት ይናገራል። ኾኖም፣ የጸጥታ ኀይሎቹ የሚወስዷቸው ፀረ ሽብርተኛ ርምጃዎች ስኬታማ መኾናቸውን አበክሮ ያስገነዝባል።

please wait

No media source currently available

0:00 0:06:44 0:00

የሶማሊያው ታጣቂ ቡድን አልሻባብ፣ ከሁለት ዓመታት በፊት በዚኽ ወር ውስጥ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ታጣቂዎቹን ደንበር አሻግሮ ወደ ኢትዮጵያ ግዛት በመላክ ጥቃት ሰንዝሮ እንደነበር ይታወሳል።

ቡድኑ ጥቃቱን በድፍረት ይሰንዝር እንጂ፣ ብዛት ያላቸው ተዋጊዎቹ ተገድለውበታ፤ የተማረኩም አሉ።

የቀጣናውን የጸጥታ ጉዳዮች የሚከታተሉ ተንታኞች እንደሚሉት፣ አልሻባብ እንዲሁም በሰሜን ምሥራቋ የሶማሊያ ግዛት - ፑንትላንድ ያሉ ታናናሽ የእስልምና መንግሥት ቅርንጫፍ ቡድኖች፣ ኢትዮጵያውያንን ለተዋጊነት መመልመላቸውን ቀጥለዋል።

ስለ ጉዳዩ፣ የአሜሪካ ድምፅ የጠየቃቸው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ነቢዩ ተድላ፣ በጽሑፍ በሰጡት ምላሽ፥ “ሽብርተኛው” አልሻባብ፣ በአፍሪቃ ቀንድ እና በምሥራቅ አፍሪካ አካባቢ አጠቃላይ ጸጥታ እና መረጋጋት ላይ አደጋ መደቀኑን እንደቀጠለ መኾኑን አንሥተዋል።

ኾኖም ኢትዮጵያ፣ ከቀጣናው አጋሮቿ ጋራ በመተባባር በንቃት እንደምታከናውን በገለጹት የስለላ እና መረጃ የመሰብሰብ ሥራ፣ እንዲሁም በሶማሊያ በሚገኘው የአፍሪካ ኅብረት ኀይል ውስጥ የተሰማሩ ወታደሮች እንዳሏት ያወሱት ቃል አቀባዩ፣ “አሸባሪው ቡድን የደቀናቸውን የጸጥታ አደጋዎች እና ቡድኑ በደንበሩ አካባቢ ተጽእኖውን ለማስፋፋትና ተዋጊ ለመልመል የሚያደርገውን ሙከራ ተከላክሎ የማክሸፍ ሚና ተጫውቷል፤” ብለዋል።

የአደጋውን መኖር የተገነዘበው የኢትዮጵያ የጸጥታ ተቋም፣ አልሻባብ የሚሰነዝረውን ማንኛውም ጥቃት መክቶ ለመመለስ፣ በኢትዮጵያ ደንበር ውስጥ ብቻ ሳይወሰን ሳያሰልስ በንቃት እየሠራ እንደሚገኝ ቃል አቀባዩ አመልክተዋል፡፡ ይኸውም፣ በአፍሪካ ኅብረት የሶማሊያ የሽግግር ተልእኮ በምኅጻሩ አትሚስ እና በኢትዮጵያ ብሔራዊ የመከላከያ ኅይሎች ሥር ያሉ የሶማሊያን አካባቢዎች ጭምር እንደሚያካትት ተናግረዋል፡፡

አልሻባብ እና የእስላማዊ መንግሥት ቡድኑ - አይኤስ፣ ጸጥታቸው በደፈረሱ አንዳንድ የኢትዮጵያ አካባቢዎች፣ ባለፉት ቅርብ ዓመታት ኢትዮጵያውያንን ለተዋጊነት መልምለዋል። በተለይም አይ ኤስ፣ ከተዋጊዎቹ ጋራ ኢትዮጵያውያንም በሥልጠና ላይ እንዳሉ የገለጸበትን የቪዲዮ ምስሎች አሰራጭቷል።

የሶማሊያ ፑንትላንድ ክፍለ ግዛት ባለሥልጣናትም፣ በተለያዩ ጊዜያት፣ በተራራማው አልሚስካድ አካባቢ፣ ከእስላማዊ መንግሥት ቡድኑ ጎን ተሰልፈው ሲዋጉ የተገኙ ናቸው ያሏቸውን ኢትዮጵያውያንን “ማርከናል፥ ገድለናል እና ለፍርድም ያቀረብናቸው አሉ” ማለታቸው ይታወሳል።

ባለፈው ሳምንት ረቡዕ፣ የፑንትላንድ የጸጥታ ኀይሎች፣ ዛንዚባር ውስጥ አንድ የአይኤስ ታጣቂ እንደያዙ ተናግረዋል። በቁጥጥር ሥር የዋለው ግለሰብ፣ ለመረመሩት ባለሥልጣናት፣ አይኤስ ከተቀናቃኙ ከአልሻባብ ጋራ በሚያካሒደው ውጊያ ላይ ሲሳተፍ ቆይቶ ቡድኑን የከዳ መኾኑን እንደተናገረ ጠቅሰዋል። በውጊያ ላይ ሳለ፣ ኢትዮጵያውያን፣ ማላዊያውያንና የመናውያን አብረውት እንደነበሩ መናገሩን ባለሥልጣናቱ አመልክተዋል።

ባለፈው የካቲት ወር ደግሞ፣ የፑንትላንድ ፍርድ ቤት፣ በስድስት ሞሮኮአውያን ላይ የሞት ጥቃት ፍርድ ሲያስተላልፍ፣ አንድ ኢትዮጵያዊ ደግሞ የ10 ዓመት እስራት ቅጣት ተፈርዶበታል።

የአይኤስ ተዋጊዎች ቁጥር፣ ቀደም ብሎ ከ100 እስከ 400 እንደሚደርስ ቢነገርም፣ አንድ ተንታኝ እንደሚሉት ግን፣ እ.አ.አ በዚኽ ዓመት ቁጥሩ ከተጠቀሰውም ጨምሯል።

ቀድሞ የፑንትላንድ የደኅንነት እና የፖሊስ አዛዥ የነበሩት ብሪጋዲየር ጀኔራል አብዲ ሐሰን ሑሴን እንደሚሉት፣ የሌላ ሀገር ዜጋ የኾኑት ተዋጊዎች ብቻ፣ ከ500 እስከ 600 ይደርሳሉ። ይኹንና አኀዙ በአካባቢው ባለሥልጣናት አልተረጋገጠም።

አብዛኞቹ ዐዲስ ተመልማዮች፣ የመካከለኛው ምሥራቅ እና የሰሜን አፍሪካ ሰዎች እንደኾኑ የተነገረ ሲኾን፣ በርከት ያሉ ኢትዮጵውያንም አሉባቸው ተብሎ ይታመናል።

ብርጋዲየር ጄኔራል አብዲ ሐሰን በሰጡት ቃል፣ የዳኢሽ(አይ ኤስ) ተዋጊዎች ቁጥር በኀምሳ ከመቶ ጨምሯል። ለዚኽም ብዙ ምክንያቶች መኖራቸውን ጠቅሰው ያስረዳሉ። የሚበዙት ምልምሎች፣ “ከኢራቅ እና ከሶሪያ እንዲሁም ከአፍጋኒስታን ሳይቀር ይመጣሉ፤” የሚሉት ብርጋዲየር ጀነራሉ፣ በአገሮቻቸው የፀረ ሽብር ጦርነት ይዞታዎቻቸውን መነጠቃቸውን ገልጸው፣ “ከሀገር እንዲወጡ ግፊት ይደረግባቸዋል፤” ብለዋል።

ከአልሻባብ ተዋጊነት የከዳውና በአሁኑ ወቅት አስተያየት ሰጪ የኾነው ዑመር መሐመድ አቡ አያን እንደሚለው፣ አይኤስ በአሁኑ ጊዜ ወጣቶችን በተዋጊነት እንዲገቡለት ለመሳብ፣ የቡድኑን ነሺዳዎች በዐማርኛ ተርጉሞ የሚያሰማ ኢትዮጵያዊ ሰባኪም አለው።

ይኸው አስተያየት ሰጪ፣ “ነጋዴዎችን እያስገደዱ ገንዘብ ይነጥቁ ጀመር። እምቢ የሚሉትን አጠቋቸው። ያን ካደረጉ በኋላ ከኢትዮጵያ ተሰድደው የመጡ ፍልሰተኞችን ሳቡ። ኦሮሞዎች እና የትግራይ ተወላጆች አሉባቸው። ነሺዳውን በዐማርኛ ተርጉሞ የሚያሰማላቸው ኢትዮጵያዊም አላቸው፤” ብሏል።

የኢትዮጵያ መንግሥት፣ የኢትዮጵያውያንን በአልሻባብ እና በአይኤስ መመልመልን ጉዳይ በስፋት የሚፈጸም ከባድ ችግር አድርጎ እንደማይመለከተው፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ነቢዩ ተድላ ተናግረዋል። ይልቁንም የሚመለከታቸው የጸጥታ እና የስለላ ባለሥልጣናት፣ ኹኔታውን በቅርበት እንደሚከታተሉት ጠቅሰው፣ “ኢትዮጵያውያንን በተለይም ወጣቶችን ለመመልመል የሚደረግ ማናቸውም ሙከራ ለማክሸፍ በንቃት በመሥራት ላይ ይገኛሉ፤” ብለዋል።

ኢትዮጵያውያንን ለአልሻባብ ምልመላ ዒላማ ሊኾኑ የሚችሉበት አጋጣሚ ቢኖር እንኳን፣ “የኢትዮጵያ መንግሥት በንቃት የሚከታተለው ጉዳይ ነው፤” ያሉት ቃል አቀባዩ፣ “የጸጥታ ኀይሎቻችን እንቅስቃሴ እንደቀጠለ በመኾኑ ኹኔታውን ለመቆጣጠር ተችሏል፤” ሲሉ አክለዋል።

ቃል አቀባዩ አስከትለውም፣ “የኢትዮጵያ መንግሥት ፀረ ሽብርተኛ ጥረቶቹን ለማጎልበት ብሎም የኢትዮጵያን ብቻ ሳይኾን በአጠቃላይ የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ጸጥታ እና መረጋጋት ለመጠበቅ፣ ከክልላዊ እና ዓለም አቀፋዊ አጋሮቹ ጋራ በቅርበት ለመሥራት ያለው ቁርጠኝነት “አሁንም የጸና ነው” ብለዋል።

በሶማሊያ፣ የእስላማዊ መንግሥት ቡድንን፣ ባለፈው ጥቅምት ወር ያቋቋሙት፣ ለተገደለው የአይኤስ ዋና መሪ ለአቡባካር አል ባግዳዲ “ታማኝ ነው” በተባለው በሼክ አብደልቃድር ሙሚን የሚመሩ የአልሻባብ የቀድሞ ተዋጊዎች ናቸው፡፡ ሙሚን፣ እ.አ.አ ባለፈው ግንቦት 31 ቀን፣ በዩናይትድ ስቴትስ የአየር ጥቃት እንደተገደለ መዘገቡ የሚዘነጋ አይደለም።

/በሃሩን ማሩፍ የተጠናቀረውን ዘገባ ቆንጅት ታየ ወደ አማርኛ መልሳዋለች/

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG