በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኢትዮጵያውያን በታሪካዊዋ ፒያሳ ፍርሰት “ጥልቅ ኀዘን ላይ ናቸው”


ኢትዮጵያውያን በታሪካዊዋ ፒያሳ ፍርሰት “ጥልቅ ኀዘን ላይ ናቸው”
please wait

No media source currently available

0:00 0:12:38 0:00

ኢትዮጵያውያን በታሪካዊዋ ፒያሳ ፍርሰት “ጥልቅ ኀዘን ላይ ናቸው”

ለወጣቷ ሰሚራ፣ ፒያሳ፥ የኢትዮጵያ ርእሰ መዲና አዲስ አበባ ዕንብርት እና የዘመናዊነት አውራ ብቻ አይደለችም፡፡ እትብቷ የተቀበረበት ታሪካዊ የትውልድ ቦታዋም ናት፡፡ ሰሞኑን የከተማው አስተዳደር በሚያካሒደው የኮሪዶር ልማት አብዛኛው የፒያሳ አካባቢ በመፍረሱ፣ ሰሚራ በከፍተኛ ኀዘን ውስጥ ትገኛለች፡፡ “ታሪካችንና ማንነታችን ነው የጠፋው” ትላለች በጥልቅ ማዘኗን ስትገልጽ፡፡

የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ከተማዋን ለማዘመን በያዙት ዐቅድ መሠረት፣ ባለፉት ሳምንታት አፈር ገፊ ቡልዶዘር መኪናዎች፣ በፒያሳ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ሕንፃዎች አፍርሰዋል። አንዳንዶቹ ደግሞ ከመቶ ዓመት በላይ ዕድሜ ያስቆጠሩ ናቸው።

በአንድ ወቅት ደማቅ የነበሩ አካባቢዎች፣ አሁን ወደ አዋራማ የቆሻሻ ክምር ተለውጠዋል። የአካባቢው ነዋሪዎችም ያለበቂ ማስጠንቀቂያ ቤታቸውንና የንግድ ስፍራቸውን ለቀው እንዲወጡ ተደርገዋል።

አንዲት ሴት፣ ከፍተኛ ፈረሳ በተካሄደበት የአዲስ አበባ ታሪካዊው ፒያሳ ሰፈር መሃል ስታልፍ - መጋቢት 14፣ 2024
አንዲት ሴት፣ ከፍተኛ ፈረሳ በተካሄደበት የአዲስ አበባ ታሪካዊው ፒያሳ ሰፈር መሃል ስታልፍ - መጋቢት 14፣ 2024

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የባቅላቫ መጋገሪያ ከነበረው ኬክ ቤት እስከ ወርቅ መሸጫ ሱቆች እና በጣም ብዙ ሰዎች ይሰበስቡባቸው እስከነበሩ ኬክ ቤቶች፣ በርካታ ታሪካዊ እና ተወዳጅ ቦታዎች ሙሉ ለሙሉ ጠፍተዋል።

በፒያሳ ተወልዶ አድጎ እዚያው በንግድ ሥራ ይተዳደር የነበረው ዮናታን ኀይሉ፣ "ከሲኒማ አምፒር አንሥቶ ፒያሳን ወደ ታች መመልከት ይረብሻል፤" ሲል ስሜቱን ያጋራል።

ከብሪቲሽ ካውንስል ጀርባ ተወልዶ ያደገው ታምራት ማለደም፣ 39 ዓመታትን በፒያሳ ኖሮ አሁን ደግሞ ልጆቹን በዚያው እያሳደገ ነው። ከልጅነት እሰከ እውቀት የኖረበት ፒያሳ ግን፣ እንደሚፈርስ በተነገረው “ሁለት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ታሪክ ኾኗል፤” ይላል።

የ30 ዓመቷ የመንግሥት ሠራተኛ ሰሚራ ደግሞ “እጅግ የምንወዳቸው የነበሩ ብዙ ታሪኮቻችን ወድመዋል፤” ትላለች። አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ እንዳናገራቸው በርካታ የፒያሳ ነዋሪዎች፣ እርሷም ሊደርስባት የሚችለውን አጸፋ በመፍራት ትክክለኛ ስሟ እንዲጠቀስ አትፈልግም። የአካባቢው ባለሥልጣናት፣ ሰሚራ ተወልዳ ያደገችበት ቤት እንደሚፈርስ ለቤተሰቦቿ ያሳወቁት "የሚፈርስበትን ትክክለኛውን ቀን ሳይነግሩን ነው" ትላለች።

የአንድ ሕፃን ልጅ እናት የኾነችውና በችኮላ በተፈጸመው ርምጃ በጠፉ እና በተጎዱ የቤተሰቦቿ ትዝታዎች ኀዘን ውስጥ የምትገኘው ሰሚራ፣ "በሳምንቱ ውኃ እና መብራት አቋረጡብን። ከዚያ በአንድ ቀን ከግማሽ ቤቱን እንድንለቅ ማስጠንቀቂያ ሰጡን፤" ስትልም ሒደቱን ታስረዳለች።

በታሪካዊው የፒያሳ አካባቢ በፈረሱ ቤቶች መካከል አንድ አዛውንት ተቀምጠው ሲተክዙ ይታያሉ - መጋቢት 17፣ 2024
በታሪካዊው የፒያሳ አካባቢ በፈረሱ ቤቶች መካከል አንድ አዛውንት ተቀምጠው ሲተክዙ ይታያሉ - መጋቢት 17፣ 2024

ሌላው የፒያሳ ነዋሪ ሳሚም ተመሳሳይ ታሪክ ይናገራል፡፡ የአባቱ ንብረት የኾነውን የሳሚን የማተሚያ ቤት ንግድ እና ሌሎች ሱቆችን የያዘው ሕንፃ ሲፈርስ የነበረውን ኹኔታ ሲያስታውስ “ኹሉም ነገር በብርሃን ፍጥነት ወዳለመኖር ተለወጠ” ይላል ሳሚ። የራሴ ሱቅ ነበረኝ፤ አሁን ግን ምንም የለኝም፤ የሚለው የ40 ዓመቱ ጎልማሳ፣ “አሮጌ ሊኾን ይችላል። ቆሻሻ ግን አይደለም። ለእኛ ቅርሳችን ነው፤” ሲል ኀዘኑን ይገልጻል።

ተቺዎችም፣ መንግሥት የአዲስ አበባ ኮሪደር ልማት ብሎ የጀመረው የከተማ እድሳት እና ማስዋብ ዕቅድ፣ ነባር ሕንፃዎችን ከማውደም ባለፈ፣ ከልዩ ልዩ የማኅበረሰብ ክፍል የተውጣጡ ሰዎች በፒያሳ የገነቡትን ማኅበራዊ ትስስርም ያፈራረሰ ነው፤ ይላሉ።

"ልዩ" የከተማ አካባቢ

በአራዳ ክፍለ ከተማ የሚገኘው አካባቢ “ፒያሳ” የሚለውን ስያሜ ያገኘው፣ እ.አ.አ. በ1930ዎቹ ኢትዮጵያን ወርሮ ቦታውን በተቆጣጠረው የኢጣሊያው ሙሶሎኒ ኀይሎች ነው። እስከ አሁን ስያሜውን እንደያዘ የዘለቀው ፒያሳ፣ በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መባቻ ላይ ሰፊ የገበያ ስፍራ ኾኖ ተገነባ።

የአንትሮፖሎጂ ባለሞያው ዶምኒክ ሐራሬ ስለ አካባቢው ሲያስረዱ፣ ከ1889 እስከ 1913 ዓ.ም. በነገሡት “በዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ጊዜ አራዳ የኢትዮጵያ የንግድ ልብ ትርታ ነበር፤” ይላሉ።

“የአዲስ አበባ አሮጌዋ ፒያሳ” የተሰኘ መጽሐፍ የጻፉት ሐራሬ፣ ታላላቅ የንግድ ቤቶችን ያስፋፉ ሕንዶች፣ አርመናውያን፣ ግሪኮች፣ ፈረንሳዮች እና ኢትዮጵያውያን፣ በገበያው ዙሪያ እና በአቅራቢያው ባሉ መንገዶች መስፈራቸውን ያወሳሉ። ይህ ዓለም አቀፋዊ ማኅበረሰብ፣ የተለያዩ የሥነ ሕንፃ ተጽእኖዎችን ማሳደር የቻለ “ልዩ ከተማ” መፍጠራቸውንም ያስረዳሉ።

እ.አ.አ ከ1920ዎቹ ጀምሮ፣ ነጋዴዎች የሚያስተዳድሯቸው መጋዘኖች፣ ከአነስተኛ ኪዮስኮች እና ሱቆች ጎን ለጎን ሥራቸውን ቀጥለው ነበር። ሀብታም ነጋዴዎች እና ባለሥልጣናት የሚኖሩባቸው በሚያማምሩ ደንጊያዮች እና ዕንጨቶች የተሠሩ ቪላ ቤቶችም፣ ከመጠነኛ ቤቶች በትይዩ ሕብር ፈጥረው ኖረዋል።

በቅኝ ገዢዎች ከተገነቡ ከተሞች ልማት ጋራ ሲነጻጸር፣ “ፒያሳን ልዩ የሚያደርገው፣ ከሌሎች የአፍሪካ ዋና ከተሞች በተቃራኒ አፍሪካዊ ባሕርይን በልዩነት ይዞ መገንባቱ ነው፤" ይላሉ የሥነ ሕንፃ ባለሞያው ፒት ኒየደር።

"የአዲስ አበባ ቤቶች" የተሰኘውንና ከተመሠረተችበት ከ1886 እስከ 1936 ዓ.ም. ድረስ ያለውን የኢትዮጵያ ከተማ ቅርሶች የሚዳስሰውን መጽሐፍ የጻፉት ኒየደር፣ ከተማዋ ይበልጥ እየለማች በሔደች ቁጥር በተመሳሳይ መፍረሶችና መፈናቀሎች ውስጥ ማለፏን ያወሳሉ። “የአሁኑን ፈረሳ ለየት የሚያደርገው ግን፣ እየደረሰ ያለው ውድመት መጠንና ብዙ መኖሪያ ቤቶች በተመሳሳይ ጊዜ እየፈረሱ መኾናቸው ነው፤” ሲሉም ያብራራሉ።

የፒያሳ መፍረስ በነዋሪዎች ላይ የፈጠረው ቅሬታ
please wait

No media source currently available

0:00 0:15:12 0:00

"ቅርሳችን"

እ.አ.አ. በ2018 ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ፣ በመሀል ፒያሳ ያስገነቡትን የዐድዋ ሙዚየም አሳንፀዋል፡፡ በየካ ተራራ ላይ በብዙ ሚሊዮን ዶላር የሚገነባውን ቤተ መንግሥት(የጫካ ፕሮጀክት) እና በርካታ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን አስጀምረዋል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ መሠረት፣ ከ21 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በግጭት እና በአየር ንብረት አደጋዎች ምክንያት አስቸኳይ ርዳታ በሚሹባት ሀገር ውስጥ እየተካሔደ ያለው የዚኽ ዓይነቱ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ቅንጡ ግንባታ፣ በብዙዎች ዘንድ ጥያቄ ፈጥሯል።

በሀገር ውስጥ የሚታተመው ሪፖርተር ጋዜጣ፣ ይፋዊ መረጃን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ በፒያሳ የሚታወቁ 56 ሕንፃዎች ሙሉ ለሙሉ ወይም በከፊል ፈርሰዋል።

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ዲሬክተር አቶ አበባው አያሌው፣ መሥሪያ ቤታቸው የአገሪቱ ቅርሶች ጉዳት እንዳይደርስባቸው በቅርበት እንደሚከታተል ይናገራሉ፡፡ በቅርቡ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት ግን፣ “የሕንፃ ዕድሜ ብቻውን ለቅርስነት ማዕርግ ብቁ አያደርግም፤” ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አበቤም፣ ሊሠሩ የታቀዱት ሰፋፊ መንገዶች፣ የብስክሌት መጓጓዣዎች እና የልጆች መጫወቻ ሜዳዎች፣ ኹሉንም ኅብረተሰብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ናቸው፤ ሲሉ ፕሮጀክቱን ደግፈው ተሟግተዋል። “እኛ ማፍረስ ሳንጀምር አንዳንድ አካባቢዎች መውደቅ ጀምረው ነበር፤" ያሉት ከንቲባዋ፣ "ተጠብቀው ሊቆዩ የሚገባቸውን ትዝታዎች ግን ጠብቀናል፤" ብለዋል።

በፒያሳ ፈረሳ የተካሔደባቸው አብዛኞቹ ቦታዎች ለጨረታ እንደሚቀርቡ፣ የከተማው ማዘጋጃ ቤት ባለሥልጣናት አስታውቀዋል። ከመኖሪያቸው ለተፈናቀሉት ሰዎች ደግሞ የገንዘብ ካሳ እና የለውጥ ቦታ እንደተሰጣቸው ቢገልጹም፣ ነዋሪዎቹ ግን ቅሬታቸውን በማሰማት ላይ ናቸው፡፡

ለአብነት ያህል፣ ላለፉት 30 ዓመታት፣ ፒያሳ ላይ በንግድ ትተዳደር የነበረችው አዜብ በለውጥ የተሰጣት መሬት፣ "ከመንገድ የራቀና ለመኖሪያ ቤትም ኾነ ለንግድ ግንባታ የማይመች ነው፤” ትላለች።

ሰሚራም የተሰጣት ኮንዶሚኒየም ቤት የሚገኝበት ሕንፃም “መስኮት፣ በር እና መጸዳጃ ቤት ያልተገጠመለት፤ ውኃ እና መብራት በቅጡ ያልተሟላለት ራቁቱን የቆመ ሕንፃ ነው፤" ትላለች፡፡ ይብሱኑ “እንስሳትን ለማኖር እንኳን ተስማሚ አይደለም፤” በማለት ታማርራለች፡፡

ሰሚራ እንደምትለው፣ በአንድ ወቅት ጠንካራ ማኅበራዊ ትስስር የነበረው የፒያሳ ሕዝብ አሁን በየቦታው ተበትኗል። “ወደፊት ልጆቻችን ስለ ቅርሶቻችንና እኛ ስላደግንበት ቦታ ሲጠይቁን ምንም የምናሳያቸው ነገርም አይኖርም፤” ትላለች።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG