በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በደብረ ብርሃን የተኩስ ልውውጥ ንጹሃን መሞታቸው ተገለፀ


በደብረ ብርሃን የተኩስ ልውውጥ ንጹሃን መሞታቸው ተገለፀ
please wait

No media source currently available

0:00 0:06:05 0:00

በአማራ ክልል፣ ሰሜን ሸዋ ዞን፣ በደብረ ብርሃን ከተማ ትናንት ረቡዕ በተቀሰቀሰ የተኩስ ልውውጥ የሞትና የአካል ጉዳት

መድረሱን ነዋሪዎችና የአካባቢው ኮማንድ ፖስት ጠቁመዋል።

ከንጋት ጀምሮ እስከ እኩለ ቀን ገደማ የዘለቀ የተኩስ ልውውጥ እንደነበር አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የከተማዋ ነዋሪ ተናግረዋል፡፡

ውጊያው “በአካባቢው በነበሩት የመንግሥት ፀጥታ አካላትና በፋኖ መካከል ሳይሆን አይቀርም” ያሉት ግለሰቡ እስከ እኩለ ቀን ድረስ የሰውና የተሸከርካሪ እንቅስቃሴ ቆሞ ማርፈዱን ጠቁመዋል፡፡

ለደህንነታቸው ስማቸው እንዳይገለጽ ያሳሰቡ ሌላው የከተማዋ ነዋሪ “በከተማዋ የተለያዩ ቦታዎች ተኩስ ነበር ፡ ሰላማዊ ሰዎች ሞተዋል” ሲሉ ብለዋል፡፡

የሟቾቹን ቁጥር በተመለከተ ከደብረ ብርሃን ሆስፒታልም ሆነ ከከተማዋ ከንቲባ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡

ሆኖም የደብረ ብርሃንና አካባቢው ኮማንድ ፖስት ዛሬ ታህሳስ 25/2016ዓ.ም ባወጣው መግለጫ “ጽንፈኛ” ሲል የጠራቸውና በስም ያልጠቀሳቸው ኃይሎች ያደረሱት ባለው “እኩይ ተግባር ሰዎች ሞተዋል” ብሏል፡፡ ምን ያህል ሰዎች እንደሞቱ ግን በቁጥር አላስቀመጠም፡፡

ከተማዋ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ መግባቷንና የመንግስት ተቋማት፣ ሱቆች ፣ ባንኮች፣ ሆቴሎች እና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ወደ መደበኛ እንቅስቃሴያቸው መመለሳቸውም አክሎ አመልክቷል፡፡

አስተያየታቸውን የሰጡን የከተማዋ ነዋሪም ይኼንኑ አረጋግጠዋል፡፡

ወቅታዊውን የጸጥታ ሁኔታ መሰረት በማድረግ ከትናንት ታህሳስ 24/2016ዓ.ም ጀምሮ በከተማዋ ለሁለት ቀናት የባጃጅ እንቅስቃሴ እንዳይኖር ኮማንድ ፖስቱ ገደብ ማውጣቱን የደብረ ብርሃን መንግሥት ኮሙኒኬሽን መምሪያ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ላይ አስፍሯል፡፡

በተመሳሳይ ዜና በአማራ ክልል፣ ሰሜን ወሎ ዞን፣ሃብሩ ወረዳ፣ መርሳ ከተማ አቅራቢያ፣ ቡሆሮ በተባለች የገጠር ቀበሌ ከትናንት በስቲያ ታህሳስ 23/2016ዓ.ም በመንግስት የጸጥታ ኃይሎችና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ለሰዓታት የዘለቀ የተኩስ ልውውጥ እንደነበር ስማቸውን ከመግለጽ የተቆጠቡ አንድ የአካባቢው ነዋሪ ተናግረዋል፡፡ በዚህም የአካል ጉዳት መድረሱንና ንብረት መውደሙን አመልክተዋል፡፡

ቪኦኤ በስልክ ያገኛቸው የሃብሩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ሁሴን መሐመድ “በአካባቢው የጸጥታ ችግር ነበር ነገር ግን በተኩስ ልውውጡ የሞተ ሰው የለም” ብለዋል፡፡ አካባቢውም ወደ መረጋጋት ተመልሷል ሲሉም አክለዋል፡፡

በተመሳሳይ ከትናንት በስቲያ ከደሴ 65 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምትገኘውና በሰሜን ወሎ ዞን ሃብሩ ወረዳ ስር ባለችው ውርጌሳ ከተማ የተኩስ ልውውጥ እንደነበር የአካባቢው ነዋሪ አስታውቀዋል፡፡

በዚህም ለገበያ በወጡ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሶ ወደ ደሴ መላካቸውን አንድ የውርጌሳ ከተማ ኗሪ ገልጸዋል፡፡

በክልሉ በቀጠለው የጸጥታ ችግር ምክንያት በተለይ አርሶ አደሩ እየተጎዳ መሆኑን በደህንነት ስጋት ምክንያት ስማቸው እንዳይጠቀስ የገለጹ በሰሜን ወሎ ሃርቡ ወረዳ የቡሆሮ ቀበሌ አርሶ አደር ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ወቅታዊ የጸጥታ ጉዳይ ላይ ሰሞኑን ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስቴሩ ዶክተር ለገሰ ቱሉ “መንግሥት በክልሉ ላይ ተጋርጦ የነበረውን የህልውና ስጋት ሙሉ በሙሉ ቀልብሷል” ማለታቸው ይታወሳል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና ከተማ በሆነችው ደብረብርሃን የተኩስ ልውውጥ መደረጉ የተገለጸው በሌላዋ የዞኑ ትልቅ ከተማ ሸዋ ሮቢት ተመሳሳይ ግጭት መፈጠሩ በተገለጸ በቀናት ጊዜ ውስጥ ነው።

የዚህን ዘገባ ዝርዝር ከተያያዘው ፋይል ያድምጡ፡፡

XS
SM
MD
LG