በሩሲያ እስር ቤት ውስጥ ትናንት አርብ ሞተዋል ለተባሉት የተቃዋሚ መሪ አሌክሲ ናቫልኒ መታሰቢያ ዛሬ ቅዳሜ በተለያዩ የሩሲያ ግዛቶች አበቦችን ያኖሩ ከ100 በላይ ሰዎች ተይዘዋል ሲል አሶሴይትድ ፕሬስ ዘግቧል።
በመታሰቢያነት የተቀመጡ አበቦችም በፖሊሶች በተመሩ ሰዎች እንዲነሱ መደረጋቸውም ተነግሯል፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስ ፣ እስር ቤት ውስጥ ለሞቱት የሩሲያው ተቃዋሚ መሪ አሌክሲ ናቫልኒ ሞት ተጠያቂው የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ናቸው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ባይደን በዋይት ሀውስ ትናንት በሰጡት መግለጫ የናቫልኒን ጀግንነት አድንቀው “የሩሲያ መሪዎች የራሳቸውን ትርክት ሊናገሩ ይችላሉ፣ ለናቫልኒ ሞት ግን በቀጥታ ተጠያቂው ያለምንም ጥርጥር ፕሬዚዳንት ፑቲን ናቸው” ብለዋል።
ከፍተኛ ፀረ-ክሬምሊን ተቃውሞዎችን የመሩት ናቫልኒ የሩሲያውን ፕሬዝዳንት ፑቲንን እና ሙስናን በከፍተኛ ደረጃ በመቃወማቸው የ19 ዓመት እስራት የተፈረደባቸው የፖለቲካ እስረኛ ነበሩ፡፡
የናቫልኒ ሞትና አሟሟት በገለልተኛ አካል አለመረጋገጡ የተዘገበ ሲሆን፣ የሩሲያ ፌደራል ማረሚያ ቤት ትናንት አርብ የእግር ጉዞ ካደረጉ በኃላ ጤንነት እንዳልተሰማቸው እና ራሳቸውን እንደሳቱ አስታውቋል።
የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤቱ አፈ-ጉባዔ ማይክ ጆንሰን “ፑቲን ክፉ አምባገነን ናቸው” ብለዋል፡፡ የቀድሞ አፈ-ጉባዔ ናንሲ ፐሎሲ ደግሞ “ፑቲን የሀሳብ ልዩነትን ዝም ለማሰኘት የወሰዱት እምርጃ ነው ሲሉ ለቪኦኤ ተናግረዋል፡፡
የናቫልኒ ባለቤት ዩሊያ፣ “የናቫልኒ ሞት ዜና እውነት ከሆነ ፑቲንን፣ አጃቢዎቻቸውን፣ የፑቲን ጓደኞቻቸውን፣ መንግስታቸው በሀገራችን፣ ቤተሰቤ እና ባለቤቴ ላይ ላደረሱት ነገር ኃላፊነቱን እንደሚወስዱ እንዲያውቁ እፈልጋለሁ።” ሲሉ ትናንት አርብ በሙኒክ የፀጥታው ጉባኤ ላይ ተናግረዋል፡፡
መድረክ / ፎረም