በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ህወሓት የምርጫ ቦርዱን ሕጋዊ ሰውነት የሚያሳጣ ውሳኔ እንደማይቀበል አስታወቀ


ህወሓት የምርጫ ቦርዱን ሕጋዊ ሰውነት የሚያሳጣ ውሳኔ እንደማይቀበል አስታወቀ
please wait

No media source currently available

0:00 0:07:11 0:00

ህወሓት የምርጫ ቦርዱን ሕጋዊ ሰውነት የሚያሳጣ ውሳኔ እንደማይቀበል አስታወቀ

ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ(ህወሓት)፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፥ ስለ ፓርቲው የሕጋዊ ሰውነት ስረዛ ያስተላለፈውን ውሳኔ እንደማይቀበልና እንዲነሣለት ያቀረበውን ጥያቄ ቦርዱ ውድቅ ማድረጉን ተቃውሟል፡፡

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በበኩሉ፣ ውሳኔው፣ በሕግም በፖለቲካም ተቀባይነት የለውም፤ ብሏል። የአሜሪካ ድምፅ ያነጋገራቸው የሕግ ምሁራንም፣ የምርጫ ቦርድ የስረዛ ውሳኔ፣ የትግራይ ክልልን ፖለቲካ ሊጎዳ እንደሚችል አመልክተዋል፡፡ የቦርዱን የሕግ አተረጓጎም አሳማኝ ኾኖ እንዳላገኙት የጠቀሱት ምሁራኑ፣ ይልቁንም ቦርዱ፣ የአገሪቱን ነባራዊ ኹኔታ ግምት ውስጥ ያስገባ የሕግ አተረጓጎም ተከትሎ ለዴሞክራሲ ምቹ ኹኔታ በሚፈጥር መልኩ ውሳኔውን እንዲያቃና ጠይቀዋል፡፡

በሌላ በኩል፣ የብሔራዊ ምርጫ ቦርዱ፣ በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱት ባይቶና ዓባይ ትግራይ እና ሣልሳይ ወያነ ትግራይ፣ መሥራች ጉባኤያቸውን እንዲያካሒዱ መወሰኑን አስታውቋል፡፡ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ(ህወሓት)፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፥ የፓርቲው ሕጋዊ ሰውነት መሰረዙን አስመልክቶ ያስተላለፈው ውሳኔ ይነሣልኝ፤ ሲል፣ ያቀረበውን ጥያቄ ቦርዱ ውድቅ ማድረጉን ተቃውሟል፡፡ ህወሓት በመግለጫው፣ የቦርዱ ውሳኔ፥ የፕሪቶርያውያን የሰላም ስምምነት እና ሕግን መሠረት ያላደረገ ነው፤ በማለት እንደማይቀበለው አስታውቋል::

የፕሪቶርያው ስምምነት ማዕከል፥ ሰላም፣ ሰብአዊ መብት፣ ዴሞክራሲ፣ ተጠያቂነት እና ወደ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዐት መመለስ መኾኑን በመግለጫው ያተተው ህወሓት፣ ይህን ስምምነት በመተግበር ረገድ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት እና ህወሓት በተናጠል እና በጋራ ግዴታቸውን እየፈጸሙ እንደሚገኙ ገልጿል::

ኾኖም፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፥ የህወሓትን ድርጅታዊ ህልውና የሚያሳጣ የሕጋዊ ሰውነት ስረዛ ውሳኔ እንዲያነሣ የቀረበለትን ጥያቄ ውድቅ ያደረገው፣ ከሰላም ስምምነቱ ውጪ በኾነ አካሔድ እንደኾነ ህወሓት ተችቷል፡፡ የቦርዱ ውሳኔ፥ የሰላም ስምምነቱን የማይቀበል፣ እየተጠናከረ የመጣውን የስምምነቱን ትግበራ ባለቤት አልባ የሚያደርግ፣ እንዲሁም ከጦርነት ወደ ሰላማዊ ትግል የሚመለሱ የፖለቲካ ኃይሎችን ከማበረታታት ይልቅ የሚያፈርስና ዘላቂ ሰላም የማያመጣ ነው፤ በማለት ተቃውሞውን አስረድቷል፡፡

በቀጣይም፣ ከሚመለከታቸው አካላት ጋራ እንደሚወያይበት ያመለከተው ፓርቲው፣ ቦርዱ ውሳኔውን ዳግም እንዲያጤነው ጠይቋል፡፡ በጉዳዩ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት እና የአፍሪካ ኅብረት እገዛ እንዲያደርጉለትም፣ ህወሓት በመግለጫው ጥሪ አቅርቧል፡፡

በሌላ በኩል፣ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ በህወሓት የሕጋዊ ሰውነት ስረዛ ጉዳይ ያሳለፈውን ውሳኔ በመቃወም መግለጫ አውጥቷል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፥ በኢትዮጵያ እየታየ ያለውን የሰላም ተስፋ ከመደገፍ ይልቅ፣ የሰላም ስምምነቱ ዋናው ባለቤት የኾነው ህወሓት፣ ህልውና እንዳይኖረው ለማድረግ ያስተላለፈው ውሳኔ እንደኾነ ጠቅሶ፣ ውሳኔው፥ በሕግም በፖለቲካም ተቀባይነት የለውም፤ ብሏል፡

የጊዜያዊ አስተዳደሩ መግለጫ፣ የቦርዱ ውሳኔ፥ ህወሓትን ወክለው በትግራይ አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ ለሚሳተፉት ከፍተኛ የፓርቲው አመራሮች እውቅናን በመንፈግ፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩን ጠቅላላ ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል፣ እንዲሁም የሰላም ስምምነቱን የሚፈታተን ነው፤ በማለት ተቃውሞታል::

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የተጀመረውን ተስፋ ሰጪ የሰላም መንገድ ለመደገፍ፣ ሕግን፥ በአዎንታዊ የትርጉም ሥርዐት ከመረዳት ይልቅ፤ ቴክኒካዊ በኾነ አረዳድ፣ ሰላማዊ ፖለቲካዊ መግባባትን ማደናቀፍ አይኖርበትም፤ ሲል፣ ቦርዱ ውሳኔውን መርምሮ እንዲያስተካክል ጊዜያዊ አስተዳደሩ ጠይቋል::

ከህወሓት እና ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ምላሽ በኋላ፣ የአሜሪካ ድምፅ በጉዳዩ ላይ አስተያየት የጠየቀው፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት፣ ፓርቲው፥ የቦርዱን ውሳኔ ስለ መቃወሙ፣ ያስገባው ቅሬታም ኾነ ደብዳቤ የለም፤ ብሏል።

የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት፣ ጥቅምት 24 ቀን 2015 ዓ.ም. ከተጀመረ ከኹለት ወር ተኩል በኋላ፣ ህወሓት፥ ኃይልን መሠረት ያደረገ የዐመፃ ተግባር ላይ መሳተፉን ማረጋገጡን ጠቅሶ፣ የፓርቲው ሕጋዊ ሰውነት እንዲሰረዝ፣ ጥር 10 ቀን 2013 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባስተላለፈው ውሳኔ፤ የፓርቲው ሓላፊዎች በፓርቲው ስም እንዳይንቀሳቀሱ፣ የፓርቲው ንብረት ህወሓት ዕዳ ካለበት እንዲከፈልበትና የቀረው ንብረት ደግሞ ለሥነ ዜጋ እና ለመራጮች ትምህርት እንዲውል ወስኖ ነበር።

ህወሓት፣ ሚያዝያ 28 ቀን 2015 ዓ.ም. ለቦርዱ በጻፈው ደብዳቤ፣ በትግራይ ክልል የነበረው ጦርነት፣ በሰላማዊ እና በሕገ መንግሥታዊ መንገድ እንዲፈታ፣ ፓርቲው ከፌዴራሉ መንግሥት ጋራ ስምምነት ላይ መድረሱን ጠቅሶ፤ የቦርዱ የቀደመ ውሳኔ እንዲነሣለት መጠየቁን፣ ቦርዱ ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ አውስቷል።

የምርጫ ቦርዱ፣ ይህን የህወሓት ጥያቄ መሠረት አድርጎ፣ ግንቦት 4 ቀን 2015 ዓ.ም. በአካሔደው ስብሰባ፣ የፓርቲውን ጥያቄ መመርመሩንና ቀደም ሲል በፓርቲው ላይ ያሳለፈው ሕጋዊ ሰውነትን የሚያሳጣ ውሳኔ ዐዋጅን መሠረት አድርጎ መወሰኑን አስረግጧል፡፡ ለስረዛ ውሳኔው መሠረት የነበረው፣ የህወሓት፥ ኃይልን መሠረት ያደረገ የዐመፃ ተግባር አሁን አለመኖሩን የጠቀሰው ቦርዱ፣ የፓርቲውን ሕጋዊ ሰውነት ዳግም ለመመለስ የሚያስችሉ ድንጋጌዎች፣ በዐዋጅ 1162/2011 ላይ ባለመስፈሩ፣ የፓርቲውን ሕጋዊ ሰውነት የማስመለስ ጉዳይ በሕግ የተደገፈ ኾኖ እንዳላገኘው አስታውቋል።

በመቐለ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር አቶ ገብረ መስቀል ኃይሉ፣ የምርጫ ቦርድ ውሳኔ አሳማኝ ኾኖ እንዳላገኙት ተናግረዋል። በውሳኔው አሰጣጥ ላይ ያላቸውን የተቃውሞ አስተያየት ሲያስረዱም፤ “ሕግ በትርጉም ይሰጣል እንጂ፣ እንደዚኽ የተወሰኑ አጀንዳዎችን እየለየ አያስቀምጥም። ስለዚኽ፣ የአገሪቱን ነባራዊ ኹኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት ስሜት በሚሰጥ መልኩ ትርጉም መሰጠት ይገባዋል፡፡ ‘በሕግ አልተደነገገምና ይህ ዐይነት ውሳኔ ነው የምሰጠው' ማለት አይገባም፡፡ ሕግ በሒደት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ሁሉንም አጀንዳዎች ሊይዝ አይችልም፡፡ እንዲህ ያሉ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ፣ የሕጉን ዓላማ በሚያሳካ መልኩ ነው የሚተረጎመው፤” ብለዋል፡፡

ምርጫ ቦርድ አያይዞም፣ ፓርቲው ሕጋዊ ሰውነት ይዞ መንቀሳቀስ የሚችለው፣ በዐዋጁ መሠረት፣ በድጋሚ የምዝገባ ጥያቄ ሲያቀርብና ቦርዱም ሕጉን መሠረት አድርጎ ሲፈቅድ እንደኾነ ገልጿል። የፓርቲውን አመራሮች እና የንብረት ጉዳይን በተመለከተ፣ የስረዛ ውጤት በመኾኑ እንደ ዐዲስ ሊጠየቁ የሚችሉ ኾነው እንዳልተገኙ ቦርዱ አስገንዝቧል፡፡

በትግራይ ክልል የፖሊሲ ጥናት ኢንስትቲዩት ተመራማሪ ዶክተር ሙዑዝ ግደይ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያስተላለፈው ውሳኔ፣ የትግራይ ክልልን ፖለቲካ በእጅጉ ይጎዳል፤ የሚል እምነት አላቸው።

“ፓርቲው በነበረው ስም እና ቁመና፣ እንዲሁም አመራሮቹ በፓርቲው ስም ሊንቀሳቀሱና ሊሠሩ አይችሉም፤ ሲባል፣ የፓርቲው ድርጅታዊ ህልውናው እንዲጠፋ መወሰን ማለት ነው፡፡ ሁለተኛ ደግሞ፣ የፕሪቶርያ የሰላም ስምምነት የፈረመ አካል እንዲጠፋ ከተወሰነ፣ የተፈረመው ውል የለም፤ ማለት ነው።

የሕግ መምህሩ አቶ ገብረ መስቀል ኃይሉ፣ ምርጫ ቦርድ ውሳኔውን ሲያልፍ፣ ለዴሞክራሲ ምቹ ኹኔታ በሚፈጥር መልኩ መኾን ይገባው ነበር፤ ብለዋል።

ሕጉ፥ በዐመፃ ተግባር የተሠማራ ፓርቲ እንዲታገድና ንብረቱ እንደሚወረስ ይደነግጋል፡፡ ከሕጉ ውስጥ ይህን አንቀጽ ነው የተጠቀሙት፡፡ በርግጥ በእንዲህ ዐይነት ተግባር ተሳትፎ የነበረ ፓርቲ፣ ጉዳዩን በሕግ እንዲፈታ ከተደረገ፣ የፓርቲው ሕጋዊ ሰውነት ስለሚመለስበት ኹኔታ፣ በሕጉ ላይ የተቀመጠ ነገር የለም። ነገር ግን፣ ዴሞክራሲያዊነትን በሚያሳይ ኹኔታ መተርጎም አለበት ብዬ ነው የማስበው፡፡

በዐመፃ ተግባር ተሳትፎ ነበር ስለተባለው፣ በአገሪቱ ከፍተኛ ሥልጣን ያለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የሽብርተኝነት ፍረጃውን አንሥቶለት፣ ችግሩ በድርድር እና ውይይት ተፈቷል፡፡ ስለዚህ ይህን በሚያበረታታ መልኩ ነው መተርጎም የሚገባው፡፡ ይህን ሒደት የሚያደናቅፍ ትርጓሜ፣ ችግር ያለበት መስሎ ነው የሚታየኝ፡፡”

በኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ በአሸባሪነት ተፈርጆ የነበረው ህወሓት፣ ከፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት በኋላ፣ በምክር ቤቱ አባላት አብላጫ ድምፅ፣ የሽብርተኝነት ፍረጃው የተነሣለት፣ ባለፈው መጋቢት ወር እንደነበር ይታወሳል፡፡

ቦርዱ ባሳለፈው ሌላ ውሳኔ፣ በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱት ሣልሳይ ወያነ ትግራይ እና ባይቶና ዓባይ ትግራይ የተባሉ ፓርቲዎች፣ መሥራች ጉባኤያቸውን እንዲያካሒዱ መወሰኑን አስታውቋል።

XS
SM
MD
LG