የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጠንካራ ተቃዋሚ የነበሩትና፣ ሙስናን ተቃውመው ከፍተኛ ፀረ-ክሬምሊን ተቃውሞዎችን የመሩት አሌክሲ ናቫልኒ፣ አርብ እለት በእስር ቤት መሞታቸውን የሩሲያ ባለስልጣናት አስታወቁ።
የሩሲያ ፌደራል ማረሚያ ቤት በሰጠው መግለጫ፣ የ47 አመት እድሜ ያላቸው ናቫልኒ አርብ እለት የእግር ጉዞ ካደረጉ በኃላ ጥሩ ስሜት እንዳልተሰማቸው እና እራሳቸውን እንደሳቱ አስታውቋል። ተጠርቶ የመጣው አምቡላንስ እርዳታ ሊያደርግላቸው ቢሞክርም ህይወታቸው ሊተርፍ አልቻለም። የሞታቸው ምክንያት "እየተጣራ ነው" ሲል መግለጫው ጨምሮ ገልጿል።
የናቫሊ ቃል አቀባይ በኤክስ የማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ የፖለቲካ ቡድናቸው እስካሁን ስለመሞታቸው ማረጋገጫ አለማግኘቱን እና ጠበቃቸው ታስረውበት ወደነበረው ከተማ እየተጓዙ መሆናቸውን አመልክተዋል።
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሜትሪ ፔስኮቭ በበኩላቸው ፑቲን ስለናቫሊ መሞት እንደተናገራቸው ገልፀው፣ ጉዳዩን ማረሚያ ቤቱ በመደበኛ አሰራሩ መሰረት ይመለከተዋል ብለዋል።
ናቫልኒ እ.አ.አ በ2021 በጀርመን ተይዘው ወደ ሞስኮ ከተመለሱ በኃላ በፅንፈኝነት ተከሰው የ19 አመት እስራት ተፈርዶባቸው ነበር። ከመታሰራቸው በፊት ሙስናን የሚቃወሙ እና ፀረ-ክሬምሊን ተቃውሞዎችን ያዘጋጁ የነበረ ሲሆን፣ በምርጫም ተወዳድረዋል።
ናቫሊ ቀደም ሲል ታስረውበት ከነበረ በማዕከላዊ ሩሲያ የሚገኝ ማረሚያ ቤት፣ ከፍተኛ ጥበቃ ወደሚደረግበት "ልዩ እስርቤት" የተዛወሩት በታህሳስ ወር ነበር።
ከሞስኮ 40 ኪሎሜትር ያክል ወጣ ብላ በምትገኘው ቡቲን ከተማ የተወለዱት ናቫልኒ፣ የህግ ዲግሪያቸውን እ.አ.አ በ1998 ሩሲያ ውስጥ ያገኙ ሲሆን፣ ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው ዬል ዩንቨርስቲም እ.አ.አ 2010 የአጭር ጊዜ ትምህርት ተከታትለዋል።
መድረክ / ፎረም