ሱዳን የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ከፈጥኖ ደራሹ ጦር አዛዥ መሀመድ ሀምዳን ዳጋሎ ጋር ያደረጉትን ንግግር በመቃወም ናይሮቢ የሚገኙ አምባሳደሯን ትናንት ሐሙስ ጠርታለች፡፡
ካለፈው ሚያዝያ ጀምሮ በአብደል ፋታህ አል-ቡርሃን ከሚመራው መደበኛ ጦር ጋር ጦርነቱ ውስጥ የገቡት ዳጋሎ፣ በግጭቱ ውስጥ የመጀመሪያቸው የሆነውን ጉብኘታቸውን በምስራቅ አፍሪካ አገሮች አካሂደዋል፡፡
ቀደም ሲል ዩጋንዳ፣ ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ እንዲሁም ኬንያን የጎበኙት ዳጋሎ በአሁኑ ወቅት ደቡብ አፍሪካ ይገኛሉ ሲል ኤኤፍፒ በትናንት ሐሙስ ዘገባው አመልክቷል፡፡
በቅርብ ወራት ውስጥ አንዳንድ ይዞታቸውን በፈጥኖ ደራሹ ጦር አጥተዋል የተባሉት አል ቡርሃን በጉብኝቱ ያልተደሰቱ ሲሆን፣ ደጋሎ ዓለም አቀፍ እውቅና እንዳያገኙ ፍላጎት እንዳላቸው ዘገባው አመልክቷል፡፡
በሱና ዜና አገልግሎት የወጣው የሱዳን ተጠባባቂ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሊ አል ሳዲቅ መግለጫ “አምባሳደሩ የተጠሩት የኬንያ መንግሥት ለአማፂ ሚሊሻው መሪ ያደረገውን ይፋዊ አቀባበል በመቃወም ማብራሪያ እንዲሰጡ ነው” ብሏል፡፡
ግጭቱን ለመሸምገል የምትሻው ኬንያ ከዳጋሎ ጋር የግንኙነት መስመሮችን ሁሉ ክፍት በማድረጓ በአል ቡርሃን እና በናይሮቢ መንግሥት መካከል ያለው ግንኙነት ለወራት ሻክሮ መቆየቱ ተነግሯል፡፡
በሁለቱ ጀኔራሎች መካከል ሱዳን ውስጥ በተፈጠረው የሀገር ውስጥ ግጭት በጥንቃቄ በተወሰደ ግምት ከ12,190 በላይ ሰዎች መገደላቸው ተመልክቷል፡፡
የቡርሃን አስተዳደር እንደ ሱዳን መንግስት መግለጫዎችን ማውጣቱን ቢቀጥልም የዳጋሎ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች የካርቱምን ጎዳናዎችን እንዲሁም ሁሉንም የዳርፉር መንገዶች እና ለሱዳን የዳቦ ቅርጫት ናት የምትባለውን አብዛኛውን የአልጃዚራ ማእከላዊ ግዛት እንደሚቆጣጠሩ ተነግሯል፡፡
በሁለቱ የሱዳን ጀኔራሎ መካከል የተካረረው ጥላቻ በማየሉ ግጭቱን ለማስቆም የሚደረጉ የሽምግልና ጥረቶች መገታታቸው ተገልጿል፡፡
በሌላም በኩል በተባበሩት መንግሥታት ሰብዓዊ ጉዳዮች ምክትል ዋና ጸሃፊ ማርቲን ግሪፊትስ 9 ወራት የፈጀው የሱዳን ጦርነት፣ ሀገሪቱን በየቀኑ ወደ ከፋ መቀመቅ እየከታት ነው ማለታቸውን የመንግሥታቱ ድርጅቱ ቃል አቀባይ ትናንት ሐሙስ ኒው ዮርክ ውስጥ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቃል አቀባይ ስቴፋኒ ትሬምሌይ ትናንት ታህሳስ 26 በሰጡት መግለጫ “በዚህ ዓመት ሱዳን ውስጥ ወደ 25 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ሰብአዊ ርዳታ ያስፈልጋቸዋል - ይሁን እንጂ ግን እየተባባሰ የመጣው ግጭት አብዛኞቹን ከአቅማችን በላይ እያደረጋቸው ነው” ብለዋል።
ግሪፍትስ በግጭቱ ውስጥ ያሉ ወገኖች ሰላማዊ ሰዎችን ደህንነት እንዲጠብቁ፣ ሰብአዊአገልግሎትተደራሽነት እንዲኖርና እና ጦርነቱን በአስቸኳይ እንዲያቆሙ ጠይቀዋል።”
“ግሪፍትስ በግጭቱ ውስጥ ያሉ ወገኖች ሰላማዊ ሰዎችን ደህንነት እንዲጠብቁ፣ ሰብአዊአገልግሎትተደራሽነት እንዲኖርና እና ጦርነቱን በአስቸኳይ እንዲያቆሙ ጠይቀዋል።” ሲሉም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል፡፡
“እኤአ በ2024፣ ዓለም አቀፉ ማበረሰብ በተለይም በሱዳን ግጭት ውስጥ ባሉ አካላት ላይ ተጽእኖ የሚያሳድሩ - ጦርነቱን ለማስቆም እና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሲቪሎችን ለመርዳት የታሰቡ ሰብአዊ ተግባራትን ለመጠበቅ “ቆራጥ እና አፋጣኝ” እርምጃ መውሰድ አለባቸው ሲሉ ግሪፍትስ መጠየቃቸውም በቃል አቀባዩ መግለጫ ተመልክቷል፡፡
መድረክ / ፎረም