በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ከኦቲዝም ጋር ለሚኖሩ ልጆች ስኬት ምን ይመስላል?


ከኦቲዝም ጋር ለሚኖሩ ሰዎች ስኬት ምን ይመስላል?
please wait

No media source currently available

0:00 0:12:18 0:00

ከኦቲዝም ጋር ለሚኖሩ ሰዎች ስኬት ምን ይመስላል?

ከኦቲዝም ጋር የሚኖሩ ሰዎች፣ ልክ እንደማንኛውም ሰው መማር፣ መስራት እና የራሳቸውን ኑሮ መምራት እንደሚችሉ የተለያዩ ጥናቶች ያመለክታሉ። እንደውም ኦቲዝም ስፔክትረም ዲሶርደር ተብሎ የሚጠራው በተለያየ መጠን እና ደረጃ የሚከሰት ውስብስብ የእድገት ሁኔታ ያጋጠማቸው ሰዎች ችግሮችን በልዩ ሁኔታ ለመፍታት ባላቸው አቅም እና ቀጥተኛ አቀራረብ ምክንያት ለአንዳንድ ስራዎች ተመራጭ ሊሆኑ እንደሚችሉም ያሳያሉ። ሆኖም ፍላጎታቸውን መረዳት እና ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ ለስኬታቸው ቁልፍ መሆኑን ባለሙያዎች ያሰምሩበታል።

ላለፉት 17 ዓመታት ከኦቲዝም ጋር የኖረው ናታን ብስክሌት ሲነዳ፣ ቤት ሲያፀዳ፣ እቃ ሲያስተካክል ወይም ቃላቶች አውጥቶ ስሜቱን ለመግለፅ ሲሞክር ማየት ለወላጆቹ ትልቅ ስኬት ነው። ምክንያቱም እናቱ ራሔል አባይነህ እንደምትለው፣ ናታን በሁለት አመት ከስምንት ወሩ የኦቲዝም እክል እንዳለበት የነገራቸው ሀኪም "የእድሜ ልክ በሽታ ነው፣ ተስፋ ቁረጡ" በሚል ተስፋቸውን ሊያጨልመው ሞክሮ ነበር።

ራሔል 'ኖኖ' እያለች በፍቅር የምትጠራው ሁለተኛ ልጇ ናታን ሲወለድ ኦቲዝም ስለሚባለው ከአንጎል እድገት ጋር የሚያያዝ እክል ምንም የምታውቀው ነገር አልነበረም። ነገር ግን ከሌሎቹ ሁለት ልጆቿ በተለየ የሚያሳየው ባህሪ ጥያቄ ይፈጥርባት ነበር።

ከህጻናት የነርቭ እና የእድገት መታወክ ጋር ከሚያያዘው ኦቲዝም ጋር የሚወለዱ ልጆች በአብዛኛው የተግባቦት፣ ማህበራዊ ግንኙነቶችን የመመስረት እና ሀሳብን በአግባቡ የመግለፅ ችግሮች ይታይባቸዋል። እንደ እክሉ ደረጃ እና መጠንም እንደ እንቅልፍ ማጣት እና የሆድ ህመም ከመሳሰሉ ህመሞች ጋርም ሊዛመድ ይችላል።

ራሔል በልጇ ላይ የምትመለከታቸውን እነዚህን ያልተለመዱ ባህሪያት ለመረዳት እና በተለይ ከተወለደ ጀምሮ እጅግ ያሳስባት የነበረውን የሆድ ድርቀት በሽታ ለማዳን በርካታ የህክምና ባለሙያዎችን ጎብኝታለች። በመጨረሻ ችግሩን ያወቀለት ሐኪም የሰጣት ተስፋ አስቆራጭ ምላሽም ለሁለት ወራት እንድታለቅስ እና ድባቴ ውስጥ እንድትገባ አድርጕታል። ነገር ግን የልጇን ችግር ማወቅ መቻሏ እና ችግሩን ተቀብላ ለመፍትሄው እራሷን ማዘጋጀቷ ናታን ዛሬ ለደረሰበት ስኬት ዋና መሠረት መሆኑን ትናገራለች።

ኦቲዝም ያለባቸውን ህፃናት እንዴት ለውጤት ማብቃት ይቻላል?
please wait

No media source currently available

0:00 0:08:31 0:00

ራሐል አሁን ከራሷ ልጅ አልፎ፣ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ከኦቲዝም የሚኖሩ ልጆች ህይወት መቀየር ምክንያት የሆነውን ነህምያ የኦቲዝም ማዕከል ከከፈተች 13 ዓመታትን አስቆጠረች።

ነህምያ ውስጥ የብዙ ሺህ እናቶች እምባ ታብሷል፣ የበርካታ ልጆች ህይወት ተቀይሯል። ከ30 በላይ ልጆች በተደረገላቸው ተገቢ የሆነ ድጋፍ፣ ስልጠና እና ክትትል መሻሻሎች አምጥተው ወደ መደበኛ የትምህርት ተቋማት መቀላቀል መቻላቸውንም ራሔል ትገልፃለች።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጥናት መሠረት፣ ኦቲዝም ስፔክትረም ዲስኦርደር ተብሎ የሚጠራው፣ በተለያየ መጠን እና ደረጃ የሚከሰት የአይምሮ እድገት መዛበት እክል፣ በዓለም ዙሪያ ከሚወለዱ 100 ህፃናት በአንዱ ላይ ይከሰታል። ሆኖም ብዙዎቹ ኦቲዝም ያለባቸው ሰዎች ነገሮችን በተለየ መንገድ በማየት፣ ልዩ ትኩረት በመስጠት፣ በስዕል፣ በሙዚቃ እና ሌሎች የትምህርት አይነቶች ብቃት እንዳላቸው ማስመስከር ችለዋል። በዓለም ዙሪያ ትልቅ ደረጃ መድረስ የቻሉት የማይክሮሶፍት ባለቤት ቢል ጌትስ እና የተስላ ኩባንያ መስራች ኤሎን መስክም ለዚህ ተጠቃሽ ናቸው።

አዜብ አታሮ በዩናይትድ ስቴትስ የኢትዮጵያ እና የኤርትራውያን የልዩ ፍላጎት ማህበረሰብ መስራች ስትሆን፣ ከኦቲዝም ጋር አብሮ የኖረው የ22 ዓመት ልጇ በተለያዩ ሱቆች ውስጥ ተቀጥሮ ሰርቷል። አሁን ደግሞ በኮምፒውተር ዲጂታይዜሽን ሙያ ሰልጥኖ በሆስፒታል ውስጥ እንደሚሰራ ትናገራለች።

ከኦቲዝም ጋር የሚኖሩ ልጆች፣ ካላቸው አቅም እና ፍላጎት ተነስቶ ተገቢው ድጋፍ ከተደረገላቸው ትልቅ ቦታ የመድረስ አቅም እና ችሎታ አላቸው የምትለው አዜብ፣ ዋና ኃላፊነቱ ግን ከወላጆቻቸው እንደሚጀምር ታሰምርበታለች።

ራሔልም ለዚህ ምስክር ናት። በነህምያ ውስጥ ከምታግዛቸው በርካታ ልጆች ጋር፣ ትክክለኛውን ድጋፍ እያገኘ ያደገው ናታን፣ ዛሬ አይችልም ይባል ከነበሩት ውስጥ አብዛኞቹን ማድረግ ችሏል። ራሔል እንደምትለው እድሉን ቢያገኝ ደግሞ ዋናተኛ መሆንም ይችል ነበር።

ከኦቲዝም ጋር የሚኖሩ ልጆችን ለስኬት ለማብቃት የመጀመሪያው መንገድ ወላጆች አይችሉም የሚለውን ከጭንቅላታቸው ማውጣታቸው ነው የምትለው አዜብ ማህበረሰቡም፣ ልጆቹ የማህበረሰቡ አባል መሆናቸውን ተቀብሎ የሚገባቸውን ድጋፍ ማድረግ ይኖረበታል ትላለች፣ በተለይ ደግሞ በትምህርት እና ስልጠና።

ራሔል እና አዜብ ከኦቲዝም ጋር የሚኖሩ ልጆቻቸውን ለስኬት ለማብቃት የሄዱበት ጎዳና ፈተና የበዛበት እና ብዙ ችግሮችን የተጋፈጡበት ይሆን እንጂ የደረሱበት ስኬት ግን ለብዙ እናቶች እና ህፃናት መልስ ሆነዋል። ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች በዚህ እክል ውስጥ ለሚያድጉ ልጆች የስኬት መጀመሪያ መንገድ ሆነውም እያገለገሉ ነው። የሁለቱም ምክር ደግሞ ከኦቲዝም ጋር የሚኖሩ ልጆች የራሳቸው ልዩ ጥንካሬዎች እና ችሎታዎች ስላሏቸው የስኬት መንገዳቸውን እንከፍትላቸው ነው።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG