በኢትዮጵያ ትልቁ የባቢሌ ዝሆኖች መጠለያ፣ ለኢንቨስተሮች ተቆርሶ የተሰጠው መሬት ቢመለስም አሁንም የቀጠለው ህገወጥ ሰፈራ ህልውናውን ለስጋት እንደዳረገው፣ የመጠለያው ኃላፊ አቶ ባንኪ ቡዳሞ ለአሜሪካ ድምፅ ገልጸዋል።
ከአንድ ዓመት በፊት ከመጠለያ ክፍሉ ተቆርሶ ለግብርና ኢንቨስተሮች የተሰጠው መሬት እንዲመለስ መወሰኑን፣ የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን አስታውቋል፡፡ ዳሩ ግን፣ 75 ከመቶ የመጠለያው ክፍል በሕገ ወጥ በተባሉ ሰፋሪዎች መያዙንና ህልውናው አደጋ ላይ መኾኑን የመጠለያው ኃላፊ አስረድተዋል፡፡
በኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን የብሔራዊ ፓርኮች አስተዳደር መሪ ሥራ አስኪያጅ ዶክተር አዳነ ጸጋዬ ለአሜሪካ ድምፅ እንዳብራሩት፣ ለግብርና ኢንቨስተሮች ከተሰጠው የዝሆኖች መጠለያ ክፍሉ ጋራ በተያያዘ፣ በዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣንና በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን አስተዳደር መካከል ከፍተኛ አለመግባባት ተፈጥሮ ቆይቷል፡፡ የተፈጥሮ ሀብት ተቆርቋሪዎች እና ምሁራን ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ደብዳቤ በመጻፍ ጣልቃ እንዲገቡ ጠይቀዋል። ከብዙ ውዝግብ በኋላም መሬቱ ለመጠለያው እንዲመለስ መወሰኑን ዶክተር አዳነ ተናግረዋል።
በዚኽ መልኩ የግብርና ኢንቨስትመንት ኩባንያው ከመጠለያው እንዲወጣ ቢወሰንም፣ በስፍራው በቆየባቸው ጊዜያት ያካሔደው የደን ምንጣሮ ያስከተለው ውድመት ከፍተኛ መኾኑንና የዱር እንስሳቱን ሕይወት እና ሥነ ምኅዳሩን በአጠቃላይ ለአደጋ ማጋለጡን ዶክተር አዳነ አመልክተዋል። መንግሥት ለኢንቨስተሩ ፈቅዶለት ወደነበረው 200 ሄክታር የሚጠጋ የመጠለያው ክፍል ከገባ በኋላ፣ ለአንድ ዓመት ደኑን መመንጠሩን፣ ከግማሽ ምእት ዓመት በላይ ያስቆጠሩ ዛፎች መቁረጡን እና የተመነጠረውን ቦታ በትራክተር ማረሱን ዶክተር አዳነ አክለዋል።
በተጨማሪም ከኦሮሚያ ክልል የምሥራቅ ሐረርጌ ዞን፣ ከሶማሌ ክልል ደግሞ የፋይዳ እና የረር ዞኖች የሚያዋስኑት የባቢሌ ዝሆኖች መጠለያ፣ በተለይ ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ፣ በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልሎች ተፈጥሮ በነበረው የፖለቲካ አለመረጋጋት ምክንያት፣ ግለሰቦች እየተደራጁ ወደ መጠለያው በመግባት በሕገ ወጥ መንገድ መስፈራቸውን፣ በአሁኑ ወቅትም ከፊል የመጠለያውን ክፍል ሸፍነው እንደሚገኙ፣ የመጠለያ ፓርኩ ኃላፊ አቶ ባንኪ ቡዳሞ ይገልጻሉ።
ከ6ሺሕ980 ስኩዌር ኪሎ ሜትር በላይ ይሸፍን የነበረው መጠለያም፣ በሕገ ወጥ ሰፈራው ምክንያት አብዛኛውን ክፍሉን ማጣቱን እና የዱር እንስሳቱም መሔጃ ስለሚያጡ በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ኃላፊው ተናግረዋል። ለአብነት ያህል፣ በዝሆኖች እና በሰዎች መካከል በሚፈጠር ግጭት፣ በዚኽ ዓመት ብቻ የ13 ሰዎች እና የስድስት ዝሆኖች ሕይወት ማለፉን፣ የመጠለያው ኃላፊ አስታውቀዋል። መጠለያው በምሥረታው ወቅት ከ600 መቶ በላይ ዝሆኖች እንደነበሩት ያወሱት ኃላፊው፣ በአሁኑ ወቅት የቀሩት ግን 300 ብቻ እንደኾኑ አመልክተዋል።
በመጠለያው እጅግ እየተባባሰ የመጣውን ሕገ ወጥ ሰፈራ ለማስቆም፣ የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማት እና ጥበቃ ባለሥልጣን ከሶማሌ እና ኦሮሚያ ክልሎች ባለሥልጣናት ጋራ በመተባበር በ2013 ዓ.ም. ወደ 780 አባወራዎችን ወደ ኦሮሚያ፣ 75 አባወራዎችን ደግሞ ወደ ሶማሌ ክልል እንዲመለሱ ማድረግ ችለው ነበር። ኾኖም ሥራው ተጠናክሮ ባለመቀጠሉና በመሀል ደግሞ የኢንቨስትመንት ተቋሙ መግባቱ ሕገ ወጥ ሰፈራውን እንዳባባሰው ዶክተር አዳነ አስረድተዋል።
ይህ ኹኔታ ሳይገታ ቀርቶ መጠለያው ለከፍተኛ የተፈጥሮ ሀብት መመናመን ከመዳረጉ በፊት፣ አሁንም የክልሎቹ ትብብር እንደሚያስፈልግ፣ ኃላፊው አቶ ባንኪ ቡዳሞ ያሳስባሉ።
በአጭር ጊዜ ውስጥ ርምጃ ተወስዶ በሕገ ወጥ መንገድ የሰፈሩት ነዋሪዎች ካልተነሡ፣ መጠለያው በቅርቡ ታሪክ ሊኾን እንደሚችል የተፈጥሮ ሀብት ባለሞያዎች ያስጠነቅቃሉ፡፡ ለፍጥረተ ዓለም ህልውና መጠበቅ መሠረታዊ የኾነውንና ከፍተኛ የብዝኀ ሕይወት ሀብት የያዘውን የባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ ከጠቅላላ ጥፋት ለመታደግ፣ የኦሮሚያ እና የሶማሌ ክልሎች ባለሥልጣናት ቀና ርብርብ እንደሚያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በኢትዮጵያ ካሉ የዱር እንስሳት መጠበቂያ ፓርኮች ግንባር ቀደሙና ከተመሠረተ ከ50 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ነው፡፡ በምሥራቅ አፍሪካ ብቸኛ የኾኑትን ጥቁር ዝሆኖችን ጨምሮ 31 ጡት አጥቢ እንስሳትንና ከ222 በላይ የአዕዋፍ ዝርያዎች ይገኙበታል፡፡
መድረክ / ፎረም