የሃማስ ታጣቂ ቡድን በእሥራዔል ላይ የፈፀመውን ድንገተኛ ጥቃት ተከትሎ የእስራኤል መንግሥት በይፋ ጦርነት ካወጀ በኋላ፣ የተለያዩ ሀገራት መሪዎች አስተያየታቸውን እየሰጡ ይገኛሉ።
በእሥራዔል እና በሃማስ ታጣቂዎች መካከል ጋዛ ላይ በታወጀው ጦርነት ዙሪያ አስተያየታቸውን ከሰጡ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች መካከል፣ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር የሆኑት ሙሣ ፋኪ ማሃማት "የእሥራዔል-ፍልስጥዔም ቋሚ ውጥረት ዋናው ምክንያት የፍልስጥዔም ህዝብ መሠረታዊ መብቶቹን፣ በተለይም ነፃና ሉዓላዊ መንግሥት መነፈጉ ነው" ብለዋል።
የዩጋንዳ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቨኒ በበኩላቸው "በእሥራዔል እና በፍልስጤም መካከል እንዳዲስ ግጭት መቀስቀሱ የሚያሳዝን ነገር ነው። ለምን ሁለቱም ወገኖች የሁለት መንግስት መፍትሄን ተግባራዊ አያደርጉም? በተለይ ደግሞ ሰላማዊ ዜጎችን እና ተዋጊ ያልሆኑ አካላት በታጣቂዎች ዒላማ መደረጋቸው መወገዝ አለበት" ብለዋል።
"ይህን አሰቃቂ ጥቃት ያቀዱትን፣ በገንዘብ የደገፉትን እና የፈፀሙትን እናወግዛለን" ያሉት ደግሞ የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋና ፀሃፊ ኮሪር ሲኞኦኢ ሲሆኑ "እሥራዔል የአፀፋ እርምጃ የመውሰድ መብት ቢኖራትም፣ ይህ አሳዛኝ ሁኔታ በሰላማዊ መንገድ መፈታት እንዳለበት እናሳስባለን" ብለዋል።
የሃማስን ጥቃት ተከትሎ፣ የእሥራዔል ምክርቤት ሀገሪቱ በምትወስደው አፀፋዊ እርምጃ ዙሪያ ድምፅ እንዲሰጥ እየተጠበቀ ቢሆንም፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ "እሥራዔል በሃማስ ላይ ትልቅ የበቀል እርምጃ ትወስዳለች" ሲሉ እስራዔል ጦርነት ላይ መሆኗን ቅዳሜ እለት አውጀዋል።
በጥቃቱ 444 ወታደሮችን ጨምሮ፣ እስካሁን ቢያንስ 600 እሥራዔላውያን መገደላቸውን እና ከአንድ ሺህ 500 በላይ ደግሞ መቁሰላቸውን እሥራዔል አስታውቃለች። የጋዛ ባለስልጣናት በበኩላቸው በግዛታቸው ውስጥ 313 ሰዎች መሞታቸውን እና 2ሺህ ሰዎች መቁሰላቸውን ይፋ ቢያደርጉም፣ የእሥራዔል ባለስልጣናት 400 ታጣቂዎችን መግደላቸውን እና በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎችን መማረካቸውን ተናግረዋል።
መድረክ / ፎረም