Text:- የደብረ ብርሃን ከተማ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ምንውየለት ጭንቅሎ ትናንት ማምሻውን ማንነታቸው ባልታወቀ ሰዎች በጥይት መገደላቸውን የከተማ አስተዳደሩ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ላይ ይፋ አድርጓል፡፡
ኮማንደሩ በከተማዋ በደማቅ ስነስርአት የሚከበረው የስላሴ ዓመታዊ በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ ሲያስተባብሩና አመራር ሲሰጡ መቆየታቸውን ጽ/ቤቱ አስታውቋል፡፡
በዓሉ ተጠናቅቆ ለሌላ የጸጥታ ስራ ተሰማርተው ባሉበት ሰዓት ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ተተኩሶባቸው ወደ ህክምና ተቋም ቢወሰዱም ህይወታቸውን ማትረፍ እንዳልተቻለ ጽ/ቤቱ ገልጿል፡፡
ጽ/ቤቱ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ባልተለመደ መልኩ ታዋቂና ጠንካራ የፖለቲካም ሆነ የጸጥታ ዘርፍ አመራሮች ያላቸውን ግለሰቦች የመግደል እንቅስቃሴ መታየቱን ገልጾ የከተማዋን ሰላም ለማደፍረስ እና ልማትን ለማዳከም የታሰበ ሲል የገለጸውን ተግባር አውግዟል፡፡
ኮማንደር ምንውየለት ጭንቅሎ ከአባታቸው ጭንቅሎ ወርቅነህ እና ከእናታቸው ላንችአደላሁ እንደሻው የካቲት 21 ቀን 1965ዓ.ም በሰሜን ሸዋ ዞን መራሃቤቴ ወረዳ ኮራ ወንጭት ቀበሌ መወለዳቸውን፤ ከየካቲት/2014ዓ.ም ጀምሮ የከተማዋ ፖሊስ አዛዥ በመሆን ማገልገላቸውን የደብረብርሃን ከተማ አስተዳደር መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ኃላፊ መቅደስ ብዙነህ ካጋሩን የህይወት ታሪካቸው መረዳት ችለናል፡፡
የሶስት ወንድ ልጆች አባት የሆኑት የኮማንደር ምንውየለት የቀብር ስነስርአት ዛሬ ከሰዓት በኋላ ቤተሰቦቻቸው፣ የስራ ባልደረቦቻቸውና ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች በተገኙበትደብረ ብርሃን ከተማ በሚገኘው እግዚአብሔር አብ ቤተክርስቲያን ዛሬ ተፈጽሟል፡፡
ግድያው በ12 ቀናት ውስጥ በሰሜን ሸዋ ዞን የተገደሉትን አመራሮችና የጸጥታ ዘርፍ በልደረቦች ቁጥር ወደ ሶስት አሳድጎታል፡፡
ሰኔ 27/2015ዓ.ም በሰሜን ሸዋ ዞን የሸዋሮቢት ከተማ አስተዳደር ፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ አብዱ ሁሴን፤ ሰኔ 29/2015ዓ.ም ምክትል ሳጅን ያለለት ደጉ የተባሉት የሸዋሮቢት የፖሊስ ባልደረባ ጸጥታ በማስከበር ስራ ላይ እንዳሉ መገደላቸውን የሸዋ ሮቢት ከተማ አስተዳደር መንግስት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ገልጾ ነበር፡፡
በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራር ግርማ የሽጥላ በትውልድ ቦታቸው ሰሜን ሸዋ ዞን መሀል ሜዳ አካባቢ የተገደሉት ሚያዝያ 19 ቀን 2015 ዓ.ም. ነበር፡፡
መድረክ / ፎረም