በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኢንዶ-ፓስፊክ የአሜሪካ እና ቻይና የኃይል ፉክክር ፍጥጫውን ጨምሮታል


በኢንዶ-ፓስፊክ የአሜሪካ እና ቻይና የኃይል ፉክክር ፍጥጫውን ጨምሮታል
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:11 0:00

በኢንዶ-ፓስፊክ የአሜሪካ እና ቻይና የኃይል ፉክክር ፍጥጫውን ጨምሮታል

ደቡብ ኮሪያ፣ የቻይና እና የሩሲያ ወታደራዊ አውሮፕላኖች ከኮሪያ ባሕረ ሰላጤ (ፔኒንሱላ) በስተደቡብ እና በስተምስራቅ በኩል፣ የአየር መከላከያ ክልሏን ጥሰው መግባታቸውን ተከትሎ ተዋጊ አውሮፕላኖቿን በአስቸኳይ ወደ ስፍራው ልካለች። ድንገተኛ ወረራው የተፈፀመው፣ ዩናይትድ ስቴትስ እና ቻይና በታይዋን ጠባብ የውሃ መተላለፊያ እና በደቡብ ቻይና ባህር ዙሪያ የገቡትን እሰጥ አገባ ተከትሎ ሲሆን፣ የባይደን አስተዳደር ሁኔታውን የቤይጂንግ ጦር ጠብ አጫሪነት እየጎለበተ ለመምጣቱ እንደምሳሌነት ይጠቅሰዋል።

እሁድ እለት በታይዋን ጠባብ የውሃ መተላለፊያ መስመር ውስጥ፣ የቻይና የጦር መርከብ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ የሚሳይል መቃወሚያ መርከቦች መጠጋታቸውን ጨምሮ፣ ከሁለት ሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥ፣ በቻይና እና አሜሪካ መርከቦች እና አውሮፕላኖች መካከል ሁለት ክስተቶች ተፈጥረዋል።

ክስተቱ ደግሞ በደቡብ ቻይና ባህር ላይ በዩናይትድ ስቴትስ፣ ጃፓን እና የፊሊፒንስ ባህር ዳርቻ ጥበቃዎች መካከል ከሚካሄደው የሶስትዮሽ የባህር ኃይል ልምምዶች ጋር ተገጣጥሟል። ሁኔታውን ተከትሎ ምላሽ የሰጡት ቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ዋንግ ዌንቢን "የመጀመሪያውን ትንኮሳ የፈፀመችው ዩናይትድ ስቴትስ ናት። የቻይና ወገን ሁኔታውን በሚመለከቱ ህጎች እና መመሪያዎች መሰረት ክስተቱን አስተናግዶ ምላሽ ሰጥቷል" ሲሉ አሜሪካንን ተጠያቂ አድርገዋል።

ከቅርብ አመታት ወዲህ በቻይና እና እንደ ፊሊፒንስ ባሉ የሌሎች ሀገራት መርከቦች መካከል የሚደረጉ ያልተጠበቁ ግንኙነቶች እንዲሁም የቤይጂንግ ጦር በቀጠናው የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች እየጨመሩ መጥተዋል።

ዩናይትድ ስቴትስም እንዲሁ በቀጠናው ካሉ አጋሮቿ ጋር የምታደርገውን ልምምድ በመጨመር፣ ፈርጣማ ጡንቻ የማሳየትን መንገድ መርጣለች። ቤይጂንግ ግን እነዚህ ትንኮሳዎች፣ በቀላሉ ወደ ግጭት ሊያድጉ ወደሚችሉ ተደጋጋሚ ክስተቶች ያመራሉ ትላለች።

በኢሮዢያ ቡድን ፋውንዴሽን ጥናት አጥኚ የሆኑት ዙሪ ሊኔትስኪ- ሁኔታው ጥሩ አካሄድ አለመሆኑን ሲያስረዱ "በተለይ ደግሞ በዩናይትድ ስቴትስ እና በቻይና ከፍተኛ መከላከያ ባለስልጣናት መካከል ያለው ግንኙነት እጅግ የተገደበ በመሆኑ፣ ይሄ አዲስ እና የሚረብሽ ልማድ ነው" ብለዋል።

ዩናይትድ ስቴትስ ግን በከፊል ጥፋተኛ መሆኗን አትቀበልም። ሆኖም ከቤይጂንግ ጋር ለመነጋገር ሙከራ እያደረገች መሆኑን የአሜሪካ የብሄራዊ ደህንነት ምክርቤት ቃል አቀባይ የሆኑት ጆን ከርቢ ይናገራሉ።

"በዚህ ላይ በጣም፣ በጣም ጠንክረን እየሰራን ነው። ፕሬዝዳንቱም (ባይደን እና ቺ ጂንፒንግ) በተገናኙበት በባሊ ወደነበረው የቻይና እና የዩናይትድ ስቴትስ መንፈስ መመለስ እንደምንችል እርግጠኛ ናቸው።"

ባለፈው ሳምንት በሲንጋፖር ሻንግሪ-ላ፣ በተካሄደው አመታዊ ጉባዔ ላይ፣ ዋሽንግተን የመከላከያ ሚኒስትሯ ሎይድ ኦስቲን እና የቻይና አቻቸው ሊ ሻንግፉ ፊት ለፊት እንዲገናኙ ያቀረበችውን ጥያቄ ቤይጂንግ፣ የአሜሪካ አስተዳደር በሊ ላይ የጣለውን ማዕቀብ አላነሳም በሚል ሳትቀበል ቀርታለች።

የአሜሪካ ባለስልጣናት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ወደ ቤይጂንግ እንዲጓዙ እና፣ በጥር ወር ላይ አሜሪካ የቻይናን የስለላ ፊኛ መታ መጣሏን ተከትሎ ዋሽንግተን ሰርዛው የነበረውን ጉብኝት እንዲያካሂዱ፣ ተለዋጭ ቀጠሮ ለማስያዝ ጥረት እያደረጉ ነው።

XS
SM
MD
LG