በሱዳን የቀጠለው ውጊያ፣ አብዛኞቹ ሕፃናት የኾኑትን በሺሕ የሚቆጠሩ ስደተኞች ለደኅንነታቸው ሲሉ ወደ ጎረቤት ደቡብ ሱዳን እንዲሰደዱ እያስገደዳቸው ነው። በእዚያም ግን በእጅጉ እየተዳከመ ያለው የጤና አጠባበቅ ሥርዓት የሚያስፈልጋቸውን ክብካቤ ሊሰጣቸው አልቻለም።
ሱዳን ውስጥ የሚካሔደውን ጦርነት የሚሸሹ ስደተኞች፣ በሱዳንና በደቡብ ሱዳን መካከል መሸጋገሪያ በኾነችው ጆዳ ደርሰዋል።
ከሚሸሹት መካከል የኾነችው የ12 ዓመቷ ብሃኪታ አልሞሃድ፣ የጡት ካንሰር ሕክምና ከተሰጣት በኋላ ብዙም ሳትቆይ አድካሚውን የብዙ ቀን የእግር ጉዞን አድርጋለች።
ብሃኪታ ዛሬ ጤንነት አይሰማትም፡፡ እናቷ ነኢማ አብደላ ስለእርሷ ስትናገር፣ “የጀመራት በአንዳንድ ሽፍታዎች እና በደረት ሕመም ነው፡፡ ከዚያም እንደ ደንጊያ የጠጠረ ከባድ ነገር ወደ መኾን አደገ፤ ቆዳዋም መርገፍ ጀመረ፤ ከዚያም እየባሰና እየከፋ መጣ። ነገሩ መክበዱን የተረዱት ያኔ ነው፤” ትላለች፡፡
ሕፃናት አድን (ሴቭ ዘ ችልድረን) የተባለው የረድኤት ቡድን እንደገለጸው፣ ካለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ጀምሮ ከ600ሺሕ በላይ ሱዳናውያን ስደተኞች እና ደቡብ ሱዳናውያን ከስደት ተመላሾች፣ ወደ ደቡብ ሱዳን ተሻግረዋል።
ቀደሞውንም ከባድ የረኀብ ቀውስ የተጋረጠበት ክልል፣ ከመጠን በላይ ለተጨናነቀ የጤና አጠባበቅ ኹናቴ ተጋልጧል፡፡
ለአዲሶቹ መጤዎች፣ ይህች የድንበር ከተማ ልታደርግላቸው የምትችለው ነገር፣ ከጠበቁት በታች ኾኖባቸዋል።
የላይኛው ናይል ግዛት የማስታወቂያ ሚኒስትር ሉካ ሳዳላ፣ በካምፑ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መኾኑን ይናገራሉ፡፡
"እኤአ እስከ ኅዳር ድረስ፣ 194 የሚኾኑቱን መዝግቤያለሁ፡፡ ከ194ቱ ውስጥ ሁለት ብቻ - አንድ ሴት እና አንድ ወንድ ሲኾኑ፣ አብዛኛዎቹ ግን ሕፃናት ናቸው፤" ብለዋል፡፡
እ.ኤ.አ በ2023 መጀመሪያ ላይ፣ ዓለም አቀፍ ለጋሾች የሚያደርጉትን መዋጮ በቀነሱበት ወቅት፣ የአገሪቱን የጤና ዘርፍ አናግቷል።
የደቡብ ሱዳን የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዮላንዳ አወል ዴንግ፣ ቡድናቸው ከአገሪቱ አጠቃላይ በጀት አነስተኛ ድርሻ እንዲይዝ በማድረግ ክፍተቱን ለመሙላት እየታገለ ነው፤ ሲሉ ያስረዳሉ።
"በውል እንደምታውቁት፣ የጤና ሚኒስቴር በጀት ሁለት በመቶ ወይም አንድ ነጥብ ስምንት በመቶ ብቻ ነው፤” ያሉት ሚኒስትሩ፣ “ያቺኑ አንድ ነጥብ ስምንት በመቶ እንኳ እኛ አናገኛትም፡፡ ያገኘናት ጊዜ ግን፣ የሚያስፈልገንን አቅርቦትና የሠራተኞችን መጠን ከፍ ለማድረግ እናውለዋለን፤ ያሉን በቂ አይደሉም፤” ብለዋል፡፡
በላይኛው ናይል ግዛት የሬንክ ሲቪል ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር አዩኤል ሉኤል፣ የሀገር ውስጥ የሕክምና ተቋማት ሥር የሰደዱ በሽታዎችን ለመቋቋም የሚያስችል ብቃት እንደሌላቸው አብራርተዋል።
ይህንኑ ሲያስረዱም፣ “እንደ የጡት እና የማኅፀን ካንሰር እንዲሁም ለተለያዩ የካንሰር ዓይነቶች የተጋለጡ ታካሚዎች፣ ሌሎችም የኬሞቴራፒ ሕክምና ሲወስዱ የነበሩ እዚኽ ሲመጡ፣ እኛ የወረዳ ሆስፒታል ብቻ ነን፡፡ ስለዚህ አንዳንድ ልንቆጣጠራቸው የማንችላቸው ጉዳዮች አሉ፤” ብለዋል ዳይሬክተሩ፡፡
የባኪታ አልሞሃድ እናት፣ ሴት ልጇን በሕይወት ለማሰንበት፣ በቀን አንድ ጊዜ እንደምትመግባትና ጆዳ ከደረሰች በኋላ ሕመሟ እየተባባሰ መምጣቱን ተናግረዋል።
ከስደተኞቹ አንዳንድ ቤተሰቦች፣ በደቡብ ሱዳን እንደሚቆዩ ይናገራሉ፡፡ እንደ ብሃኪታ ያሉ ሌሎች ደግሞ፣ በአገራቸው ያለው ጦርነት በቅርቡ እንደሚቆምና ያ ሲኾን ወደ ሱዳን ተመልሰው የሚያስፈልጋልቸውን ልዩ ሕክምና እንደሚያገኙ ተስፋ ያደርጋሉ፡፡