በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ለዐማራ ክልል ግጭት ሰላማዊ መፍትሔ ጥረት እየተደረገ እንደኾነ ደመቀ መኰንን ተናገሩ


ለዐማራ ክልል ግጭት ሰላማዊ መፍትሔ ጥረት እየተደረገ እንደኾነ ደመቀ መኰንን ተናገሩ
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:58 0:00

ለዐማራ ክልል ግጭት ሰላማዊ መፍትሔ ጥረት እየተደረገ እንደኾነ ደመቀ መኰንን ተናገሩ

መንግሥት፣ በዐማራ ክልል በአገር መከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂ መካከል የተስፋፋውን ግጭት፣ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ፣ አቶ ደመቀ መኰንን ገለጹ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኰንን፣ በዐዲስ አበባ ለሚገኙ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት፣ በክልሉ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ፣ ዛሬ ማክሰኞ፣ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

አቶ ደመቀ በማብራሪያቸው፣ መንግሥት እስከ አሁን በወሰዳቸው ርምጃዎች፣ ለውጥ እንደመጣ ገልጸዋል

ከአቶ ደመቀ የመግቢያ ንግግር በኋላ፣ ለብዙኀን መገናኛ ዝግ በነበረው በዚኹ ውይይት ላይ ስለተነሡ ዝርዝር ጉዳዮች፣ እስከ አኹን የወጣ መረጃ የለም፡፡

በአንጻሩ፣ መንግሥት፣ ለዐማራ ክልል ችግር ሰላማዊ መፍትሔን ከመሻት ይልቅ፣ የኀይል ርምጃን ተመራጭ አድርጓል፤ ሲሉ የሚተቹ አካላት አሉ፡፡

በርካታ ዓለም አቀፍ እና የሀገር ውስጥ አካላትም፣ አሳስቦናል ያሉት በክልሉ የተስፋፋው ግጭት፣ በውይይት እንዲፈታ መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኰንን፣ በዐዲስ አበባ ለሚገኙ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት፣ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ በሰጡት ማብራሪያ፣ ስለ ዐማራ ክልል ወቅታዊ ኹኔታ እና ክልሉን ለማረጋጋት መንግሥት እየወሰዳቸው ስላሉ ርምጃዎች፣ ገለጻ አድርገዋል፡፡

በመንግሥት የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጸደቀበት ማግስት፣ ዛሬ ነሐሴ 9 ቀን 2015 ዓ.ም. አቶ ደመቀ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሰጡት በዚኹ ማብራሪያቸው፣ “ግጭቱን ተከትሎ፣ መንግሥት፥ ሕግንና ሥርዐትን የማስከበር ርምጃዎችን ወስዷል፤” ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል፣ ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም አመልክተዋል፡፡

የመንግሥት “የሰላማዊ ጥረት መፍትሔ”፣ ሽማግሌዎችን፣ የሃይማኖት አባቶችን፣ ምሁራንን፣ ወጣቶችንና ሴቶችን በማሳተፍ፣ ለክልሉ ውጥረቶች እልባት ለማስገኘት ጥረት የሚደረግበት እንደኾነ፣ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

አቶ ደመቀ ይህን ይበሉ እንጂ፣ መንግሥት፣ ለክልሉ ግጭት ሰላማዊ መፍትሔን ከመሻት ይልቅ የኀይል ርምጃን ተመራጭ አድርጓል፤ ሲሉ የሚተቹ አሉ፡፡

ከተቺዎች መካከል አንዱ፣ የቀድሞው የክልሉ ርእሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ናቸው፡፡ በክልሉ ላይ የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ለማጽደቅ፣ ትላንት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በረቂቁ ላይ ውይይት ሲደረግ፣ “መንግሥት ራሱ የፈጠራቸውን የፖለቲካ ችግሮች በውይይት ከመፍታት ይልቅ፣ የኀይል ርምጃን ምርጫው አድርጓል፤” ሲሉ ተቃውመዋል፡፡

ይህም፣ የብልጽግና ፓርቲ መሩ መንግሥት፣ “ካለፉት አምስት ዓመታት ስሕተቶቹ አለመማሩን የሚያሳይ ነው፤” ሲሉ፣ የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በኋላም የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደኅንት አማካሪ አቶ ገዱ ወቅሰዋል፡፡

ለችግሩ እልባት መስጠት ካስፈለገ፣ መከላከያ ሠራዊት ከክልሉ ወጥቶ ወደ ካምፑ መመለስ እንዳለበት፣ አቶ ገዱ ተናግረዋል፡፡ በራሳቸውም ከፍተኛ ሚና በተመሠረተው በብልጽግና ፓርቲ የሚመራው የክልሉ መንግሥት ፈርሶ፣ “ኹሉን አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር” እንዲቋቋም ጠይቀዋል፡፡ በክልሉ የተፈጠረው ችግርም ሊፈታ የሚችለው፣ በፖለቲካዊ ውይይት ብቻ እንደኾነም አብራርተዋል፡፡

በርካታ ዓለም አቀፍ እና የሀገር ውስጥ አካላትም፣ “አሳስቦናል” ያሉት የክልሉ ግጭት፣ በውይይት እንዲፈታ መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ፣ የአውስትራሊያ፣ የጃፓን፣ የኒውዚላንድ እና የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥታት፣ ባለፈው ሳምንት ዐርብ፣ ነሐሴ 5 ቀን 2015 ዓ.ም. በጋራ ባወጡት መግለጫ፣ “ኹሉም ወገኖች፣ ውስብስብ ጉዳዮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እንዲተባበሩ” ጥሪ አስተላልፈዋል።

በኢትዮጵያ የአውሮፓ ኅብረት ልዑክ እና 19 የአውሮፓ ሀገራት ኤምባሲዎችም፣ በዚያው ቀን ተመሳሳይ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትሩ አቶ ተስፋዬ በልጂጌ በበኩላቸው፣ ትላንት ለምክር ቤቱ አባላት በሰጡት ማብራሪያ፣ “ለዐማራ ክልል የጸጥታ መደፍረስ መፍትሔው፣ ሰላማዊ ውይይት እንደኾነ” መንግሥት በጽኑ እንደሚያምን ገልጸዋል፡፡ ይህን ኹኔታ ለመፍጠር ግን፣ በቅድሚያ፣ በክልሉ ሰላምን ማምጣት እንደሚያስፈልግ፣ አቶ ተስፋዬ አመልክተዋል፡፡

ከአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ ድንጋጌ በኋላ፣ በመከላከያ ሠራዊት ኀይል በተወሰዱ ርምጃዎች መጥቷል ያሉትን አንጻራዊ ሰላም ለማጠናከር የዐዋጁ መጽደቅ አስፈላጊ እንደኾነም አጽንዖት ሰጥተዋል፡፡

አቶ ደመቀ መኰንንም በዛሬው ማብራሪያቸው፣ እስከ አሁን በመንግሥት የተወሰዱ ርምጃዎች፣ ዋና ዋና ከተሞችን ጨምሮ በአብዛኛው የክልሉ አካባቢዎች መረጋጋትን እንደፈጠሩ፣ አቶ ደመቀ መኰንን ተናግረዋል፡፡ ይህን ተከትሎ የአየር ትራንስፖርት በመጀመሩ፣ በርካታ የውጭ ሀገራት ዜጎች፣ ክልሉን ለቀው መውጣት እንደቻሉም ገልጸዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አክለውም፣ ኢትዮጵያ፥ “ይህን ፈታኝ ጊዜ፣ በትዕግሥት እና በሰላማዊ መንገድ ዘላቂ መፍትሔ በማምጣት በድል ታልፈዋለች፤” ብለዋል፡፡

ለሌሎችም በሀገሪቱ ላሉ በርካታ ጥያቄዎች ዘላቂው መፍትሔ፣ ሰላማዊ ውይይት ብቻ እንደኾነ፣ አቶ ደመቀ ገልጸው፣ ለዚኽም፣ የኢትዮጵያ ኹሉን አቀፍ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንና የሽግግር ፍትሕ ትግበራ ወሳኝነትን አመልክተዋል፡፡ በሒደቱም፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድጋፉን እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

መንግሥት፣ ለሰላማዊ መፍትሔ ቅድሚያ መስጠት አለበት፤ በማለት በተደጋጋሚ የገለጸው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ትላንት ባወጣው መግለጫ፣ “ለሰላማዊ መፍትሔ” አጽንዖት ሰጥቷል፡፡

ኮሚሽኑ፣ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን(ኢጋድ)፣ የአፍሪካ ኅብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና በኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ አካላት እና ሚሲዮኖች፣ በግጭቱ ተሳታፊ ወገኖች መካከል የሚደረጉ ውይይቶችን እንዲያመቻቹና እንዲደግፉም ጠይቋል።

አቶ ደመቀ መኰንን፣ ዛሬ ማክሰኞ፣ በዐዲስ አበባ ለሚገኙ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት በሰጡት ማብራሪያ፣ በኢትዮጵያ ያሉ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት፣ የመንግሥትን ጥረት እንዲደግፉ ቢጠይቁም፣ “በዐማራ ክልል ያለውን ችግር የሀገር ውስጥ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ” በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እንደታቀደ አስታውቀዋል፡፡

ሚኒስትሩ ይህን ይበሉ እንጂ፣ በክልሉ ያለው ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ፣ ግጭቱን በውይይት ለመፍታት፣ በተግባር ጥረት ስለ መጀመር አለመጀመሩ፣ ከሌላ የመንግሥት አካል በግልጽ የተባለ ነገር የለም፡፡

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ሚኒስትሩ ዶክተር ለገሰ ቱሉ ግን፣ ባለፈው ሳምንት ዐርብ በሰጡት መግለጫ፣ መንግሥት፣ ማንኛውንም ጥቃት መከላከል የሚያስችል ኀይል እንደገነባ አስታውቀዋል፡፡ የዐማራ ክልል ግጭት በሰላም እንዲፈታ ከተፈለገ ግን፣ ጽንፈኛ እና ዘራፊ ያሉት አካል፣ “ትጥቁን ፈትቶ ወደተዘጋጁለት ካምፖች መግባት ይኖርበታል፤” የሚል ቅድመ ኹኔታ አስቀምጠዋል፡፡

አቶ ደመቀ ከሰጡት አጭር ማብራሪያ በኋላ፣ ለብዙኀን መገናኛ ዝግ በነበረው ቆይታ፣ የፍትሕ ሚኒስትሩ ዶር. ጌዲዮን ጢሞቴዎስ፣ ሰፋ ያለ ማብራሪያ መስጠታቸው ታውቋል፡፡ ኾኖም፣ ስለ እርሳቸው ማብራሪያ እና ስለተደረገው አጠቃላይ ውይይት፣ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ የወጣ መረጃ የለም፡፡

ከሁለት ሳምንት በፊት፣ በዐማራ ክልል የተቀሰቀሰውን የትጥቅ ግጭት ተከትሎ፣ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች፣ በቁጥር ያልገለጻቸው በርካታ ሰላማዊ ሰዎች እንደተገደሉ፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ በትላንቱ መግለጫው አመልክቷል፡፡

ይኹን እንጂ፣ በግጭቱ ስለደረሰው የጉዳት መጠን፣ እስከ አሁን ከመንግሥት አካል የተሰጠ ዝርዝር መግለጫ የለም፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG