በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ስምምነቱን የተቃወመችው ሶማሊያ አምባሳደሯን ጠራች


ስምምነቱን የተቃወመችው ሶማሊያ አምባሳደሯን ጠራች
please wait

No media source currently available

0:00 0:07:14 0:00

ስምምነቱን የተቃወመችው ሶማሊያ አምባሳደሯን ጠራች

ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችውን የመግባቢያ ሰነድ ውድቅ ያደረገችው ሶማሊያ በአዲስ አበባ የሚገኙትን አምባሳደሯን ጠርታለች።

በመግባቢያ ሰነዱ ላይ ተቃውሞውን የገለፀው የሶማሊያ መንግሥት ሥምምነቱ “ሉዓላዊነቴን የሚጻረር እና ተቀባይነት የሌለው ነው” ብሏል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት እና የአፍሪካ ሕብረትን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ የሶማሊያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ለማስጠበቅ ጫና እንዲያሳድሩም ጥሪ አቅርቧል፡፡

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ዓለም አቀፍ እውቅና ያልተሰጣት የራስ ገዟ ሶማሌላንድ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሂ አብዱ፣ ትላንት ታኅሳስ 22 ቀን 2016 ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ ስምምነቱን ተፈራርመዋል፡፡

የመግባቢያ ስምምነቱ ለኢትዮጵያ የባሕር በር የሚያስገኝላት መሆኑን የኢትዮጵያ መንግሥት ሲገልጽ፣ ሶማሌ ላንድ ደግሞ አዲስ አበባ የነጻ ሀገር ዕውቅና ልትሰጣት መስማማቷን አስታውቃለች።

ኢትዮጵያ እስካሁን ለሶማሊላንድ የነጻ ሀገርነት እውቅና ለመስጠት ተስማምታለች መባሉን በተመለከተ በይፋ የገለጸችው ነገር የለም። ከሶማሊያ መንግሥት በኩል ለተሰነዘረው ቅዋሜም ምላሽ አልሰጠችበትም፡፡

የሶማሊላንዱ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሂም በቀድሞው ትዊተር በአሁኑ “ኤክስ” ገጻቸው “በስምምነቱ መሰረት ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ ሪፐብሊክ በይፋ እውቅና ስትሰጥ ሶማሊላንድ ደግሞ ከግዛቷ ላይ በ50 ዓመት ሊዝ ለኢትዮጵያ ትሰጣለች” ብለዋል፡፡

ስምምነቱ “ከኢትዮጵያና ሶማሊላንድ ባለፈ፣ ለቀጣናው ውህደትና እድገትም ጉልህ ፋይዳ” ያለው ሁለቱ መንግሥታት ገልጸዋል፡፡

ስምምነቱን የተቃወመው የሶማሊያ መንግሥት "የኢትዮጵያ ድርጊት መልካም ጉርብትናን፡ ሰላምና መረጋጋትን አደጋ ላይ ይጥላል" ሲል በቃል አቀባዩ ፋርሃን ጂማሌ በኩል አስታውቋል፡፡

የሀገሪቱ መንግሥት ካቢኔ ዛሬ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ፣ ሕጋዊ የመግባቢያ ስምምነት በፅኑ እንደሚያወግዝ አስታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ እርምጃ የሶማሊያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት የሚጥስ “ግልፅ ጥቃት ነው” ብሏል፡፡

"የኢትዮጵያ እና የሶማሌላንድ ስምምነት ፤የሶማሊያን ሉዓላዊነት እና አለም አቀፍ ህግን የሚጻረር ነው”

የሶማሊያ ፕሬዝደንት ሀሰን ሼኽ መሀሙድ ለሀገራቸው ፓርላማ ባደረጉት ንግግር፣ "የኢትዮጵያ እና የሶማሌላንድ ስምምነት ፤የሶማሊያን ሉዓላዊነት እና አለም አቀፍ ህግን የሚጻረር ነው” ሲሉ አውግዘዋል። የሶማሊያ ህዝብ “በጋራ ቆሞ የውጭ ጣልቃ ገብነትን በመከላከል አንድነቱን እንዲጠብቅ” ሲሉም አሳስበዋል።

ፕሬዚዳንቱ ቀድሞ ትዊተር በአሁኑ ኤክስ ገጻቸው ላይ “እንደ መንግስት በትላንትናው እለት ኢትዮጵያ በብሄራዊ ሉዓላዊ ግዛታችን እና ግዛታችን ላይ የፈጸመችውን ህገወጥ ጥሰት አውግዘናል፤ ሶማሊያ የሶማሌ ህዝብ ነች።” ብለዋል፡፡

በሶማሊያ ህገ መንግሥት መሠረት ሶማሊላንድ የሶማሊያ አካል ነች ያለው የሶማሊያ መንግሥት፣ የትላንቱን ስምምነት በመቃወም፣ በኢትዮጵያ የሚገኘውን አምባሳደሩን” ለምክክር” በሚል ጠርቷል፡፡

የሶማሊያ መንግሥት፣ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ለአፍሪካ ህብረት፣ ለአረብ ሊግ እና ለቀጣናዊው የምስራቅ አፍሪካ ቡድን ኢጋድ እና ሌሎችም “ሶማሊያ ሉዓላዊነቷ እንዲቀጥል እና ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ህጎችን እንድታከብር ከጎኔ ቁሙ” የሚል ጥሪ ማቅረቡንም የሀገሪቱ የዜና ወኪል ዘግቧል፡፡

ሶማሊያ ሉዓላዊነቷ እንዲቀጥል እና ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ህጎችን እንድታከብር ከጎኔ ቁሙ”

ከተጠቀሱት ዓለም አቀፍ ተቋማትም ይሁን ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል፣ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ በይፋ የተሰጠ ምላሽ የለም፡፡ የአሜሪካ ድምፅ ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለስልጣናት ተጨማሪ አስተያየትና ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ሙከራም ለጊዜው አልተሳካም፡፡

የሶማሌላንድ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሂ አብዱ፣ በኢትዮጵያ የሥራ ጉብኝት ላይ ናቸው፡፡

በስምምነቱ ዙሪያ የምሁራን አስተያየቶችን ያካተተውን ዘገባ ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG