በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ዓመታዊው የዓለም የስደተኛ ቀን እየተከበረ ነው


ዓመታዊው የዓለም የስደተኛ ቀን እየተከበረ ነው
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:55 0:00

ዓመታዊው የዓለም የስደተኛ ቀን እየተከበረ ነው

ዛሬ፣ እ.አ.አ ሐምሌ 20 ቀን፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓመታዊው የዓለም የስደተኞች ቀን ነው። በዓለም ዙሪያ፣ ከግጭቶች እና ከሌሎችም ስጋቶቻቸው ከለላ ፍለጋ፣ አገራቸውን ጥለው ለወጡ ከ35 ሚሊዮን በላይ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች መፍትሔ ይፈለግላቸው ዘንድ፣ የመንግሥታቱ ድርጅት ባለሥልጣናት ተማጥኖ አቅርበዋል።

ስደተኞችን፣ በጥላቻ ዓይን ማየት እየጨመረ ባለበት በዚኽ ወቅት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፥ በጦርነት፣ በመሳደድ፣ በሰብአዊ መብቶች ረገጣ፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በሌላም መከራ ምክንያት፣ ለስደት ስለተዳረጉ ሰዎች ጽናት እና ኅብረተሰባዊ አስተዋፅኦ ትኩረት በመስጠት፣ የዛሬውን የዓለም የስደተኞች ቀን በማክበር ላይ ነው።

የዘንድሮው የዓለም የስደተኞች ቀን፣ በዓለም ዙሪያ የመከራ ኑሮ እየገፉ ለሚገኙት፣ ከ35ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች፣ ያሉባቸውን ፈተናዎች በመጥቀስ፣ ዓለም አቀፍ ጥበቃ ማግኘት ሕጋዊ መብታቸው እንደኾነ በማስገንዘብ ላይ ነው።

የስደተኞቹንና የሚያስተናገዳቸውን ኅብረተሰብ የኑሮ ኹኔታ የሚያሻሽሉ ተጨባጭ ርምጃዎች እንዲወሰዱ፣ ጥሪ ያቀረቡት የመንግሥታቱ ድርጅት ባለሥልጣናት፣ ስደተኞች፥ ለራሳቸው እና ለቤተሰቦቻቸው የተሳካ የወደፊት ሕይወት እንዲገነቡ የሚያስችል ዕድል እንዲመቻችላቸው ተማፅነዋል።

የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ፣ በኬኒያ፣ በግዙፉ የካኩማ የስደተኞች ካምፕ በተካሔደ ሥነ ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር፣ “እዚኽ የተገኘኹት፥ ስደተኞች የትም ይኹኑ የት፣ ያለው ኹኔታ ምንም ይኹን ምን፣ ይህን ተስፋ ልንሰጣቸው፣ ዕድሎችንና መፍትሔዎችን ልናቀርብላቸው እንደምንችል እንደሚገባም የተቀረውን ዓለም ለማሳወቅ ነው፤” ብለዋል።

የኬንያ መንግሥት፣ ለስደተኞቹ የተሻሻለ አሳታፊ ፖሊሲ ለመዘርጋት በመወጠኑ፣ ኮሚሽነሩ አድናቆት ሰጥተዋል።"ይህም፣ ኬኒያ ከምታስተናግዳቸው፣ ቁጥራቸው ወደ ግማሽ ሚሊዮን ከሚደርሱ ስደተኞች መካከል ብዙዎቹ፣ ካስጠለሏቸው ኬንያውያን ማኅበረሰቦች ጎን ለጎን እየሠሩ እንዲኖሩ፣ በራስ የመተማመን መንፈሳቸው እንዲዳብር ይረዳል፤” ያሉት ፊሊፖ ግራንዲ፣ ኢኮኖሚውን በማሳደግ አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱና በሰብአዊ ርዳታ ላይ መተማመናቸው እንዲቀንስ ያደርጋል፤” ሲሉም አስረድተዋል።

“ከአገሩ ለወጣ ተስፋ መስጠት” በሚለው፣ በዘንድሮው የዓለም የስድተኞች ቀን መሪ ርእስ፣ በተጠለሉባቸውም ይኹን ተቀብለው በሚያሰፍሯቸው ሀገራት፣ ኑሯቸውን ለመገንባት ዕድል ስለማያገኙ፣ ለበርካታ ዐሥርት ዓመታት በእንግልት ለሚኖሩ ስደተኞች አሳታፊ መፍትሔ በመስጠት ላይ ትኩረት ለመሳብ ታልሟል።

የዜና እና የብዙኃን መገናኛ ሓላፊው ማቲው ሶልትማርሽ፣ ለቪኦኤ በሰጡት ቃል፣ “ስደተኞች፣ ብዙ ጊዜ የተጠጉትን ኅብረተሰብ ዐቅም የሚበዘብዙ፣ ቁጭ ብለው የሰብአዊ ርዳታ የሚጠብቁ ተደርገው ይታያሉ። እንደዚኽ ካለው አስተሳሰብ መራቅ አለብን። ስደተኞች በዋናነት የሚፈልጉት፣ በእግራቸው ቆመው ቤተሰባቸውን እየደገፉ እና ልጆቻቸውን እያስተማሩ መኖር ነው። በተጠለሉበት ዐዲስ ኅብረተሰብ ውስጥ፣ አስተዋፅኦ ለማበርከት በተቸገሩ ጊዜ፣ መጠጊያ የሰጣቸውን ሕዝብ ለማመስገን ይሻሉ። ነገር ግን፣ ለኑሯቸው ሠርተው ለማግኘት ዕድል በማያገኙበት ርቆ በሚገኝ ካምፕ ውስጥ፣ የግድ መቀመጥ ካለባቸው፣ ያላቸው ዕድል፥ ሰብአዊ ርዳታ ከመጠበቅ ሌላ ምርጫ አይኖራቸውም፤” ብለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ በዓለም ላይ፣ በኹኔታዎች አስገዳጅነት ከቀዬአቸው የሚፈናቀሉ ሰዎችን በሚመለከተው ዓመታዊ ሪፖርቱ፣ እ.አ.አ ባለፈው 2022 መጨረሻ፣ 108 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሰዎች ከመኖሪያቸው እንደተፈናቀሉ አመልክቷል። ይህ አኀዝ፣ በየትኛውም ዓመት ከነበረው የገዘፈ እንደኾነ ገልጾ፣ የዩክሬኑ ጦርነት፣ ለአምናው የተፈናቃዮች ቁጥር ማሻቀብ፣ ዋናው ምክንያት እንደኾነ ጠቅሷል። ከዚያ ወዲህ ደግሞ፣ በአመዛኙ በሚያዝያ ወር አጋማሽ በተቀሰቀሰው በሱዳኑ ጦርነት ሳቢያ፣ አጠቃላዩ የተፈናቃዮች ቁጥር፣ ከ110 ሚሊዮን መብለጡን አስረድቷል።

በተለምዶ እንደሚታሰበው ሳይኾን፣ በዓለም ዙሪያ ከሚገኙት ስደተኞች ውስጥ፣ 76 ከመቶውን የሚያስተናግዱት፣ ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሀገራት እንጂ ባለጸጎቹ እንዳልኾኑ ያመለከተው የተመድ የስደተኞች ኮሚሽን(UNHCR)፣ ከአጠቃላዩ የስደተኞች ቁጥር፣ ከአምስቱ አንዱ የተጠለሉት፣ ከሰሃራ በታች ባሉት የአፍሪካ ሀገራት እንደኾነ አሳውቀዋል።

የድርጅቱ የብዙኃን መገናኛ ክፍል ሓላፊው ማቲው ሶልትማርሽ፣ ለቪኦኤ በሰጡት ቃል፣ የስደተኞች እና የተፈናቃዮች ቁጥር በጨመረ መጠን፣ ፀረ ስደተኛ አመለካከቶች እና መጤ ጠል የጥላቻ ንግግሮች እየተባባሱ እንደመጡ ገልጸዋል፡፡ አክለውም፣ “በተለይም፣ በአገር ውስጥ አስቸጋሪ ኹኔታዎች ሲፈጠሩና ኢኮኖሚው ሲዳከም፣ በባዕዳን ላይ ማሳበቡ ቀላል ስለሚኾን፣ ስደተኞች ምክንያት ተደርገው ይወነጀላሉ፤” ብለዋል። //ሊሳ ሽላይን ከጄኔቫ ያጠናቀረችውን ሙሉ ዘገባ ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።//

XS
SM
MD
LG