በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

እንደራሴዎችን ጨምሮ፣ የታሰሩ ሰዎችን ቤተሰብ እንዲያገኛቸው ከፖሊስ ጋር መግባባት ላይ እንደተደረሰ ኢሰመኮ አስታወቀ



የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን መለዮ
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን መለዮ

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዛሬ ባወጣው መግለጫ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት አባል አቶ ዮሐንስ ቧያለው፣ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባል ዶ/ር ካሳ ተሻገር፤ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አባል አቶ ስንታየሁ ቸኮል፣ በአማራ ክልል በኃላፊነት ይሠሩ የነበሩት አቶ ከፋለ እሱባለው፣ እንዲሁም የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያ የሆነውን በቃሉ አላምረውን ጨምሮ ከአዲስ አበባ ከተማና ከአማራ ክልል የተለያዩ ቦታዎች የተያዙ 53 ወንድ እስረኞች፤ አዋሽ አርባ ተወስደው በእስር ላይ እንደሚገኙ አስታውቋል፡፡

አዋሽ አርባ አካባቢ በሚገኘው የሀገር መከላከያ የምዕራብ ዕዝ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ካምፕ ውስጥ ተይዘው የሚገኙትን እነዚህን ታሳሪዎች፣ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለን ጨምሮ 5 የኮሚሽኑ ባለሙያዎች ትላንት ነሐሴ 26 ቀን 2015 ዓ.ም. መጎብኘታቸው በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡

እጅግ አብዛኛዎቹ ታሳሪዎች ለእስር የተዳረጉት በብሔር ማንነታቸው ብቻ መሆኑን እንደሚያምኑ የገለጸው ኢሰመኮ፣ ከፊሎቹ በቁጥጥር ስር በሚውሉበት ወቅት የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደተፈጸመባቸው፤ ሆኖም በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከሆኑ በኋላ የተፈጸመ ድብደባ ወይም አካላዊ ጥቃት አለመኖሩን ተናግረዋል ብሏል፡፡

አሁን የሚገኙበት ስፍራ ፣ ከፍተኛ ሙቀት ያለው በመሆኑና መደበኛ የተጠርጣሪዎች ማቆያ ስፍራ ስላልሆነ ለጤንነታቸው፣ ለደኅንነታቸውና ለሕይወታቸው ሥጋት እንዳላቸው፣ ከቤተሰብም ጋር መገናኘት እንዳልቻሉ መግለጻቸውንም አመልክቷል፡፡

የፖሊስ ኃላፊዎች በበኩላቸው፣ ታሳሪዎቹ ወደ አሽ አርባ የተዛወሩት አዲስ አበባ የሚገኘው የፌዴራል ፖሊስ ማቆያ ጣቢያ ላይ ከፍተኛ መጣበብ በመፈጠሩ መሆኑን፣ ለአየር ሁኔታው አንጻርም የተሻለ በሆነ ሰፊ አዳራሽ ውስጥ አብረው የተያዙ መሆኑን ስለመግለጻቸው ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡

ምግብና ሕክምናን ጨምሮ የተለያዩ አገልግሎቶች እንደሚቀርቡላቸውም እንዲሁ፡፡

ከቤተሰብ ጋር የሚገናኙበት ሁኔታ እንዲመቻች መግባባት ላይ መደረሱንም የኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ክትትልና ምርመራ ሥራ ክፍል ከፍተኛ ዳይሬክተር ዶ/ር ሚዛኔ አባተ ተናግረዋል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG