በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ደሴን የጎበኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከታጣቂዎች ጋራ ለመነጋገር ዝግጁነታቸውን ገለጹ


የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ አማራ ክልል ደሴ ከተማ፣ ሰኔ 22 ቀን 2016 ዓ.ም./ ፎቶ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፌስቡክ ገጽ
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ አማራ ክልል ደሴ ከተማ፣ ሰኔ 22 ቀን 2016 ዓ.ም./ ፎቶ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፌስቡክ ገጽ

በዐማራ ክልል የትጥቅ ግጭት በቀጠለበት ኹኔታ ውስጥ ወደ ክልሉ የተጓዙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ትጥቅ ያነገቡ አካላት ወደ ሰላም እንዲመለሱ፥ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች እና ወላጆች የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ያዳምጡ

please wait

No media source currently available

0:00 0:04:01 0:00

ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ትላንት ቅዳሜ፣ በደሴ ከተማ ጉብኝት ማድረጋቸውንና ከኅብረተሰቡ የተወጣጡ ከተባሉ ነዋሪዎች ጋራ መወያየታቸውን ሲገልጹ፣ መንግሥታቸው ከማንኛውም የታጠቁ ኀይሎች ጋራ ለመነጋገር ዝግጁ መኾኑን ተናግረዋል፡፡

ትላንት ቅዳሜ፣ ሰኔ 22 ቀን 2016 ዓ.ም. በደሴ ከተማ ተገኝተው ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተውጣጥተዋል ከተባሉ ነዋሪዎች ጋራ መወያየታቸውን፣ በፌስቡክ የማኅበራዊ ትስስር ከጻቸው ያስታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ከመንግሥታቸው ጋራ በትጥቅ ግጭት ውስጥ ለገቡት የፋኖ ቡድን ታጣቂዎች የሰላም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በውይይቱ ላይ፥ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች እና ወላጆች፣ ትጥቅ ያነሡ ኀይሎችን ወደ ሰላም እንዲመጡ በማድረግ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

ባለፈው ሳምንት፣ በባሕር ዳር ከተማ የተካሔደው የሰላም ጉባኤ ተሳታፊዎች፣ “በጫካ ለሚገኙ ወንድሞች” በሚል ለጠሯቸው ኀይሎች፣ በውይይት እና በድርድር ወደ ማኅበረሰቡ ተቀላቅለው በአገራዊ ምክክሩ በመሳተፍ የሕዝቡን ኹለንተናዊ ችግር በመፍታት ታሪካዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ፤ በግጭቱ ዐውድ ውስጥም የታሰሩ ፖለቲከኞች፣ ምሁራን፣ ጋዜጠኞች እና ተጽእኖ ፈጣሪ ዜጎች እንዲፈቱ በአቋም መግለጫቸው መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩም በትላንቱ የደሴው ጉብኝታቸው ላናገሯቸው የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች፣ “በግራ በቀኝ የወጡትን መክራችኹ መልሱ፤ በዚያ መንገድ ምንም ዐይነት ውጤት፣ ምንም ዐይነት ድል እንደማይመጣ እናውቀዋለን፤ እኛ የምንፈልገው ሰላም ነው፤” ሲሉ፣ መንግሥታቸው የሰላም ጥረቱ እንዲሳካ ለውይይት ዝግጁ መኾኑን አረጋግጠዋል፡፡

በዐማራ ክልል የተፈጠረው የጸጥታ መደፍረስ ከክልሉ ዐቅም በላይ እንደኾነ በመገለጹ፣ ላለፉት ዐሥር ወራት ተደንግጎ የቆየው የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ የሕግ ተፈጻሚነት፣ ባለፈው ግንቦት 24 ቀን ቢገባደድም፣ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ትጥቃዊ ግጭቶች መቀጠላቸውን፣ ነዋሪዎች ለአሜሪካ ድምፅ ገልጸዋል።

አንድ ወጥ ዕዝ ለመፍጠር በመሥራት ላይ እንደሚገኙ የሚገልጹት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የፋኖ ታጣቂ ቡድኖች በበኩላቸው፣ “የዐማራ ሕዝብ ላይ የተጋረጠው የህልውና ስጋት አልተቀለበሰም፤ ልዩ ኀይሉ ትጥቁን መፍታት የለበትም፤ ክልሉ አሁንም ለሌላ ዙር ጥቃት ተጋላጭ ነው፤” የሚሉና መሰል ጭብጦችን በማንሣት፣ ከመንግሥት የጸጥታ ኀይሎች ጋራ የትጥቅ ግጭት ውስጥ ከገቡ አንድ ዓመት ገደማ እንደኾናቸው ይታወቃል፡፡

የትጥቅ ግጭቱ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ከተስፋፋ ወዲህ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የትላንቱን የደሴ እና የሐይቅ ጉብኝታቸውን ጨምሮ፣ የባሕር ዳር ከተማንና ከጎንደር ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኘውን ጎርጎራን መጎብኘታቸው ይታወሳል፡፡

በደሴ ከተማ በተደረገው ውይይት ላይ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አገኘሁ ተሻገርንና የዐማራ ክልል ርእሰ መስተዳደር አረጋ ከበደን ጨምሮ የፌደራል እና የክልል መንግሥታት ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል፡፡

በተያያዘ፣ በ“ገበታ ለትውልድ” ፕሮጀክት ውስጥ በተካተተችውና ከደሴ 30 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ባለችው ለጎ ሐይቅ አካባቢ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የዘንድሮውን የ“አረንጓዴ አሻራ” ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ማስጀመራቸውን፣ መንግሥታዊ የኾኑ ብዙኀን መገናኛዎች ዘግበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ በፌስቡክ የማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባጋሩት መልእክት፣ ያደረጉት ውይይት እና የጎበኟቸው የልማት ሥራዎች አመርቂ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG